በሩብ ዓመቱ ከግል ሠራተኞች የተሰበሰበው የጡረታ መዋጮ በግማሽ ቢሊዮን ጨመረ

0
767

የግል ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ በ 2012 በጀት ዓመት መጀመሪያ ሩብ ዓመት ከኹለት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር በላይ የጡረታ መዋጮ መሰብሰቡን እና ይህም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የግማሽ ቢሊዮን ብር ጭማሪ ማሳየቱን አስታወቀ።

በሩብ ዓመቱም ኹለት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ሙሉ ለሙሉ መሳካቱን የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ግዛቸው መንግሥቴ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ገንዘቡን ለመሰብሰብ ሰባት በመቶ ከሠራተኛው ደሞዝ የሚቆረጥ ሲሆን፣ ድርጅቶቹ የሠራተኛውን ደሞዝ 11 በመቶ ለኤጀንሲው እንደሚከፍሉ ተገልጿል። የጡረታ መዋጮውን በማይከፍሉ ድርጅቶች ላይ ክፍያው በየወሩ አምስት በመቶ እንዲያድግ በማድረግ ድርጅቶች ክፍያውን በተቀመጠላቸው ጊዜ ውስጥ እንዲከፍሉ እየተደረገ መሆኑን ግዛቸው ገልጸዋል።

በኤጀንሲው ከ189 ሺሕ 503 በላይ የግል ድርጅቶች ተመዝግበው የሚገኙ ሲሆን፣ ከ 1.5 ሚሊዮን በላይ የግል ሠራተኞች ተመዝግበው የጡረታ መዋጮ በመክፈል ላይ ይገኛሉ።

ከጡረታ መዋጮ የሚገኘውንም ገንዘብ በመሰብሰብ ኢንቨስትመንት ላይ ለማዋል በስፋት እየተሠራ መሆኑን የገለፁት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው፣ መንግሥት የሚያወጣቸውን የግምጃ ቤት ሰነዶች በመግዛት ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት እየተሠራ ነው ብለዋል። በኢንቨስትመንት ሥራውም በሩብ ዓመቱ 105 ሚሊዮን ብር ትርፍ ለማግኘት መቻሉንም ጨምረው አንስተዋል።

በሥራ ላይ ለማዋል ከታቀደው 95 ሚሊዮን ብር ውስጥ 78 ሚሊዮን ብር ለአበል ክፍያ እና ለሌሎች ሥራዎች ወጪ ተደርጓል ተብሏል።

የግል ድርጅት ሠራተኞች በዕድሜ፣ በሥራ ላይ ጉዳት፣ በህመም ሠራ በሚያቋርጡበት ወቅት የገቢ መቋርጥን ለመተካት እየተሠራ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በሩብ ዓመቱም ጡረታ መውጫ እድሜያቸው ለደረሰ 1 ሺሕ 199 ባለመብቶች የጡረታ አበል ክፍያ እንዲያገኙ መደረጉ ተጠቅሷል።

በሩብ ዓመቱ በርካታ የግል ድርጅቶች የሠራተኞችን ማህደር ሳያሟሉ ማምጣታቸው በሥራዎች ላይ እንቅፋት መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፣ እስከ አሁንም ሠራተኞቻቸውን ያላስመዘገቡ እና ወደ ጡረታ መዋጮ ስርዓት ያልገቡ ድርጅቶች መኖራቸው ተጠቁሟል።

ከዚህ በተጨማሪም በአንዳንድ የግል ድርጅቶች ውስጥ ከፍተኛ የሠራተኛ ፍልሰት በመኖሩ፣ ነባሮች ተቀንሰው አዳዲስ ሠራተኞች ሲገቡ እንደ አዲስ የሚመዘገብ መሆኑ ኤጀንሲው ካለው ውስን አቅም እና የሠራተኛ ቁጥር አንፃር ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑ ተጠቅሷል።

በአራት ወራት ውስጥም 503 አዳዲስ የግል ድርጅቶችን እና 45 ሺሕ በላይ ሠራተኞችን በመመዝገብ ወደ መዋጮ ስርዓቱ እንዲገቡ ተደርጓል።

በግል ድርጅት ሠራተኞች የጡረታ አዋጅ መሰረት ማንኛውምና እያንዳንዱ የግል ድርጅት የሠራተኞች የጡረታ መዋጮ ከደመወዛቸው ቀንሶና የራሱን መዋጮ ጨምሮ፣ ለሠራተኞች የወር ደሞዝ ከተከፈለበት ቀን አንስቶ በ 30 ቀናት ውስጥ የመክፈል ግዴታን በድርጅቶቹ ላይ ያስቀምጣል።

እንዲሁም ከሠራተኞቹ ደመወዝ ሊቀነስ የሚገባውን መዋጮ ሳይቀንስ የቀረ የግል ድርጅት ክፍያውን ራሱ ለመፈፀም ኀላፊ ይሆናል። ኤጀንሲው ወይም ውክልና የተሰጠው አካል ተገቢውን የጡረታ መዋጮ ለጡረታ ፈንድ ገቢ ሳያደርግ ከ 3 ወር በላይ የቆየ የግል ድርጅትን፣ በባንክ ካለው ሂሣብ ላይ ተቀንሶ ገቢ እንዲሆን የማስደረግ ሥልጣን እንደሚኖረው ያውጃል።

በኤጀንሲው የመዋጮ ስርዓት ውስጥ ያልገቡ ድርጅቶችን ለመመዝገብ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የጡረታ መመዝገቢያ እና መዋጮ መሰብሰቢያ እንዲሁም ክፍያ መፈፀሚያ ዘዴ እየተዘጋጀ ተጠናቆ በምዝገባና እና መዋጮ ዘዴዎች መረጃዎችን የመመዝገብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ኤጀንሲው ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 60 ታኅሣሥ 18 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here