ስለ ራያ ሕዝብ አሰፋፈር፣ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ያደረገውን ውሕደት እና የወረሴህ ስር ወመንግሥት አመሠራረት እንዲሁም የራያ ሕዝብ ከዐጤ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት እስከ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ድረስ ያለፈበትን የታሪክ ጉዞ፣ ብሎም የራያ “ቀዳማይ” የሚባለው የወያኔ አመፅ ራያን ለሁለት እንዲከፈል እንዳደረገው ያስነበቡን ብሩክ ሲሳይ በዚህ የመጨረሻ ክፍል መጣጥፋቸው የራያን መልሶ በወሎ መካተት፣ እንዲሁም የአሁኑን የማንነት ጥያቄ እና እንዴት ሕዝበ ውሳኔ ያግኝ በሚለው ጉዳይ ጽፈዋል።
(የመጨረሻ ክፍል)
በ1949 ደጅ አዝማች ሸዋ አስረስ እና ወረሴሁ ፊታውራሪ ሞገስ ዓሊ ከመላው ራያ ዐሥራ ስምንት የሕዝብ ተወካዮችን እየመሩ አዲስ አበባ ሔደው ራያ ከሁለት መከፈሉ ቀርቶ በመላ ወደ ወሎ ጠቅላይ ግዛት እንዲመለስ ለንጉሡ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ራያ ከወገኑ የወሎ ሕዝብ ጋር እንደገና በ1949 ተካተተ። ከዚያ በኋላ ይኼው አስተዳደር በደርግ ዘመን የቀጠለ ሲሆን የኢሕአዴግ መንግሥት በ1983 ማዕከላዊ መንግሥቱን ሲቆጣጠር፥ ራያ ከሁለት ተከፍሎ ቀድሞ በወሎ ክፍለ ሀገር የራያ ቆቦ አውራጃ ዋና ከተማ እና ማዕከል የነበረችው አላማጣ ከተማን፣ ወፍላ ወረዳ፣ ኮረም እና ዋጃ ጭምር ወደ ትግራይ ሲካለሉ ቆቦ እና አካባቢው ዞብልን ጨምሮ በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ወረዳ ተብለው ተዋቀሩ።
እንደሚታወቀው የኢሕአዴግ መንግሥት የክልል አወቃቀር እና የፌድራል ስርዓቱ መሠረት ያደረገው ቋንቋን በመሆኑ የትግራይ ክልል ወደ ግዛቱ ያስገባቸውን የራያ አካባቢዎች እንደ ትግራዋይ እና ትግርኛ ተናጋሪ በመቁጠር የአስተዳደር መዋቅሩን በመዘርጋቱ ገና ከጅምሩ በራያ ማኅበረሰብ እና ልኂቃኑ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል። እነዚህ ወደ ትግራይ የተካለሉ የራያ ግዛት ነዋሪዎች ሁሉም የአማርኛ ቋንቋን በሚገባ ይናገራሉ። አብዛኛወቹ ደግሞ ራይኛ የሚባለው እና በተለምዶ የራያ ትግርኛ የምንለውን ቋንቋ እና አማርኛ ይናገራሉ። እጅግ ጥቂቶች ደግሞ ኦሮምኛ የአፍ መፍቻቸው ሲሆን ከዚያ በተጨማሪ አማርኛ እና ራይኛን አቀላጥፈው ይናገራሉ። ከእነዚህ ቁጥራቸው ከፍ ያሉ የቆቦ እና የላስታ ግዳን ተዋሳኝ በርካታ የራያ አላማጣ ቀበሌዎች ደግሞ ከአማርኛ ውጭ ሌላ ቋንቋ አይናገሩም። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ከ1983 ጀምሮ የሚተዳደሩትም ሆነ ልጆቻቸው ትምህርታቸውን የሚከታተሉት በትግርኛ ቋንቋ ነው። በዚህም ምክንያት ሕጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዳይማሩ ሆነዋል ማኅበረሰቡም በራሱ ቋንቋ እንዳይዳኝ እና እንዳይተዳደር ተደርጓል።
እዚህ ላይ ስለ ትግርኛ ቋንቋ እና በተለምዶ የራያ ትግርኛ ስለምንለው የራይኛ ቋንቋ ግልጽ ማድረግ ይፈልጋል። ራይኛ የሚባለው ቋንቋ ምንም እንኳን የዓረፍተ ነገር መዋቅሩ የትግርኛን ቢመስሉም 70% የሚሆኑት ቃላቶቹ ግን የአማርኛ እና የኦሮምኛ ናቸው[Abraha Girma]። በራይኛ እና በትግርኛ መካከል ያለው ልዩነት በአማርኛ እና በትግርኛ ቋንቋ መካከል ካለው ልዩነት ጋር ተቀራራቢ ይሆናል ነገር ግን የራይኛ እና የትግርኛ ቋንቋ የዓረፍተ ነገሮቹ አወቃቀር ያመሳስላቸዋል። ራይኛ ላይ ያሉ ቃላቶች ትርጉማቸው በትግርኛው ተቃራኒ የሚሆኑበት አጋጣሚም ቀላል አይደለም።
በትግርኛ ቋንቋ ከተጻፉ ከ8ኛ እና 7ኛ ክፍል የተማሪዎች መማሪያ መጽሐፍት 1000 የትግርኛ ቃላት በግብታዊነት ተመርጠው ወፍላ፣ ጨርጨር እና አላማጣ አካባቢዎች ለሚገኙ ለራያ ሽማግሌዎች ቃላቱን ማወቃቸውን እና አለማወቃቸውን ተጠይቀው ወደ 870 ማለትም 87% የሚሆኑትን ቃላት አለማወቃቸውን በጥናት ተረጋግጧል[Abraha Girma]። ይህ የሚያሳየው የጎንደር አማርኛ፣ የወሎ አማርኛ፣ የሸዋ አማርኛ ወዘተ እንደምንለው አሊያም ደግሞ የተምቤን ትግርኛ፣ የሽሬ ትግርኛ፣ የአድዋ ትግርኛ እንደሚባለው የአነጋገር ዘይቤ ልዩነት ሳይሆን በመሠረታዊነት የራይኛ ቋንቋና ትግርኛ ቋንቋ ልዩነት እንደላቸው ነው።
ከቋንቋ በተጨማሪ የራያን ሕዝብ ማራኪ እና አስደሳች ባሕሎቹን እና ማንነቱን በመዋጥ አዲስ የትግራዋይ ማንነት ለማስረፅ ለአለፉት 27 ዓመታትሕወሓት በርካታ ጥረት አድርጓል።… የራያ ሕዝብ ከ1983 ጀምሮ በአብዛኛው በራሱ ልጆች ተዳድሮ አያውቅም፤ ሕወሓት የሚያስቀምጣቸው ብዙዎቹ ሹመኞች ከአዲግራት፣ አድዋ፣ አክሱም እና ሌሎች የትግራዋይነት ጠንካራ መሠረት ካላቸው አካባቢዎች ነው። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በህወሓት ማዕከላዊም ሆነ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የራያ ልጆች የሉም ነበር፤ ከዚያ ይልቅ ብአዴን በአመራርነት ደረጃ በርካታ የራያ ሰዎች ነበሩት።
እንደ ሚታወቀው የራያ ሕዝብ ከሰሜኑ የወሎ ክፍል አጎራባቹ ከሆኑት ከየጁ፣ ከዋግ እና ላስታ ግዳን ሕዝብ ጋር ያለው ቁርኝት በጉርብትና ብቻሳይሆን በጋብቻ የተሳሰረ፣ የደም እና የአጥንት ጭምር ነው። በአሁኑ ወቅት የራያ ማኅበረሰብ የተጣላን እና ደም የተቃቡ ሰዎችን‹በዘወልድ አምላክ፣ በክፍሉ አምላክ› እያለ በማስታረቅ ዛሬ ድረሰ የሰላም እሴት የሆነው ባሕላዊ የእርቅ እና የጋብቻ ሥርዓት የመሠረቱት እነ ዘወልድ እና ክፍሉ አውራ የዘር ትውልድ መነሻቸው ከምሥራቅ ላስታ ከግዳን አቡኃይ ጋራ አካባቢ ነው። ላለፉት 600 እና ከዚያ በላይ ዓመታት ማኅበረሰባዊም፣ ኢኮኖሚያዊም፣ እንዲሁም ፖለቲካዊ በሆነ መንገድ ይደረጉ በነበሩ ጋብቻዎች ምክንያት የዋግ እና ላሰታ ማኅበረሰብ ወደ ታች ወደ ቆላማው የራያ ክፍል በመውረድ በእጅጉ ተዋሕዷል።
በአብዛኛው የእስልምና ተከታይ የሆነው የሰሜን እና የምስራቁ የራያ ክፍል ሀረጉን የሚጠቅሰው ከቃሉ፣ ከወረባቦ፣ ከየጁ እንዲሁም ከአፋር ማህበረሰብ ጋር በማያያዝ ሲሆን ሰሜኑ የራያ ክፍል ደግሞ ትግርኛ የራሳቸውን የውጅርኛ ቋንቋ የዋጠባቸው ከዋጅራቶች ጋር ትስስር አለው። ይህ ለዘመናት የተካሔደውን የማኅበረሰብ ውሕደት ውጤት ነው የራያ ማንነት የሚባለው። ለዚያም ነው የራያ አባቶች “ራያና ላስታ፤ ራያና ዋግ ራስና ትራስ፣ ጥርስና ከንፈር ናቸው“ በማለት አንዱ ያለ አንዱ መኖር አይችሉም ብለውየሚገልጡት። የራያ ሕዝብ በዙሪያው ካለው የላስታ፣ የዋ፣ የየጁ እና የአፋር ሕዝብ ጋር ለዘመናት ያዳበረው ይህ የጠነከረ ትስስር እንዲላላ እናግንኙነቱወደሰሜንካሉትግራውያንጋርብቻእንዲሆንበርካታ ተግባራት ሲካሔዱ ኖረዋል።
ላለፉት 28 ዓመታት ሕወሓት በነበረው የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ የበላይነት ምክንያት አዳፍነው የነበረው የራያ ማኅበረሰብ የመብት እና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በተለያየ መንገድ ውስጥ ውስጡን ሲብላላ ቆይቷል። ይሁንና የጠቅላይ ሚንስቴር ዐቢይ አሕመድ ወደ መሪነት መምጣት ተከትሎ በተወሰዱ የለውጥ እርምጃዎች እና በተፈጠረው መነቃቃት ምክንያት ራሳቸውን በኮሚቴ ያደራጁ የማኅበረሰቡ ልጆች ወደ አደባባይ አውጥተው ማኅበረሰቡን አስተባብረው ጥያቄያቸውን ለመንግሥት አቅርበዋል። የተቋቋመው የራያ ማንነት እና መብት አስከባሪ ኮሚቴ የሁሉንም የራያ ማኅበረሰብ ፍላጎት ሊያረካ የሚችል፣ ከላይ የተጠቀሱት ሁሉም ቋንቋዎች በሕግ የሚከበሩበት፣ ሕፃናት በአፍ ቋንቋቸው የሚማሩበት፣ ማኅበረሰቡ በሚፈልገው ቋንቋ የሚተዳደርበት፣ ቋንቋዎችን ከማክበር ውጭ ያለ ፍላጎት አንደኛው በሌላው ላይ የራሱን ቋንቋ የማይጭንበት በማኅበረሰባዊ ስሪቱ ተመሳሳይ ብቻ ሳይሆን አንድ ዓይነት ከሆነው ከወሎ ማኅበረሰብ ጋር ጎን በጎን በልዩ ዞንነት በአማራ ክልል ሥር ለመተዳደር በየደረጃው ላሉ የተለያዩ የመንግሥት አካላት በሕጋዊ መልኩ ጥያቄው ቀርቧል።
ይህ የራያ ሕዝብ የሦስት ዐሥርት ዓመታት የአስተዳደር እና ማንነት ጥያቄ በአሁኑ ጊዜ ለትግራይ ክልል አስተዳደር ራስ ምታት ከመሆኑም በተጨማሪ የወቅቱን የአገራችንን የፖለቲካ አየር የተቆጣጠረ ጉዳይ ሆኗል። ከዚሁ ከራያ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ባለፉት አምስት ወራት ከ10 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፣ ቁጥራቸው ወደ 500 የሚጠጋ አረጋውያን፣ ነጋዴዎች፣ ወጣቶች እና ተማሪዎች በትግራይ ክልል በአስከፊ እስር ቤቶች ውስጥ ይገኛሉ። ይህ ሁሉ እየተካሔደ ባለበት ወቅት የራያ መብት እና ማንነት ጥያቄኮሚቴው ለራያ ሕዝብ የልዩ ዞንነት አስተዳደር ጥያቄ በማቅረቡ እና የመብት እና የማንነት ጥያቄውን ኮሚቴው በልዩ ዞንነት ነው የሚፈታው በማለቱ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የሚገኙት የራያ ቆቦ ተወላጆች እና ሌሎችም ኮሚቴውን በክፋትም ይሁን በየዋህነት በጥርጣሬ ከመመልከትም በላይ ልዩ ዞኑ ቆቦንም ይጨምራል በሚል ግርታ ተፈጥሮባቸዋል፡፡…
ይህ የልዩ ዞንነት ጥያቄ የሚወሰነው በግዴታ በኮሚቴው ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መልኩ በሕዝበ ውሳኔ ማኅበረሰቡ ሲመርጠው ብቻ ነው ይላሉ የሚችለው። በመሆኑም ይህ አሁን እየተጠየቀ ያለው ጉዳይ የሚመለከተው በትግራይ ክልል ሥር የሚገኘውን የራያ ማኅበረሰብን ሲሆን ከዚያ በመቀጠል ለጥያቄው ድጋፍ እንዲሰጥ በቅድሚያ የሚመለከተው የራያ ቆቦ ማኅበረሰብን ሲሆን ከዚያ በመቀጠል ግን በብዙ መልኩ መሰሉ እና አካሉ የሆነው የየጁ ሕዝብ፣ በደምና በአጥንት የሚተሳሰረው የላስታና የዋግ ሕዝብ እንዲሁም የአፋር ማኅበረሰብ ነው። ይህን ግንዛቤ በማስገባት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ይበልጡን ደግሞ የወሎ ሰው በትግራይ ክልል ሥር እየተዳደሩ የሚገኙት የራያ ወገኖቹ ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ መደገፍ፣ ከለላ መስጠት እና ማበረታታት ይገባዋል በማለት የኮሚቴው አመራሮች ይገልጻሉ።
ብሩክ ሲሣይ በአማካሪነት፣ ተመራማሪነት እና በኋላፊነት በማገልገል የሚገኙና በግላቸው የታሪክ ጥናትና ምርምር ሥራዎች ተነስተው የተለያዩ ታሪካዊ ጦማሮችን ያዘጋጃሉ። በኢሜይል አድራሻቸው brooh77@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።
ቅጽ 1 ቁጥር 3 ኅዳር 22 ቀን 2011