ማክሰኞ ፣ ኅዳር 18/2011 በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ሊሙ ወረዳ በተፈጠረ ግጭት የኦሮሚያ ፖሊስን ጨምሮ የበርካታ ነዋሪዎች ሕይወት ማለፉን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።
ግጭቱ የተፈጠረበት አርቁምቤ የተሰኘ አካባቢ በምሥራቅ ወለጋ ዞንና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዋሳኝ መሆኑን ያሳወቀው ቢሮው በአካባቢው ነዋሪዎችና በኦሮሚያ ፖሊስ አባላት ላይ አሰቃቂ ወንጀል ተፈፅሟል ብሏል።
በግጭቱ ሕይወታቸው ያለፈ እና የተጎዱ ሰዎች ቁጥር በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ተገልጾ፣ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች አስከሬን ነቀምቴ ሲገባ ሕዝቡ ስሜታዊ ሆኖ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉም ተጠቅሷል። በግጭቱ ግምቱ ያልታወቀ በርካታ ንብረት ወድሟልም ተብሏል።
የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ኅዳር 20/2011 ባወጣው መግለጫ በዜጎች ላይ ጉዳት ያደረሱ አካላትን ለሕግ እንደሚያቀርብ አሳውቋል።
የተገኘውን ለውጥ ለመቀልበስ ሥልጣንን ያለአግባብ ተጠቅመው ዘረፋ ሲያካሒዱ የነበሩ አካላት በተለያዩ ቦታዎች እሳትን እያቀጣጠሉ ነው ያለው መግለጫው የሰው ልጆች ላይ መፈፀም የሌለበት ወንጀል እንዲፈፀም እያደረጉ ነው ሲል ወቅሷል።
የኦሮሞን ሕዝብ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን እርስ በእርስ እንዲጋጩ እየታተሩ ስለመሆኑም አትቷል።
እነዚህ አካላት በቅርቡ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልና የሱማሌ ወሰን አካባቢ የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ የግድያ እርምጃ እንደወሰዱና የተቀናጀ ጦርነት በመክፈት በኦሮሚያ ፖሊስ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን አመልክቷል።
ቅጽ 1 ቁጥር 3 ኅዳር 22 ቀን 2011