በአዲስ አበባ አምስት ሕፃናት በጅብ ጥቃት ደረሰባቸው

0
723

ከአንድ ሳምንት በፊት አንድ ሕፃን ሕይወቷ አልፏል

በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ በተለምዶ የካ ሚካኤል ጨረቃ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ ብቻ በአምስት ሕፃናት ላይ ጅቦች ጥቃት ያደረሱ ሲሆን፣ ከአንድ ሳምንት በፊት የሦስት ዓመት ሕፃን ሕይወት ማለፉን ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።

የአምስት ዓመት ልጃቸው ላይ በጅብ ጥቃት የደረሰባቸው አበበች ዓለማየሁ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ከኹለት ወር ከአስራ አምስት ቀን በፊት እሳቸው በቄጤማ ሽያጭ ሥራቸው ላይ ሆነው ልጃቸው ላይ በጅብ ጥቃት ደርሷል። ፍራኦል በቀለ የተባለው ሕፃን ከቀኑ 12 ሰዓት ላይ ከቤቱ ወጥቶ ባለበት ጅቡ ጭንቅላቱን በመያዝ ሊበላው እንደሞከረ እና የአካባቢው ሰው ተሯሩጦ ሕይወቱን እንዳተረፈው እናቱ ይናገራሉ።

በተመሳሳይም ከ 10 ቀን በፊት ስርአተ ቀብሯ የተከናወነው የሦስት ዓመት ሕፃን ልጅ፣ እናቷ ከበር ለመውጣት ስትከፍት በር ላይ የሚጠብቀው ጅብ ከእጃቸው መንትፎ እንደወሰደባቸው እና የሕፃኗን ሕይወት ማትረፍ እንዳልተቻለ የአካባበው ነዋሪዎች ይናገራሉ። በተመሳሳይ ሳምንትም ስራዓተ ቀብሯ መፈፀሙንም ጨምረው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የአራት ልጆች እናት የሆነት እና ቄጤማ ሽጠው የሚተዳደሩተ አበበች ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ልጃቸው ላይ ጉዳት ከደረሰ በኋላ ሥራቸውን ትተው ልጃቸውን በማስታመም እና ሌሎች ልጆቻቸውን በመጠበቅ እንደሚያሳልፉ እና ጎረቤቶቻቸው በሚያደርጉላቸው ድጋፍ እንደቆዩ ተናግረዋል።

‹‹መንግሥት ይድረስልን ነው የምንለው፣ እኛ ድሆች ነን የት እንሂድ? አሁን ከ 12 ሰዓት በኋላ በር ዘግተን ነው የምንቀመጠው›› በማለት ጠይቀዋል። ‹‹ልጄ ሌሊት እንቅልፍ የለውም። ቆሞ ይሄዳል ግን አእምሮው ውስጥ ምን እንደደረሰ አላውቅም። ሲጮህ ነው የሚያድረው›› የሚሉት እናት ‹‹አራት ጥርሶቹም ረግፈዋል፣ ግን እድሜ ለጎረቤቶቼ ሕይወቱን አተረፉልኝ›› በማለት ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 60 ታኅሣሥ 18 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here