ሰኞ ሐምሌ 29ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በኮሜርሻል ኖሚኒስ በኩል ለኢትዮጲያ ንግድ ባንክ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞችን ለመቀነስ እቅድ ተይዟል መባሉ ተከትሎ በባንኩ የተለያዩ ቅርንጫፎች የሚገኙ ሰራተኞች ቅሬታቸውን እያሰሙ እንደሆነ እየተገለጸ ነው፡፡
በኮሜርሻል ኖሚኒስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በኩል ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች ናቸው ይቀነሳሉ የተባለው፡፡
በተለይም በአብዛኛው በተቋሙ እንደ መስተንግዶና መዝገብ ቤት ባሉ የስራ መደቦች ላይ ተቀጥረው የሚሰሩ ሠራተኞች ከስራቸው ሊሰናበቱ እንደሚችሉ ተነግሯል ፡፡
በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የኢትዮጲያ ንግድ ባንክ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አልሰን አሰፋ የሰራተኞች ጉዳይን በሚመለከት በተለይም በጽዳት፣መስተንግዶና መሰል አገልግሎት ላይ የሚሰሩ ሰራተኞችን ቅጥር የምንፈጽመው በኮሜርሻል ኖሚኒስ በኩል ነው ብለዋል፡፡
አሁን ላይ ሊሰናበቱ ነው የተባሉትን ሰራተኞች በሚመለከትም ባንኩ ምንም አይነት መረጃ እንደሌለው የገለጹት ሃላፊው በእነዚህ የስራ መደቦች ላይ የሚሰሩ ሰራተኞችን የሚያቀርበው ኮሜርሻል ኖሚንስን ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የሰራተኞቹ ቅሬታ ይመለከተዋል የተባለው ኮሜርሻል ኖሚኒስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በ10 ሺህ የሚቆጠሩ ሠራተኞችን በመቅጠር ለሶስተኛ ወገን የሚያሰራ ሲሆን ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደ መስተንግዶ ፣ጽዳትና እና መዝገብ ቤት ባሉ የስራ መደቦች ላይ ሰራተኞችን ያቀርባል፡፡
አሁን ላይ ታዲያ የድርጅቱ አሰራር እንደቀየረ የሚያነሱት ቅሬታ አቅራቢ ሰራተኞቹ ከስራ ሊሰናበቱ እንደሆነ ከድርጅቱ ተጽፏል ባሉት ደብዳቤ ማወቃቸውንም ጠቁመዋል
የሰራተኞቹን ቅሬታ በሚመለከት አዲስ ማለዳ የኮሜርሻል ኖሚኒስ ሃላፊዎች ለማግኘት ያደረገችው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም፡፡
ይሁን እንጂ ለአንድ የአገር ውስጥ መገኛኛ ብዙሃን ምላሽ የሰጡት የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አንድም የሚቀነስ ሰራተኛ የለም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡



