በመጻሕፍቱ ቃል አትታበይ!

0
654

ከቅርብ የሥራ ባልደረቦች ጋር ከሚነሱ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የሴቶች ጉዳይ እንዲሁም ‹ፌሚኒዝም› ነው። በቀደም ታድያ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ተጠቅሶ ክርክር ወይም ምልልስ ተጀመረ። እናት አባትን ማክበርን ከሚጠቅሰው የቅዱስ መጽሐፍም ሆነ የቁርዓን ክፍል ይልቅ ብዙዎች መርጠው የሚያውቁት ‹ሴት ለወንድ ትገዛ› ዓይነት ትርጓሜ የሚሰጡትን ክፍል ነው።

ሰው አንድም ከአምላክ አንድም ከሕግ በታች ሊሆን እንደሚገባ ግልጽ ነው። የሚገርመኝ፤ እልፍ ዓይነት አፈጣጠርና መልክ ሊጠቀም ሲችል፤ መጻሕፍቱ በመግቢያቸው እንዳኖሩት፤ አምላክ ሰውን በአምሳሉ ፈጥሯል። ታድያ ስለምን ሲል አንዱን መልኩን ከሌላው መልኩ ያበላልጣል። አንድን ሰውስ ከሌላው ሰው ዝቅና ከፍ አድርጎ ስለምን ይፈጥራል? አስተምኅሮውና መምህራኑ እንደሚሉት ሰው በግብሩ ከፍና ዝቅ ይል እንደሆነ እንጂ።

ታድያ ግን ‹ወንድ ራስ ነው› ‹ሴት ለወንድ ተፈጠረች እንጂ ወንድ ለሴት አልተፈጠረም› ‹ትገዛለት› ወዘተ የሚሉትን ከመጽሐፍ ቅዱስ ይጠቅሳሉ። እነዚህ ጥቅሶች በቅዱስ መጽሐፍ ይገኛሉ። (በቅርበት የማውቀው መጽሐፍ ቅዱስ ስለሆነ) ነገር ግን ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ‹ሴት ከወንድ ታንሳለች› ለሚል መከራከሪያ እንደሚጠቀሙበት ዓይነት መንገድ የተቀመጡ አይደሉም። ከፊታቸውና ከኋላቸው ሌሎች ቃላት ያሏቸው ናቸው።

አንድ ሰው በማኅበራዊ ገጹ ላይ ካሰፈረው ሐሳብ፤ ‹‹ኢትዮጵያዊ ነበርኩ…›› የሚለውን ነቅለው ‹‹አሁን አይደለሁም እያለ ነው›› ብለው ለማናፈስ እንደሚራወጡ ሰዎች ቁጠሩት። የጸሐፊውን ገጽ ስትመለከቱ ግን ‹‹ኢትዮጵያዊ ነበርኩ… አሁንም ነኝ፤ ወደፊትም ኢትዮጵያዊ ሆኜ እቀጥላለሁ›› የሚል ይኖረዋል።

እና ምን ለማለት ነው፤ ብዙዎች ሴት ልጅን አሳንሰው ማየታቸውን በሃይማኖታቸውና ዓለም ሁሉ በሚያውቀው መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ቁርዓን ሊያስደግፉት ሲሞክሩ ይታያል። ይህም ያሳፍራል/ ያሳዝናልም። ሴቷን እየበደሉና አንገት እያስደፉ፤ በዛ ላይ ‹‹የአምላክ ትዕዛዝ ነውና ተገዢ›› እያሉ መጨመር ምን የሚባል ነው?

በእርግጥ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ አስተያየት መስጠት ጥንቃቄን የሚፈልግ ነገር ነው። በድፍረትም በትዒቢትም ሊሆን አይገባም። ኢትዮጵያዊ ሆኖ ደግሞ ከሃይማኖት በራቀ ዓለማዊ መንገድ መነጋገር አይቻልም። የተለያየ ይሁን እንጂ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሚባል ደረጃ ሃይማኖት ያለው ሕዝብ ነው። ግን ከመካከል ብዙ ጥራዝ ነጠቆች ደግሞ አሉ።

እውነት ለመናገርም በትክክል የሃይማኖቱን አስተምኅሮ ከሚያውቁት ይልቅ አጥፊዎች ጥራዝ ነጠቅ የሆኑት ናቸው። እንጂ አስተዋይ ሰው የተጠቀሱትን ሐሳቦች በቁንጽል ወስዶ አይተውም፤ በዝርዝር ምን ማለት እንደሆኑ ይጠይቃል። ቀጥሎ መልእክቶቹ ለምን ተላለፉ? ምን ማለት ናቸው? አውዱ ምን ነበር? ወዘተ የሚሉትንም ማገናዘብ ይገባል።
ከትዒቢት ከተቆጠረብኝ ይቅርታ ይደረግልኝ፤ ነገር ግን ሴትን አሳንሶና ዝቅ አድርጎ ለማየት ሃይማኖትን መሠረት ማድረግ በራሱ ትዕቢት ነው ብዬ አምናለሁ። ሴትም ወንድም ሰው ናቸውና በፈጣሪያቸው ፊት በሥራቸው ካልሆነ በሰውነታቸው አይበላለጡም። ይህንንም መጽሐፉ ደጋግሞ የነገረንና እንደ ሰውም ሕሊናችን የሚያቀብለን እውነት ነው። ‹ወንድ ስለሆንኩ ራስ ነኝ›ና ብሎ የበላይ ለመሆን አጋጣሚ የመጠቀም ነገር አያስሔድም። ሰው ጾታውን ሠርቶ ለፍቶ ያመጣው ነገር አይደለም፤ የተሰጠው ነው። እናም አንደኛ በተሰጠ ነገር መታበይ ደስ አይልም። ሲቀጥል ፈጣሪን እያነሱ ቃሉን እየጠቀሱ ሰውን ከሰው ለማሳነስ መሞከርም ትክክል አይደለም።

እናም ጥራዝ ነጠቅ ወንዶች ሆይ፤ በመጽሐፉ ቃል አትታበዩ። አንድም ቃሉ በትክክል ምን ሲል እንደሆነ ተረዱ እንጂ ባሻችሁ ተርጉማችሁ ሴትን አታስቸግሩ፤ አንድም ቀና ባለች ቁጥር ቃል እየጠቀሳችሁ ‹ትዕዛዙን ተላለፍሽ› አትበሏት። መጀመሪያ እንደ ሰው እናስብ!
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 61 ታኅሣሥ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here