ወደ ኢትዮጵያ በአማካይ ከ300 እስከ 400 የሚሆኑ ኤርትራውያን ስደተኞች ድንበር አቋርጠው እንደሚገቡ በትግራይ ክልል የሚገኘው የእንዳባ ጉና ስደተኛ ጣቢያ አስታወቀ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጣቢያውን አስተባባሪ ሐዱሽ ኪዳኔ በመጥቀስ ባወጣው ዘገባ ላይ፣ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የስደተኞች ቁጥር እየበዛ እንደመጣ እና ይህም ተጨማሪ በጀት የሚያሻው ጉዳይ እንደሆነ ተጠቁሟል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በትግራይ ክልል በእንዳባ ጉና፣ በማዕይኒ፣ በዓዲ ሓሩሽ እና በህፀፅ እንዲሁም በሽመልባ ካምፖች የሚገኙትን ኤርትራውያን ስደተኞች ሁኔታ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። በዚህም የመጠለያ፣ የምግብ፣ የውሃ እና የመፀዳጃ አቅርቦት ውስንነት መኖሩን መመልከት እንደቻሉ አስታውቀዋል።
የስደተኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣት በአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያስከተለ እንደሚገኝም ሐዱሽ ተናግረዋል። በተለይም ደግሞ ለስደተኞች ባላፉት ዓመታት ይፈቀድ የነበረው የዩኒቨርሲቲ ትምህርት እድል አሁን ላይ በመቋረጡ ምክንያት፣ ተምረው እራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን መርዳት የሚችሉ ወጣቶች ሥራ ፈትተው መቀመጣቸውን ተናግረዋል።
እንደ ኤርትራ ስደተኞች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ገለፃ፣ ከ240 ሺሕ በላይ የተመዘገቡ የኤርትራ ስደተኞች በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሲሆን፣ 60 ሺሕ የሚሆኑት በመጠለያ ካምፖች ውስጥ እየኖሩ ነው። ይሁን አንጂ፤ ስደተኞቹ በሚኖሩበት ካምፖች አካባቢ መሰረተ ልማቶች አለመሟላታቸው ከኑሮ ውድነት መባባስ ጋር ተዳምሮ ችግር ላይ መውደቃቸውን ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ አንድ አራተኛ የሚሆኑት ኤርትራውያን ናቸው። በተለይም በአዲስ አበባ በሚገኙ የተለያዩ ኮንዶሚኒየሞች የሚኖሩ ኤርትራ ስደተኞች ቁጥራቸው የጨመረ ሲሆን፣ ይህም በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የቤት ኪራይ እንዲወደድ ምክንያት መሆኑት ከዚህ ቀደም አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል።
ለስደተኞቹ ቁጥር መጨመር ዋነኛ ምክንያት በኤርትራ ያለው የኑሮ ሁኔታ እና ወጣቶች ያለ ጊዜ ገደብ ወታደራዊ ግዳጅ እንዲፈፅሙ መገደዳቸው ሲሆን፣ የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት እና ሠርቶ የመለወጥ መብት መገደቡ እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያት እንደ አምነስቲ እና የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ድርጅት የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።
ኤርትራ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ሉአላዊነቷን ካወጀች ማግስት አንስቶ በፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ እየተመራች ሲሆን፣ በአገሪቷ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ከመኖሩ ባሻገር ዴሞክራሲያዊ ምርጫም ኖሮ አያውቅም። ኤርትራ የምትመራበት ሕገ መንግሥት የሌላት ሲሆን፣ የአገሪቷም ፓርላማ ከተበተነ ከኹለት አስርት ዓመታት በላይ ሆኖታል።
በአገሪቷም ሚኒስትሮችን ጨምሮ በሺሕዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች የሚገኙ ሲሆን፣ ይህም የዜጎች በነፃነት የመናገር እና የመጻፍ መብት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል። በአገሪቷም የሞባይል ኢንተርኔት የሌለ ሲሆን በዚህም የተነሳ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር የአጠቃላይ ሕዝቦቿን አንድ በመቶ እንኳን አይሆንም።
በቅርቡ የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ለሥራ ጉብኝት መምጣታቸው ይታወሳል። በተለይም በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት ዙሪያ የአልጀርስ ስምምነትን ጨምሮ የንግድ ለውውጥና ምክክር ይደረጋል ተብሎ ቢጠበቅም፣ በኹለቱም ወገን እስከ አሁን በግልፅ ይፋ የሆነ ነገር የለም። በአሁኑ ወቅት በኤርትራ ወደ ሦስት ሚሊየን ሰዎች ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል።
ቅጽ 2 ቁጥር 61 ታኅሣሥ 25 2012



