በቲክቶከሩ ዮሀንስ ዳንኤል (ጆን ዳንኤል) እና ሌሎች 5 ተጠርጣሪዎች ላይ የሽብር ወንጀል ምርመራ ተጀመረ

0
426

እሁድ ነሐሴ 19 ቀን 2016 ( አዲስ ማለዳ) ፌደራል ፖሊስ ሰሞኑን ከአዲስ አበባ መቀሌ ለጉዞ በተዘጋጀ አውሮፕላን ውስጥ የአቪዬሸን አሰራርን በጣሰ መንገድ ግርግርና ወከባ ፈጥረዋል የተባሉ 6 ተጠርጣሪዎች ላይ የሽብር ወንጀል ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል።

ተጠርጣሪዎቹ ዮሀንስ ዳንኤል በርሄ፣ አማኑኤል መውጫ አብርሃ፣ ናትናኤል ወንድወሰን ሹሜ፣ ኤልያስ ድሪባ በዳኔ፣ ይዲድያ ነጻነት አበበ እና እሌኒ ክንፈ ተክለአብ ናቸው።

የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ የምርመራ መዝገብ እንደሚያሳየው፥ እነዚህ ተጠርጣሪዎች በአየር መዛባት ምክንያት አውሮፕላኑ መብረር አይችልም እየተባለ፣ ተገድዶ እንዲሄድ የፈጠሩት ግርግር በወንጀል ሕጉ ተጠያቂ ያደርጋቸዋል ብሏል።

የፖሊስ የምርመራ ቡድን ተጠርጣሪዎች ላይ በወንጀል ተጠያቂ ለማድረግ ከተጀመረው ምርመራ ባሻገር፣ ከጸረሰላም ሃይሎች ተልእኮ ተቀብለው የተንቀሳቀሱ በመሆናቸው በሽብር ወንጀልም መጠርጠራቸውን ነው የሚያመላክተው።

በወቅቱ የአየር መንገዱ ከደህንነት ኃይሎች ጋር በመሆን በትዕግስት ቢማጸናቸውም፣ ድብቅ አጀንዳቸውን እያራመዱ በመሆናቸው አሻፈረን ማለታቸውንም በምርመራ መዝገቡ አካቷል።

ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ተግባር መጠቀም ሲገባቸው፣ የሀገር ኩራት እና የራሳቸው ንብረት የሆነውን አየር መንገድ ማንቋሸሻቸው አሳዛኝ ተግባር ስለመሆኑም የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ገልጿል።

በመሆኑም እነዚህ በቁጥጥር ስር የሚገኙ 6 ተጠርጣሪዎችን ቢሮው በተላለፉት የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የበረራ አሰራር ጥሰት ብሎም በሽብር ወንጀሎች የምርመራ መዝገብ ነገ ሰኞ  ነሐሴ 20 ቀን 2016 ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሏል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here