ቀረጥ ላልከፈለ መኪና ሰነድ አዘጋጅታችኋል የተባሉት መንግሥት ሠራተኞች ተከሰሱ

0
535

በአዲስ አበባ ከተማ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ትራንስፖርት መሥሪያ ቤት ተሽከርካሪ ለመመዝገብ ሊሟሉ የሚገባቸውን ሕጋዊ ሰነዶች ሳይሟሉ እና ሥልጣናቸውን በመጠቀም ያለ አግባብ በመመዝገብ በመንግሥት ላይ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ ኹለት ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ።

የሲስተም አስተዳደር እና የተሸከርካሪ ፈቃድ ባለሞያ የሆኑት ኹለቱ ተከሳሾች፣ በሥራ ላይ ከሚጠቀሙበት ሕጋዊ ሶፍትዌር የተለየ ሶፍት ዌር በሥራ ቦታቸው ላይ በማስገባት እና በይለፍ ቃል በመዝጋት ለዚሁ ዓላማ አውለዋል ሲል ዐቃቤ ሕግ የፖሊስን ማስረጃ ጠቅሶ ከሷቸዋል። ይህንን ሶፍት ዌር በመጠቀምም በጊዜያዊነት ወደ አገር ውስጥ የገባ ቶዮታ ራቫ ፎር መኪናን፣ መኪናውን ሲያሽከረክሩ በቁጥጥር ስር በዋሉት ግለሰብ ሥም በመመዝገብ መጠርጠራቸውን ክሱ ያስረዳል።

በአዲስ አበባ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በግንቦት ዘጠኝ 2011 መኪናውን ሲያሽከረክሩ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሦስተኛ ተከሳሽም፣ ሕጋዊ ስርአቱን ያልጠበቀ መሆኑን እያወቁ ወይም ማወቅ ሲገባቸው ምንም ዓይነት ውል ወይም ሕጋዊ ደረሰኝ ወይም ‹ዲክላራሲዮን› ሳይኖረው በመያዛቸው ክስ ተመሥርቶባቸዋል።

ከኹለቱ የመንግሥት ሠራተኞች መካከል ኹለተኛ ተከሳሽ የሆኑት ሄኖክ ስዩም ተስፋዬ፣ እስከ አሁን በቁጥጥር ስር ያልዋሉ ሲሆን፣ መኪናውን ሲያሽከረክሩ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሦሰተኛ ተከሳሽ የዋስትና መብታቸው ተከብሮላቸዋል። የተሸከርካሪ ብቃት ፈቃድ ባለሞያ የሆኑት አንደኛ ተከሳሽ በእስር ላይ ይገኛሉ።

በባለሥልጣኑ የመንግሥት ሠራተኛ የሆኑት ተከሳሾች ሰነድ በማጥፋት እና የሕጋዊ ሰዎችን ሥም በመጠቀም፣ በሥልጣናቸው ያለ አግባብ ተገልግለዋል ያለው ዐቃቤ ሕግ፤ ለመንግሥት ሊከፈል የሚገባው አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ብር ጉዳት አድርሰዋል በሚል ክሱን አቅርቧል።

ለጉብኝት የሚገቡ መኪኖች ወይም ከሌላ አገር በጊዜአዊነት በሚገቡ መኪኖች ሂደት በመጠቀም ገብቷል የተባለው ይህ መኪና፣ በሕጉ መሠረት የተፈቀደለትን ጊዜ ሲጨርስ ታጅቦ ከአገር መውጣት ወይም የሚጠበቅበትን የጉምሩክ ክፍያዎችን በመክፈል ነበር ሕጋዊ መሆን የሚችለው።

የሻንሲ እና የሞተር ቁጥሮችን በመቀየር ጊዜአዊ ሰሌዳ ለመኪናው እንዲሰጠው አድርገዋል ያለው ዐቃቤ ሕግ፣ ከዚህ ቀደም ሕጋዊ መኪና የተጫነበትን የጭነት ሰነድ ቁጥር በመጠቀም በባህር እና ትራንዚት አገልግሎት እንዳለፈ በማስመሰል በሕገ ወጥ ሰነድ ተገልግለዋል ሲል ለፍርድ ቤቱ አቤቱታውን አሰምቷል።

የሙስና እንዲሁም የኮንትሮባንድ ወንጀሎች ተጣምረው በመዝገቡ የተካተቱ ሲሆን፣ የመንግሥት ሠራተኛ የሆኑት ኹለቱ ግለሰቦች በሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውን መዝገቡ ያስረዳል። በተመሳሳይም የጉምሩክ ስነ ስርዓቱን ያልተከተለ ተሽከርካሪን በመግዛታቸው የተጠረጠሩትን ግለሰብ ጨምሮ ሦስቱም ተጠርጣሪዎች በአጠቃላይ መንግሥት ሊያገኝ የሚገባውን የጉምሩክ ክፍዎች በማሳጣት በፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጉምሩክ ችሎት አቅርቧቸዋል።

የጉምሩክ ኮሚሽን በመስከረም 2012 አካባቢ ባካሔደው ኦፕሬሽን፣ አምስት መቶ የሚጠጉ የጉምሩክ ግዴታቸውን አልተወጡም ያላቸውን የተለያዩ መኪኖች መያዙ ይታወሳል። ከእነዚህ መኪኖችም ከፍተኛ ቁጥሩን የሚይዘው የቶዮታ ራቫ 4 መኪኖች ነበሩ። በሶማሊያ እና በጅቡቲ አዋሳኝ ከተሞች በኩል ገብተዋል በሚል ኮሚሽኑ የያዛቸው መኪኖቹ፣ ሕገ ወጥ ሰነዶችን በመጠቀም ሰሌዳ አግኝተዋል በሚል በቁጥጥር ስር አውሏቸው ነበር።

ቅጽ 2 ቁጥር 61 ታኅሣሥ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here