በድሬዳዋ ከተማ 82 የእምነት ተቋማት የይዞታ ማረጋገጫ ተሰጣቸው

0
797

በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለሚገኙ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን፣ የሙስሊም መስጊዶች እና ለወንጌላዊያን አማኞች ቤተክርስቲያናት ሲገለገሉቸው ለቆዩ 82 የመሬት ይዞታዎች ማረጋገጫ ሰነድ ተሰጠ።

ማረጋገጫ ካገኙት መካከልም 66ቱ መስጊዶች ሲሆኑ ዘጠኝ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስትያናት እንዲሁም ሰባት የወንጌላዊያን አማኞች ናቸው። የማረጋገጫ ሰነዶቹን በአስቸኳይ ለማዘጋጀት ምክንያት የሆነውም በድሬዳዋ ከተማ በተለያዩ ጊዜያት በሚነሱ ግርግሮች፣ ግለሰቦች በቤተክርስቲያን እና መስጊድ ይዞታዎች ውስጥ አልፎ በመግባት የተለያዩ ግንባታዎችን ለማከናወን እና በሕገወጥ ደላሎች የመሬት ሽያጭ ለማከናወን እንቅስቃሴዎች በመታየታቸው መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ገልጿል።

‹‹የእምነት ተቋማት እየተደፈሩ እና በሐይማኖት ተቋማት መካከል ግጭቶችን በሚያስከትል መልኩ ግጭት ነበር›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማት እና አስተዳደር ኀላፊ ደራራ ሁቃ (ዶ/ር)፣ ጨምረውም ‹‹ባለፉት ጊዜያትም በኹለት መስጊዶች ውስጥ በመግባት የእኛ ነው በማለት ለመሸጥ እና ግንባታ ለማከናወን ሙከራዎች በመደረጋቸው ምክንያት ሐይማኖትን መሠረት ያደረገ ግጭት እንዲነሳ መንስኤ ሊሆን ችሏል›› ብለዋል።

ችግሩንም ለመቅረፍ በከተማ አስተዳደሩ በተደረገ ጥናት፣ በከተማዋ ከተመሠረቱ ከ 45 ዓመት በላይ ካስቆጠሩ ቤተ እምነቶች አብዛኛዎቹ የይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸው እና በልማድ ታጥረው የተቀመጡ መሆናቸው ተረጋግጧል።
የእምነት ተቋማት ተመሥርተው በሚገኙበት ይዞታ ማረጋገጫ እንዲያገኙ መደረጉን የተናገሩት ደራራ፣ ከተማው መሪ ፕላን የሚነካቸውን የእምነት ተቋማት ሳይቀር ምንም ሳይነካባቸው የይዞታ ማረጋገጫ አግኝተዋል ብለዋል።
በግለሰብ ቤቶች ውስጥ ተከራይተው የሚገኙ የወንጌላውያን አማኞች ቤተ ክርስቲያኖች መኖራቸውን የጠቀሱት ኃላፊው፣ ስምንት ለሚሆኑት ቦታ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

የይዞታ ማረጋገጫ እንዲኖራቸው ማድረጉ ተቋማቱ ለዘመናት ይዘውት ለቆዩት ቦታ ሕጋዊ ባለቤት እንዲሆኑ ከማስቻሉ ባሻገር፣ ቤተ እምነቶችን ለማጥቃት የሚመጡ ሰዎችን በሕግ ለመጠየቅ እና ተገቢውን ውሳኔ ለማግኘት እንደሚረዳም ተጠቅሷል።

‹‹ይህ እርምጃ በከተማዋ ሐይማኖትን መሰረት አድርገው የሚነሱ ግጭቶችን ለመቅረፍ የመጨረሻ መፍትሔ ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም። ኅብረተሰቡ ሁሉንም ሐይማኖቶች በእኩል ዐይን እንዲመለከት እና ጥበቃ እንዲያደርግ ለማድረግ መሥራት ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል›› ሲሉም ደራራ ተናግረዋል።

በድሬዳዋ ከተማ እስከአሁን ድረስ የአምልኮ ቦታ እና ተከታይ ኖሯቸው የሚንቀሳቀሱት ሦስቱ የእምነት ተቋማት ናቸው የተባለ ሲሆን፣ እስካሁን በውስጣቸው ካለ ክፍፍል ውጪ ለሰባት የፕሮቴስታንት የእምነት ተቋማት ቦታ ለመስጠት አስተዳዳሩ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ ገልፀዋል።

ከዚህ ቀደም በተከሰቱ ግጭቶችም በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከከተማው ወጣ ብለው በሚገኙ ኹለት ቤተክርስቲያኖች ላይ በተፈፀመ ጥቃት፣ በርካታ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን እና የፖሊስ ተሽከርካሪዎች ላይም የመቃጠል ጥቃት መድረሱን ደራራ አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ በኹለት መስጊዶች ላይ ሕገወጥ የመሬት ወረራ ተደርጎ ነበር። ነገር ግን የከፋ ጥቃት የሚስተዋለው በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያኖች ላይ ነው ሲሉም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በድሬዳዋ ከተማ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በተነሱ ግጭቶች የበርካታ ሰዎች ሕይወት ማለፉ የሚታወስ ሲሆን፣ ባሳለፍነው ሳምንት የተከሰተውን ጨምሮ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲም ተደጋጋሚ ግጭቶች መስተዋላቸው አይዘነጋም።

ቅጽ 2 ቁጥር 61 ታኅሣሥ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here