ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የጋዜጠኞች የሥራ ማእከል ሊያዘጋጅ ነው

0
1025

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዋና መሥሪያ ቤት ህንፃ ላይ ከ30 እስከ 40 የሚሆኑ ጋዜጠኞች ተቀምጠው ሥራቸውን የሚያካሂዱበት፣ አገልገሎት እንዲሁም መረጃ የሚያገኙበትን የሚዲያ ማእከል በጥቂት ወራት ውስጥ አጠናቆ ክፍት እንደሚያደርግ አስታወቀ።

እነዚህ ክፍሎች ጋዜጠኞቹ ተቀምጠው ሥራቸውን የሚሠሩባቸው ሲሆኑ፣ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እጅ የሚገኙ የተለያዩ ሕጎችን፣ ታሪካዊ ሰነዶችን እንዲሀም በምስል እና በድምጽ ተመዝግበው ያሉ መረጃዎችን ለማግኘት እንዲያስችል ሆኖ እንደሚዋቀርም ታውቋል። የኢንተርኔት አገልግሎትን ጨምሮ አዳዲስ የሚወጡ አዋጆች እና ደንቦችን ጋዜጠኞች በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ እንዲሁም ሥራቸውን በቀላሉ እንዲያከናውኑ ያስችላል ሲሉ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ዝናቡ ቱኑ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ባለ ዐስር ወለል ህንፃ ላይ ሥራውን የሚያከናውነው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ ለመንግሥት ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን በሰጠው የእድሳት ሥራ ዲዛይን ውስጥ የምድር ቤት ወለሉን ለዚሁ ሥራ እንዲውል በማሰብ እድሳት እንደሚያከናውንም ታውቋል። በሦስት ክፍሎች ተከፋፍሎ እየተከናወነ የሚገኘው እድሳቱ፣ በቅድሚያ የከፍተኛ አመራሩን ሥራ ቦታ አድሶ ማገባደዱን ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

በኹለተኛው ክፍልም አራት ወለሎችን እያደሰ ሲሆን፣ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይገባደዳል ሲሉ ዝናቡ ተናግረዋል። በመጨረሻው ዙር ደግሞ የሚዲያ ማእከሉን ጨምሮ ሌሎች አራት ወለሎች ከበጀት ዓመቱ መገባደድ በፊት ተጠናቀው ሥራ ይጀምራሉ ብለዋል።

ይህ የፕሬስ ክፍል በኢትዮጵያ በሚገኙ ተቋማት እምብዛም አይስተዋልም የሚሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያ ሕግ መምህር እና በሚዲያ ሕግ ማሻሻያ አስተባባሪ የሆነት ሰሎሞን ጎሹ ናቸው። በአደጉ አገራት ጋዜጠኞች ደጋግመው የሚሄዱባቸው ተቋማት ጋዜጠኞች መረጃን የሚያገኙባቸው እና የሚሠሩባቸውን ቦታዎች ማማቻቸት የተለመደ እንደሆነም ይናገራሉ።

አሁን በኢትዮጵያ ባለው ልምድ፣ መገናኛ ብዙኀን መረጃ ለማግኘት ቅፅ መሙላት እንዲሁም በርካታ ውጣ ውረዶችን ማለፍ እንደሚጠበቅባቸው የሚያነሱት ሰሎሞን፣ እንደ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ያሉ መረጃዎች በተደጋጋሚ የሚፈለጉባቸው ተቋማት መረጃዎቹን ቀድመው አዘጋጅተው ለመጠበቅ ማሰባቸው ሊበረታታ የሚገባው እንደሆነ አንስተዋል።

‹‹አዲሱ የመረጃ ነፃነት ሕግ በራሱ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተዘጋጀ ነው፤ አሁን በሕግ ባለሙያዎች እና በባለ ድርሻ አካለት ውይይት እየተደረገበት ይገኛል። የመረጃ ነፃነት ሕጉ አሰራሮችን ከመቀየር በተጨማሪ በመሬት ላይ ያለውን የአሰራር ባህል እና ልምድ ይቀይራል›› ሲሉ ሰለሞን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ‹‹ሕጉ ምንም ያህል ለውጦችን የሚያመጣ ቢሆንም፣ በፈፃሚ አካላት ላይ የሚስተዋለው የአሰራር ክፍትት ሊቀረፍ ይገባዋል። መረጃ ያላቸው የመንግሥት ተቋማት መልካም ጎናቸውን ብቻ ሳይሆን ጥፋቶችም ሲገኙ የሚጠየቁበት ክፍት የሆነ የመረጃ ፍሰት ሊኖር እንደሚገባ ማሳመን ያስፈልጋል›› ብለዋል።

ጋዜጠኞችም መረጃን ለማግኘት እስከ መጨረሻው ሊጠይቁ ይገባል ያሉት ሰሎሞን፣ አዲሱ አስተዳደር ከመጣ ወዲህ የመንግሥት ተቋማት ዓላማዎቻቸውን እና ሥራዎቻቸውን ለማሳወቅ መጣራቸው ሊበረታታ ይገባል። እንደ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ያሉ እንዲሁም ሌሎች የመንግሥት ተቋማት ስለሚያከናውኗቸው ሥራዎች ሕዝብ እንዲያወቅ ለማድረግ መሰል ለውጦችን ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል።

የመገኛኛ ብዙኀን የመረጃ ነፃነት ሕግን አዘጋጅቶ ለምክር ቤት ለማቅረብ ከባለሙያዎች እና ከሚመለከታቸው አካለት ጋር በስፋት እየሠራ መሆኑ ተገልጿል።

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 የሕግ አስከባሪ ተቋም ሆኖ መቋቋሙ ይታወቃል። በማቋቋሚያ አዋጁ መሰረት፣ ከዚህ ቀደም በፌዴራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ይከናወኑ የነበሩ የሙስና ወንጀል ክስና የክርክር ሥራዎች በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እንዲከናወኑ መታወጁ ይታወሳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 61 ታኅሣሥ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here