ቅዳሜ ነሐሴ 25 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በአፍሪካ ቀንድ የተነሳውን ውጥረት ለማርገብ ኢትዮጵያ የታጁራ ወደብን በቀጥታ እንድታስተዳድር አማራጭ ሃሳብ ከወደ ጅቡቲ መቅረቡ ተሰምቷል፡፡
ኢትዮጵያ የጂቡቲ ንብረት የሆነውን የታጁራ ወደብ “ሙሉ በሙሉ እንድታስዳድር” አገራቸው አማራጭ ሃሳብ ማቅረቧን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የባህር መዳረሻ ችግሯን ለመቅረፍ እንዲሁም ከሶማሊያ ጋር የገባችበት ውጥረት እንዲረግብ በማለም አማራጭ ሃሳቡን ሀገራቸው ማቅረቧን ሚኒስትሩ የገለጹ ሲሆን ይህን ተከትሎ ኢትዮጵያ በጅቡቲ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኘውን ወደብ እንዲሁም አዲስ የተገነባውን ኮሪደር እንድታስተዳድር ሃሳብ ቀርቧል ማለታቸውንም አስታውቀዋል።
አማራጭ ሃሳቡን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኦማር ጊሌህ ለኢትዮጵያ ማቅረባቸውን የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በተፈፃሚነቱ ዙርያ ዝርዝር አስተያየት ከመስጠት መቆጠባቸውም ተመላክቷል።
በአማራጭ ሃሳቡ ዙሪያ በሚቀጥለው ሳምንት በሚካሄደው የቻይና አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ሁለቱ መሪዎች የመወያየት እድል ሊኖራቸው እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
ይህ የተገለጸው ደግሞ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን የባሕር በር ስምምነትን ተከትሎ ከሶማሊያ ጋር የገባችበት ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት በተካረረበት በዚህ ወቅት ነው።



