ከኹለት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የመጅሊስ ምርጫ ይካሄዳል ተባለ

0
745

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አሸማጋይነት መደበኛ ምርጫ እስኪካሄድ የተዋቀረው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) ቦርድ ከኹለት ወር ባነሰ ጊዜ ቋሚ የመጅሊስ ምርጫ ለማካሄድ እየሠራ መሆኑን አስታወቀ።

በሚያዚያ 23/2011 የተቋቋመው የሽግግር ጉባኤ 26 አባላት ያሉት የባለአደራ የኡለሞች ምክር ቤት እና ሰባት አባላት ያሉት ጊዜያዊ የመጅሊስ ቦርድን ያጠቃለለ ነው። ይህ ቦርድ በስድስት ወራት ውስጥ ቋሚ ምክር ቤት በማስመረጥ ሥራውን ማስረከብ ይጠበቅበት የነበረ ቢሆንም፣ በተለይም የሃጅ ጉዞ ሥራ በመሃል በመግባቱ ከሦስት ወራት በላይ ያለ ሥራ ማሳለፉ ቋሚ ምርጫ ሳይደረግ ወራት እንዲያለፉ ምክንያት መሆኑን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች የቦርድ ሰብሳቢ ሼህ ኑረዲን ደሊሊ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ ሲቋቋም ሦስት መሠረታዊ ሥራዎችን በማከናወን ለዓመታት ሕዝበ ሙስሊሙ ሲያነሳ የቆየውን ወኪል የመምረጥ ጥያቄ በመመለስ ሥራውን ለማጠናቀቅ አቅድ ይዞ ነበር። የመጅሊሱን ደንብ እና መመሪያዎች ማሻሻል፣ የሙስሊሙን ኡለማ አንድነት ሰነድ ወደተለያዩ ባለድርሻ አካላት በመላክ በውይይት አዳብሮ ማፅደቅ እንዲሁም የምክር ቤቱን መዋቅር በማስተካከል ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ በአዋጅ እንዲቋቋም ማድረግ ዋና ዋና ሥራዎቹ ነበሩ።
እነዚህን ኀላፊነቶች በአግባቡ እየተወጣን ነው ያሉት ሼህ ኑረዲን፣ የኡለማ አንድነት ሰነድን በማገባደድ ወደ ሥራ ለማስገባት በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልፀዋል።

ምርጫውንም ለማከናወን በርካታ መሟላት የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉ የተናገሩት ሼህ ኑረዲን፣ ‹‹እንደ አገር የሙስሊሙ ቁጥር ብዙ ነው። ይህንን ሰፊ ማኅበረሰብ የሚመራ አካል መምረጥ በጥንቃቄ የሚታይ ጉዳይ በመሆኑ በአፋጣኝ ሦስቱን ዋና ዋና ሥራዎች በመጨረስ ምርጫውን ከሕዝብ ጋር በመወያየት ለማድረግ የሽግግር መጅሊሱ ዝግጅቱን እያካሄደ ነው›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ምርጫውን በአጭር ጊዜ ለማድረግ አሁን ያለው መጅሊስ ከፍተኛ ቁርጠኝነት አለው ያሉት ሼሁ፣ መጅሊሱ ባስቀመጠው እቅድ መሰረት ከኹለት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ምርጫውን ለማከናወን አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል።

በቀጣይ የሚመረጠው መጅሊስ የኡለማዎች ኅብረት የበላይነት ያለው ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል የተባለ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ የሚረዳ እንዲሁም ሰላምን እና አንድነት ማስፈን የሚችል ምክር ቤት እንደሚሆን ይጠበቃል። ከምሁራን፣ ከወጣቶች እንዲሁም ሴቶች የሚካተቱበት ይህ ኅብረት የሙስሊሙን ችግር የሚፈቱ አባላት ይኖሩታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተገልጿል።

በተያያዘም የሽግግር መጅሊሱ በሞጣ ከተማ በመስጊዶች ላይ የተከሰተውን ጥቃት የሚያጣራ ዘጠኝ አባላት ያሉት ኮሜቴ አቋቁሞ እየሠራ እንደሚገኝ ባሳለፈነው ሳምንት ሐሙስ ታኅሳስ 23/2012 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይፋ አድርጓል። ኮሚቴው በቦታው ላይ የተፈፀመው ጥቃት በከተማው የፀጥታ ኃይሎች ጭምር የተደገፈ እንዲሁም ሙስሊሞች ላይ ብቻ ያተኮረ እንደነበር አስታውቋል።

በሞጣ ከተማ አራት መስጊዶች ወድመዋል ያለው ኮሚቴው፣ ከ167 በላይ የሙስሊም ሱቆች በእሳት መቃጠላቸውን ጠቅሶ የወደመው ንብረት ከ 450 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመትም በማከል መንግሥት የካሳ ክፍያ እንዲፈፅም ጠይቋል።

ለረጅም ዓመታት ሕዝበ ሙስሊሙ ሲያነሳው የቆየው ነፃ የሆነ መጅሊስ ምርጫ በተለይም ከ 2003 ጀምሮ የተለያዩ ተቃውሞዎችን አስተናግዷል። ይህም ‹ድምጻችን ይሰማ ›የተባለውን ንቅናቄ እንዲፈጠር ምክንያት የሆነ ነበር። የምርጫውን ጉዳይ ጨምሮ ሌሎች ጥያቄዎችን እንዲፈቱ የተወከሉትን መፍትሄ አፋላላጊዎችን ለእስርም የዳረገ እንቅስቃሴ ነበር።

ቅጽ 2 ቁጥር 61 ታኅሣሥ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here