በ11 ቢሊዮን ብር ወጪ አራት የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጀመረ

0
470

በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በ2012 በጀት ዓመት ከ 11 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ አራት የመስኖ ግድብ እና ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጀመረ።

ግንባታዎቹ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች የሚከናወኑ ሲሆን፣ ከ 33 ሺሕ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብሏል። ግንባታቸውም ከሦስት ዓመታት በኋላ የሚጠናቀቅ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ሦስቱ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ሲሆን፣ በጨልጨል ወንዝ ላይ የሚገነባው የጨልጨል ግድብ እና መስኖ ልማት ፕሮጀክት፣ የወልመል መስኖ ልማት እና ጉደር ፋቶ ሲሆኑ የላይኛው ርብ መስኖ ፕሮጀክት በአማራ ክልል የሚከናወን ነው።

የጨልጨል ግድብ 46 ሜትር ከፍታ እና 685 ሜትር እርዝማኔ ሲኖረው ከ 50 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ሜትር ውሃ የመያዝ አቅም አለው። ከ 1 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር መሬት ላይ ውሃው እንደሚተኛ እና 4 ሺሕ 500 ሄክታር መሬት በማልማት 9 ሺሕ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

ሌላው በኦሮሚያ ክልል የሚገነባው የጉደር ፋቶ ግድብ ሲሆን፣ 57 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ሜትር ውሃ በመያዝ 4 ሺሕ 900 ሄክታር መሬትን የማልማት አቅም አለው። ይህም 10 ሺሕ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል። የመልምል የወንዝ መቀልበሻ በኦሮሚያ ክልል በደሎ መና ወረዳ እና በሃረና ወረዳ የሚገኘውን የመልምል ጎዳ ወንዝን አቅጣጫ በማስቀየር 1 ሺሕ 100 ሄክታር መሬትን ለማልማት ያስችላል። የፕሮጀክቱም ግንባታ 34 ኪሎ ሜትር የውሃ መተላለፊያ ቦይ ግንባታ ሲኖረው፣ በ ሦስት ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖሩ ከ 22 ሺሕ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 61 ታኅሣሥ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here