የኅብረት ሥራ ዩኒየኖች የፋይናንስ መረጃ ቋት ሊዘረጋ ነው

0
443

የፌዴራል ኅብረት ሥራ ዩኒየን ኤጀንሲ በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ለሚገኙ የኅብረት ሥራ ዩኒየኖች የሚዘረጋ የመረጃ ቋት አዘጋጅቶ መተግበር ጀመረ።
የማኅበራቱን አሰራር ከማዘመን ባለፈ ከ 19 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያንቀሳቅሱትን እነዚህን ማኅበራት ገቢ የሚያስተዳድር እና ለመንግሥትም የሚላኩ ሪፖርቶችን የሚያሰናዳ እንደሆነም ተገልጿል። የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አያልሰዉ ወርቅነህ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ስርዓቱን ለመገንባት 20 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ የሃርድ ዌር እና የሶፍት ዌር ግንባታ ተካሂዷል።

በመላው አገሪቱ ካሉት 128 ሺሕ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ውስጥ፣ የመጀመሪያ ሙከራዉን የሚከናወነዉ በአምስት ክልሎች በተመረጡ 50 ኅብረት ሥራ ማኅበራት ላይ ነው። ዘመናዊ በሆነዉ የዲጂታል የመረጃ አያያዝ ስርአት የማኅበሩን ገቢ እና ወጪ ከመቆጣጠር ባሻገርም፣ የፋይናንስ ደኅንነትን የሚያስጠብቅ መሆኑንም አያልሰው ተናግረዋል።

በመላው አገሪቱ ከአምስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አባለት ያሏቸው ዩኒየኖቹ፣ 42 በመቶ ያክል ሴት አባላት ያሉት ሲሆን በኢትዮጵያ ላለው የቁጠባ እድገት አራት በመቶ ገደማ አበርክተዋል። ከዚህ ውስጥ 78 በመቶው ማኅበራት በገጠር አካባቢ የተመሰረቱ ሲሆኑ፣ ሌሎች ቀሪ 22 ፐርሰንቱ ደግሞ በከተማ የተሰማሩ ናቸዉ።

በመረጃ ስርዓቱ ተጠቃሚ የሚሆኑ ወረዳዎች በኦሮሚያ 15፣ በአማራ 14፣ በደቡብ 11፣ በትግራይ ዘጠኝ እና በቤንሻንጉል ጉምዝ አንድ ወረዳ ላይ እንደሚሆን የፌዴራል ኅብረት ሥራ ማኅበር ኤጀንሲ መረጃ ያመላክታል።

ቅጽ 2 ቁጥር 62 ጥር 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here