ዳግም ምጽአት ‘ሐለዋ ወያነ-ወ-ፈዳያን’!

0
770

ሕወሓት በመቀሌ ከተማ ታኅሳስ 18 እና 19 እንዲሁም ታኅሳስ 25 እና 26/ 2012 ያደረጋቸውን አስቸኳይ ስብሰባዎች ላይ ተነሱ የተባሉ ጉዳዮችን መሠረት አድርገው የተነሱት ግዛቸው አበበ፣ ከስብሰባው ቀድሞ በትግራይ ተወላጆች መካከል የነበረውን ስሜት ቃኝተዋል። እንዲሁም ከስብሰባው በኋላ በቀረበው የሕወሓት የአቋም መግለጫና ውሳኔ ላይ “በኹለቱ መንግሥታት መካከል” የሚል ሐረግ መጠቀሱ፣ በሕወሐት መንግሥት እና የብልጽግና ፓርቲ መንግሥት ወይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥትና በክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል መንግሥት መካከል ግብግብ መጀመሩን ያመላክታል ይላሉ። ከዚህም አልፎ ‹‹ሕወሐት ወደዚያ የበረሀ ሥራው ይመለስ ይሆን?›› የሚለውን ጥያቄ በማንሳት፤ ስለ ‹‹ሐለዋ ወያነ›› ጥቂት ብለዋል።

‘ተአምር የሠራው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ተክዶ በደባል አመለካከት ተተክቷል… ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ተጥሶ በክልሎች ጣልቃ መግባት ተጀምሯል… ሕዝብ የመረጠውና መንግሥት ያደረገው ኢሕአዴግ በሕገ-ወጡ የዐቢይ ቡድን ሥልጣኑን ተነጥቋል (መፈንቅለ መንግሥት ተደርጎበታል)…. አገራችንን በብዙ መስኮች ወደ ፊት እንድትገሰግስ ያደረጋት የኢሕአዴግ መስመር ስለተተወ የኋሊት ጉዞ ተጀምሯል… ለውጭ ኃይሎች ያጎበደደው የዐቢይ ቡድን የአገሩቱን ህልውና አደጋ ላይ ጥሎታል…’ እነዚህን በርካታ መሰል እሮሮዎች በሕወሐት መደበኛ ስብሰባ እንዲሁም ታኅሣሥ 18-19 ሕወሐት ጠርቶት በተካሄደው የመቀሌው ሕዝባዊ ኮንፈረንስ እና ታኅሣሥ 25-26/2012 በተካሄደው የሕወሐት አስቸኳይ ስብሰባ ተስተጋብተዋል።

‘በእርግጥ ኢሕአዴግና አገዛዙ እንዲህ ነበሩ እንዴ?’ የሚል ጥያቄ ለማንሳት ግድ የሚል እሮሮ ነው። በእነዚህ ስብሰባዎች ሕወሐት የራሱን ጉዳይ ከመወሰንና የራሱን አቋም ከመግለጽ አልፎ በሌሎች ፓርቲዎች መጻዒ ዕድል ላይ ‘እኔ ልወስንላቸው ሲገባ ለምን በራሳቸው መንገድ ነጎዱ!’ የሚል ዓይነት አዝማሚያ በማሳየቱና በዚህም መከፋቱንና ቁጣውን በመግለጹ ትዝብት ላይ የወደቀበት አጋጣሚ ሆኗል።

በእነዚሁ ስብሰባዎች በተለይም በታኅሣሥ ወር በተካሄዱት ኹለት ስብሰባዎች፣ ሕወሐት ‘ኢትዮጵያ’ ብሎ የመጥራት ‹አላርጂው› እንዳልለቀቀው ያጋለጡ አጋጣሚዎች ናቸው። ሆኖም ‘…የአገራችንን ህልውና ለማስቀጠል ማንኛውንም ሕገ መንግሥታዊ የትግል ስልት እንጠቀማለን፣ የአገራችንን ፌደራላዊ ስርዓት ለማስቀጠል ከሌሎች ወገኖች ጋር በፎረም፣ በኅብረት፣ በውህደት፣ በግንባር ወዘተ አብረን እንሠራለን… ሕወሐት የአገራችንን መጻዒ ዕድል በሚመለከት በሕገ-መንግስቱና በፌደራላዊ ስርዓቱ ስር ሆኖ መታገሉን ይቀጥላል…..’ የሚሉ ግንባሩ ለዚች አገር ተቆርቋሪና አሳቢ ስለሆነ ብልጽግና ፓርቲን የሚቃወም ሆኖ ወይም መስሎ የታየባቸው ናቸው።

እነዚህ ‘አገራችን’ በሚሉ ቃል የተከሸኑ አባባሎች፣ በእርግጥ ሕወሐት ለኢትዮጵያ ሕልውናና አንድነት መቆርቆሩን ያሳያሉን? ወይስ ከ2010 መገባደጃ ወራት ሕወሐት በባለሥልጣናቱ፣ በደጋፊዎቹ፣ በጀሌ ምሁራኑና በተቃዋሚ ነን ባይ ተለጣፊዎቹ አማካኝነት፤ ትግራይን ስለ መገንጠል ባነሳ ቁጥር ቅሬታውን ከማሰማት ያልቦዘነውን የትግራይ ሕዝብ ለመደለል ሙከራ እያደረገ ነው? ለዚህ ጥያቄ መልሱን የሚሰጠው ጊዜ ነው።

የመቀሌዎቹ ሕዝባዊ ኮንፈረንስና የሕወሐት አስቸኳይ ስብሰባ ሌላም ገጽታ ነበራቸው። ዛቻ፣ ማስፈራሪያ፣ ማስደንበሪያና ማስጠንቀቂያዎች በገፍ ተዥጎድጉደውባቸዋል። ‘….የውስጥ ጠላቶች፣ ተላላኪዎች፣ ባንዳዎች፣ የዐቢይ ቡድን ወኪሎች፣ የሕዝብ አንድነት የሚንዱ፣ በገንዘብ የተገዙ የትግራይ ሕዝብ ጠላቶች…’ ተብለው በተፈረጁ የትግራይ ተወላጆች ላይ ሰይፍ መመዘዙ በከፍተኛ በጩኸት ተነግሯል። ‘በእሳት እየተጫወታችሁ ነው…እረፉ ወይም እናሳርፋችኋለን’ የሚል ዓይነት ማስፈራሪያ መሰንዘሩ ለብዙዎች በትግራይ ሰማይ ጥቁር የስጋት ደመና እያንዣበበበት ሆኖ እንዲሰማቸው እድርጓል። ይህ ማስፈራሪያና ማስጠንቀቂያ ሕወሐት በበረኸኛ ዘመኑ አስፈሪ ጥቃቶችን በትግራይ ተወላጆች ላይ ሲፈጽምባቸውና ሲያስፈጽምባቸው የነበሩትን ‹ሐለዋ ወያነ›ን እና ‹ፈዳይኖች›ን ወደ አእምሮ የሚያመጣ ጉዳይ ነው። ‘ሐለዋ ወያነ’ ና ‘ፈዳይኖች’ ዳግመኛ የትግራይ ተወላጆችን ሊተራምሱ ነውን?

ስለ ‘ሐለዋ ወያነ’፣ ስለ ‘ፈዳይኖች’ እና ተግባሮቻውን አሳምሮ የሚያውቅ ሰው፤ ይህን ጥያቄ ሲመለከት ስጋቱ ከሚገባው በላይ ለማጋነን ከመፈለግ ወይም ሕወሐትን በቀድሞ (የበረሀ) ሥራው ለመወንጀል በማሰብ ወይም በትግራይ ሕዝብ ላይ ሽብር በመንዛት ሕዝብን ለማነሳሳት በማሴር የተሰነዘረ ጥያቄ አድርጎ ሊወስደው ይችላል። ነገር ግን የሕወሐት የወቅቱ አካሄድ በክልሉ መሪ ደረጃ ማስፈራሪያዎችና ዛቻወች በአደባባይ የሚሰነዘሩበት ነውና ‘የሐለዋ ወያነ’ እና የፈዳይኖች ድብቅ ጥቃት ዳግም ወደ ሥራ መመለስ ፈጽሞ ሊሆኑ የማይችሉ ነገሮች ናቸው ብሎ ድምዳሜ ላይ መድረስ ሞኝነት ሊሆን ይችላል።

እንደ ሕወሐት ድምዳሜ፣ ብልጽግና የሚባል ፓርቲ መወለዱ በትግራይ ሕዝብ ላይ፣ በፌደራላዊ ስርዓቱ ላይ፣ በሕገ-መንግሥቱ ላይ፣ በዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ላይ፣ በትግራይ ጥቅም ላይ፣ በትግራይ ሕዝብ ሰላምና አንድነት ላይ፣ በትግራይ ክልል ህልውና ላይ አደጋ የጋረጠ ፍጻሜ ነው። ሕወሓት ሕጋዊና የኃይል ትግል እንደሚጠብቀው ጠቆም አድርጎ በዐቢይ አሕመድ ቡድን የተላኩ ባላቸው የትግራይ ተወላጆችና ቡድኖች ላይ የመረረ እርምጃ ሊወስድ መዘጋጀቱን በይፋ አሳውቋል። ማስጠንቀቂያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አያድንህም የሚል አንደምታ ያለው ነው።

ሕወሐት በአስቸኳይ ስብሰባው ያወጣው የአቋም መግለጫና ወሳኔ “በኹለቱ መንግሥታት መካከል” የሚል ሐረግን ስለተጠቀመ፣ በሕወሐት መንግሥት እና የብልጽግና ፓርቲ መንግሥት ወይም በዐቢይ መንግሥትና በደብረጽዮን መንግሥት መካከል ግብግብ መጀመሩን፣ በግርግሩ መካከል ሊጨፈለቁ የሚችሉ የትግራይ ተወላጆች ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል። ይህ የሕወሐት ዛቻ፣ በትግራይ ተወላጆች ውስጥ ስጋትም ማጫሩ እንዳለ ሆኖ ዛቻው ያስደሰታቸው ግለሰቦችና ቡድኖችም አልታጡም። ይህ ስጋትና ደስታ ደግሞ በትግራይ ተወላጁ/ተወላጇ በኢትዮጵያዊነት ማመንና አለማመን ላይ የተመረኮዘ ነው።

ለመሆኑ ‘ሐለዋ ወያነ’ ምንድን ነው? ‘ፈዳይኖችስ’ እነ ማን ናቸው?
‘ሐለዋ ወያነ’ ማለት ሕወሐት ከሕዝባዊ ግንባሩ ‘ሀለዋ ሰውራ’ ኮርጆ አደራጅቶት የነበረው ልዩ የሥራ ክፍል ነው። ‘ሐለዋ ወያነ’ እና ‘ሐለዋ ሰውራ’ በብርጌድ ደረጃ የተደራጁ የሥራ ከፍሎች ሲሆኑ፣ የእነዚህ ብርጌዶች ዋና ዓላማ የእናት ድርጅቶቻቸውን ህልውናና አንድነት ከውስጣዊ ስጋቶች መጠበቅ ነው። ‘ሐለዋ’ የሚለው የትግርኛ ቃል ‘ጥበቃ’ የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ‘ወያነ’ ማለት ደግሞ ‘አብዮት’ እንደማለት ነው።

ለምሳሌ ‘ኢሕአዴግ’ (የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር) በትግርኛ ሲጠራ ‘ኢህወዴግ’ (ናይ ኢትዮጵያ ሕዝቢ ወያናይ ዴሞክራሲያዊ ግንባር) ይሆናል። እዚህ ውስጥ ‘አብዮታዊ’ የሚለው ቃል ‘ወያናይ’ በሚል ነው የተተካው። በሻእቢያው ‘ሐለዋ ሰውራ’ ውስጥ ያለው ‘ሰውራ’ የሚለው ቃልም ከአረብኛ የተወሰደ ሆኖ ‘አብዮት’ እንደ ማለት ነው ነው። ስለዚህ ‘ሐለዋ ወያነ’ እና ‘ሀለዋ ሰውራ’ ማለት ተመሳሳይና ‘የአብዮት ዘብ’ ወይም ‘የአብዮቱ ጠባቂ’ የሚል ትርጉም ያላቸው ናቸው። በዚህ ላይ ‘ከሁሉም በላይ አብዮቱ!’ የሚለውን የአብዮተኞች መፈክር ስንጨምርበት፣ በአብዮቱ ላይ ለመጣ ምህረት የለም ወደሚለው ድምዳሜ ያደርሰናል። ታሪካቸውም እንደዚያው ነው የነበረው።

‘ፈዳይን’ የሚለውን ቃል ‘ተበቃይ’ ወይም ‘ደም መላሽ’ በሚሉት የአማርኛ ቃላት መተካት ይቻላል። ሕወሐትና ሻእቢያ በበረሀ በነበሩበት ወቅት ቅጣት የሚሉት እርምጃ ይወስዱ የነበረው በበረሀ እስር ቤቶቻቸው ውስጥ ብቻ አልነበረም። ወደ ከተማ እያሰረጉ በሚያስገቧቸው ወይም በከተሞች ውስጥ ሰላማዊ ሰው አስመስለው በሚያሰማሯቸው ‘ፈዳይን’ በሚባሉ ነፍሰ ገዳዮች አማካኝነትም ጭምር ነው። ፈዳይኖች በከተሞች፣ በመንደሮችና በገጠር አካባቢዎችም ጭምር ግድያዎችን አካሂደዋል። ግንባሮቹን በሚቃወሙ የትግራይና የኤርትራ ተወላጆች ላይ ሲወሰድ የነበረው እርምጃ በኹለቱ ሕዝቦች ዘንድ የሚረሳ አይደለም።

የሻእቢያና የሕወሐት ፈዳይኖች ለግንባሮቹ ገንዘብ አላዋጣም ያሉ የኤርትራ የትግራይ ተወላጆችን፣ ግንባሮቹ በከተሞች ውስጥ ለሚያካሂዷቸው ሥራዎች ለመመልመል ፈቃደኛ ያልሆኑ ወጣቶችን፣ በልዩ ሙያቸው ግንባሮቹን ያገለግሉ ዘንድ ወደ በረሀ እንዲወርዱ ጥሪ ሲደረግላቸው ፈቃደኛ የማይሆኑ ባለሙያዎችን (ሐኪሞች፣ መካኒኮች ወዘተ…)፣ ደርግን ይደግፋሉ የሚባሉ ዘፋኞችንና ባለሀብቶችን ወዘተ… ይገድሉ ነበር።

ግንባሮቹ በደርግ/ኢሠፓ መዋቅሮች ውስጥ በመለመሏቸው ወይም ሆነ ብለው በሰገሰጓቸው አባላቶቻቸው አማካኝነት፣ ጠላቶቻቸውን ብቻ ሳይሆን የማይደግፏቸውን ገለልተኛ የክፍለ አገራቱ ተወላጆችን በሐሰት ውንጀላ ወደ ደርግ እስር ቤት እንዲገቡ ከማድረግ ጀምሮ፣ በደርግ ጥይት እንዲረሸኑ በማድረግ ጭምር ሕዝብ ላይ የጭካኔ ዘመቻ ያካሄዱ ድርጅቶች ናቸው። ሕወሐት በኹለቱ የመቀሌ ስብሰባወች ፍጻሜ ላይ እንዲነበቡ ያደረጋቸው የአቋም መግለጫወችና ውሳኔዎችም፣ የሕወሐትን ተቃዋሚ ቡድኖች ብቻ ሳይሆን ሕወሐትን በማይደግፉ የትግራይ ተወላጆች የስጋት ደመና እንዲያንዣብብ ምክንያት መሆናቸው ገሀድ የወጣ ጉዳይ ነው።

የእነዚህ የሥራ ክፍሎች ዋና ትኩረት፣ በራሳቸው በግንባሮቹ ውስጥ እና እንወክለዋልን በሚሉት ሕዝብ መካከል የሚነሱ ጸረ-ግንባር (ጸረ-አብዮት) እንቅስቃሴዎችን እየተከታተሉ መደምሰስ ነው። ‘ሐለዋ ወያነ’ እና ‘ሐለዋ ሰውራ’ ግፍና ሰቆቃ የሚፈጸምባቸው እስር ቤቶችን የሚያስተዳድሩ ሲሆን፣ በእነዚህ እስር ቤቶች የሚታጎሩትም ሆነ ግፍና ሰቆቃ የሚፈጸምባቸው ታጋዮች ወይም ግንባሮቹን በጽኑ የሚቃወሙ ወይም ለግንባሮቹ ጸር ናቸው በሚል የተጠረጠሩ የክፍለ አገራቱ (የኤርትራና የትግራይ) ተወላጆች ናቸው። የእነዚህ ብርጌዶች እጅ አጭርና በኤርትራና በትግራይ በረሀዎች ውስጥ ብቻ የተወሰነ አልነበረም።

ስለ ‘ሐለዋ ወያነ’ ብዙ የማይወራው ለምንድን ነው?
በየጊዜው የኤርትራውን ሻእቢያን (የአሁኑን ሕዝባዊ ግንባርን) እየተቃወሙ፣ ጥለውት የወጡ የግንባሩ ባለ ሥልጣናት፣ ታጋዮች፣ የ‘ሐለዋ ሰውራን’ ጡንቻ የቀመሱ የኤርትራ ተወላጆች፣ ስለ ‘ሐለዋ ሰውራ’ የሚያውቁትን ቅንጥብጣቢ ዕውቀትና መረጃ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስለሚያጋልጡ፣ እነዚህን መረጃዎች በመገጣጠም ስለ ሻእቢያው ‘ሐለዋ ሰውራ’ ትልቅ ምስል መፍጠር ተችሏል። ሻእቢያን ተቃውመው ከወጡት ሰዎች መካከል፣ ‘የሐለዋ ሰውራን’ ምንነት ሲመለከቱ ቅሬታ ተፈጥሮባቸው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ግንባሩን ጥለው የወጡ ኃላፊዎችና ተራ ታጋዮች ስለሚገኙና እነሱም ለሕዝባቸው ሲሉ ጉዱ እንዲጋለጥ ስላደረጉ፣ ከሞላ ጎደል ‘የሐለዋ ሰውራ’ ታሪክ በጥሩ ደረጃ ይፋ ሆኗል ማለት ይቻላል።

ይህ ደግሞ ብዙ የኤርትራ ጸሐፍትና ጋዜጠኞች ‘የሐለዋ ሰውራ’ን የግፍ ታሪክ ለኤርትራ ሕዝብና ስለ ኤርትራ ትግል ታሪክ ለማወቅ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች ሰፊ መረጃ እንዲያቀርቡ አስችሏቸዋል። በአገራችንም ‘ቅርምት- የኢትዮጵያ ዕጣ በዘመነ ግንባር’ የተባለው መጽሐፍ ስለ ‘ሐለዋ ሰውራ’ ታሪክ አንድ ሙሉ ምዕራፍ ለንባብ አብቅቷል።

በተቃራኒው የሕወሐቱ ‘ሐለዋ ወያነ’ ታሪክ እንደተቀበረና እንደተዳፈነ እየኖረ ነው ማለት ይቻላል። ይህን መሰል የግፍ ሥራ ሲሠራ፣ ነገሮች ሁሉ በከፍተኛ ምስጢር መያዛቸው የግድ ሲሆን፣ አንዳንዴ በቦታው ተመድበው በርካታ ምስጢሮች የማወቅ ዕድል ያገኙ የተራ ታጋዮችና የዝቅተኛ ኃላፊዎች በሕይወት መኖር ለዋናዎቹ አለቆቻቸው ከፍተኛ ስጋት የሚፈጥር ነውና፣ ስንቶቹ ይሆን በሕይወት ያሉት ብሎ መጠየቅ የግድ ይላል። ስለዚህ ምስጢሩን ማጋለጥ የሚችሉት የሕወሐት ከፍተኛ አለቆች ናቸው። የሕወሐት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የነበሩትና በተለያዩ ጊዜያት ግንባሩን በመቃወምም ሆነ በማኩረፍ ጥለው የወጡ ግለስቦች ግን ይህን ሲደርጉ አይታዩም። ለምን?

አቶ ስዬ አብርሃ፣ አቶ ገብሩ አስራት፣ ወ/ሮ አረጋሽ፣ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፣ አቶ አሰገደ ገብረሥላሴ ወዘተ… ግንባሩን ጥለው ከወጡ በኋላ የሕወሐትን ማንነት የሚያጋልጥ ያሉትን መጽሐፍ ያሳተሙ ቢሆንም፣ ‘የሐለዋ ወያነ’ን የግፍ ሥራ ለማጋለጥ አንዳችም ሙከራ አላደረጉም። እነዚህ ግለሰቦችና ሌሎች ጓዶቻው ሕወሐትን የሚቃወም እንቅስቃሴ ቢጀምሩም፣ የእነሱ ተከታይ፣ አባልና ደጋፊ መሆን ለሚገባው የትግራይ ሕዝብ ሕወሐት በበረኸኛ ዘመኑ በትግራይ ተወላጆች ላይ የፈጸመውን ግፍ በዝርዝር አለማጋለጣቸው ሕወሐትን ለትግራይ ሕዝብ ስለሚቆረቆር ብቻ የሚቃወሙት ሳያስመስላቸው አልቀረም። ለዚህም ሊሆን ይችላል፣ ብዙ ቆራጥ ተከታይ ማግኘት የሚሳናቸው። ከእነዚህ ሰዎች አንዳንዶቹ ሕወሐት በመሀል አገር ችግር በገጠመው ቁጥር፣ ከሕወሐት ጋር ለመሞዳሞድ ቅርብና ችኩል ሲሆኑም አይተናልና ለትግራይ ሕዝብ ያላቸው ተቆርቋሪነት እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ማሳያ ሊሆን ይችላል።

የሐለዋ ወያነን ጉድ ስለማጋለጥ ሲወሳ፣ አንድ ሊረሱ የማይገባቸው ሰው መኖራቸውን ግን መካድ አይቻልም። እሳቸውም የቀድሞው የሕወሐት መካከለኛ ባለሥልጣንና በአሁኑ ሰዓት በስደት አውስትራሊያ የሚኖሩት ገብረመድኅን አረአያ ናቸው። ገብረመድኅን የሕወሐትን ጸረ-ኢትዮጵያዊነት ያለማቋረጥ በማጋለጥ የሚታወቁ ሰው ናቸው። ሕወሐት ጸረ-ኢትዮጵያዊነቱን ለማራመድ ዋነኛ መሣሪያ ያደረገውም ጸረ-አማራነትንና ጸረ-ኦርቶዶክስነት መሆኑንም ከነምክንያቱ ዘርዝረው በማስረዳት ይታወቃሉ። አቶ ገብረመድህን ገና የደርግ ስርዓት ሳይወድቅ ጀምረው ሲያጋልጡት የነበረው የሕወሐት ሴራና ተንኮል፣ የደርግን ውድቀት ተከትሎ ተራ በተራ በኢትዮጵያና በሕዝቦቿ ላይ ሲፈጸም ታይቷል። በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ገብረመድኅን የሕወሐት የመጨረሸ ግብ ነው እያሉ ሲያጋልጡት የነበረው ነገር ሊተገበር ዳርዳር ሲባል በገሀድ እየታየ ነው። ኢትዮጵያን አዳክሞ፣ ከፋፍሎ ማፈራረስና ታላቋን የትግራይ ሪፐብሊክ መመስረት።

ገብረመድህን ትኩረት ሰጥተው ካጋለጧቸው የሕወሐት አሳፋሪና አስከፊ ጉዶች መካከል፣ ሐውዜን ከተማን ለቦምብ ድብደባ የማመቻትና መልሶ ደርግን የመወንጀል ሴራ ቅንብር፣ ራሳቸው ገብረመድኅን ሱዳናዊ እህል አቅራቢ ነጋዴ መስለው የተሳተፉበት በተራበው የትግራይ ሕዝብ ሥም ዶላር የመሰብሰብ ሴራ፣ በሕወሐት ውስጥ የጾታዊ ግንኙነት መፈጸም በተከለከለበት ጊዜ በዚህ ጉዳይ ገብተው በተገኙ ታጋዮች (በተለይ በሴቶች) ላይ ሲፈጸም የነበረው በሰቆቃ የተሞላ ቅጣት፣ የጾታ ግንኙነት ከመፈጸም አልፈው የተገናኟቸው ሴቶች ሲያረግዙ ወንጀላቸውን ለመደበቅ ሴቶቹ ከወለዱ በኋላ ደብዛቸው እንዲጠፋ ስላደረጉ የበርካታ የሕወሐት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጉድ፣ ሕወሐት በ1980 አጋማሽ መላ ትግራይን ከተቆጣጠረ በኋላ ‘ትግራይን ነጻ አውጥተናልና ውጊያው ይቁም’ በሚሉ በርካታ ታጋዮች ላይ ስለወሰደው አረመኔያዊ እርምጃ ወዘተ… ተጠቃሽ ናቸው።

እኚህ የሕወሐትን እውነተኛ ማንነትና ምንነት ለማጋለጥ ቆርጠው የተነሱ ሰው ስለ ሐለዋ ወያነም የሚያውቁትን ያህል ተናግረዋል (አጋልጠዋል)። ኢሳትን ጭምሮ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ደጋግመው ቀርበው ከተናገሯቸው በርካታ አስደንጋጭ ታሪኮች መካከል አንዱ ይህን ይመስላል። እርግበ የተባለች አክሱማዊት ወጣት እህቷን አስከትላ ሕወሐትን ተቀላቅላ ለመታገል ወደ በረሀ ወረደች። ብዙም ሳይቆይ ከሕወሐት ከፍተኛ ባለሥልጣናት አንዱ (አሁንም ትግራይ ውስጥ በሥራ ላይ ነው) ዐይኑን አሳረፈባትና የግንባሩን መመሪያ ችላ ብሎ አስገድዶ ደፈራት። ይህ ባለሥልጣን በዚህ በቃኝ ሳይል የደረሰባትን በደል ያካፈለቻትን እህቷንም በተመሳሳይ አስነወራት። በመጨረሻም ባለሥልጣኑ ጉዱን ለመደበቅ በማሰብ ብቻ እህትማማቾቹን ለደርግ ሊሰልሉ እንደተላኩ አድርጎ በመወንጀል ወደ ሐለዋ ወያነ እስር ቤት እንዲወርዱ አድርጎ አስረሽኗቸዋል።

በእርግጥ የሕወሐት/ኢሕአዴግ ስርዓት ባለፉት 27 ዓመታት በመላ ኢትዮጵያ እስር ቤቶች፣ በአደባባዮች፣ በጎዳናዎች፣ በቤተ-እምነት አጸዶች፣ በዩንቨርሲቲ ግቢዎች ወዘተ… የፈለገውን ግፍና ሰቆቃ ሲፈጽምና ሲያስፈጽም የኖረ ስርዓት ነውና ‘ሕወሐት ወደዚያ የበረሀ ሥራው ይመለስ ይሆን?’ ብሎ መጠየቅ አስቀድሞ ስለሚታወቅ ጉዳይ አጉል መመራመር ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ጥያቄውን ማንሳት የግድ የሚለው የዚህ የግፍ ሥራ ብቸኛ ዒላማ የሚሆነው የትግራይ ሕዝብ ብቻ ስለሆነ፣ ሕወሐት ያደርገዋል ወይ ብሎ ለመነጋገር የግድ ስለሆነ ነው።

ይህን የሐለዋ ወያነ ታሪክ ለማውሳትና ተያያዦቹን ጥያቄዎች ማንሳት ግድ የሚል ጉዳይ አለን? አዎ አለ!!… ይህ ዕብደት ሊጀመር እንደሚችል የሚጠቁም ፍንጭስ አለ? አዎ… አለ!!
ታኅሳስ 18-19 እንዲሁም 25-26/ 2012 መቀሌ ላይ የተካሄዱትን ኹለት ስብሰባዎች የትግራይ ሕዝብ የተከታተለበት ጉጉትና ስጋት በመሀል አገር የሚኖረው ሕዝብ ሊገምተው ከሚችለው በላይ ነበር። የታኅሳስ 18 እና 19 ስብሰባ እስኪጀመር በሕዝቡ ዘንድ መነጋገሪያ ከነበሩ በርካታ ጉዳዮች ውስጥ ኹለቱ ትኩረትን የሚስቡ ነበሩ። ‹‹ሕወሐት ይፈረሳል ወይስ አይፈርስም›› የሚለው ውዝግብ አንደኛው ሲሆን፣ ሌላው ‹‹ሕወሐት ካልፈረሰና በዲፋክቶ መንግሥትነት ይሁን በሌላ ዘዴ ከመሀል አገር ፖለቲካ ራሱን የሚያርቅ ከሆነ፣ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች የተከማቸው የሕወሐት ሀብትና ንብረት ዕጣ ምን ይሆናል›› የሚል ነበረ። የሀብትና ንብረትን ጉዳይ የሚመለከተው ውዝግብ የማይንቀሳቀስ ሀብትና ንብረት አዲስ አበባና በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ባከማቹ የሕወሐት ሰዎችና ሀብት ንብረታቸውን በትግራይ ባከማቹ የሕወሐት ሰዎች መካከልም ውዝግብ መኖሩ እየተሰማ ሰንብቷል።

ታኅሳስ 25 እና 26/2012 የተካሄደውን ስብሰባ ተከትሎ ደግሞ፣ በእርግጥም ሕወሐትና ባለ ጸጋዎቹ ስለ ሀብታቸው በጣም መጨነቃቸውን የሚያጋልጥ ዓረፍተ ነገር በአቋም መግለጫው ውስጥ መካተቱ ይፋ ሆኗል። በዚህ ስብሰባ ሕወሐት ለራሱ፣ ለአውራዎቹ፣ ለባለጸጋ ደጋፊዎቹ ሃብት ሲጨነቅ ለሕዝብ ነጸናትና መብት ግን ግድ የለሽና ‘ከራስ በላይ ነፋስ’ ባይ መሆኑን አረጋግጧል።
ታኅሳስ 25 እና 26 የተካሄደውን ስብሰባ ተከትሎ ስጋትና ስሜታዊነት የሞላበት ተስፋ የመቀሌ ብሎም የትግራይ መንታ ገጽታዎች መሆናቸው ይሰማል። ሕወሐቶች በክልሉ ለሚኖሩ ተቃዋሚዎቻቸው የሰነዘሩት ማስጠንቀቂያ የሕወሐትን አካሄድ ባልወደዱ የትግራይ ተወላጆች ላይም ሰይፍ ሊመዘዝ እንደሚችል የሚጠቁም ዛቻ ተደርጎ ተወስዷል።

ሕወሐት ከበረሀ ወጥቶ ከተሜ ባለሥልጣን መሆኑን ተከትሎም፣ በመላ ኢትዮጵያ የነበረው ጸባይ ትግራይ ውስጥም ተመሳሳይ ነው የነበረው። አንጋፋ የሕወሐት ባለሥልጣናት ከሥልጣን ውጭ ሆነው ወይም ሕወሐት ገዥ ፓርቲ መሆኑ ከቀረ ከፍርድ ነጸ ሆነው መኖር ይችላሉን? ዛቻውና ‹በሥልጣናችን አትምጡ› የሚለው ማስፈራሪያ በዚህ ጉዳይ ላይ የተመረኮዘ ነው። ይህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ 6 አገራት ለሥልጠና የተላከ ጦር አለ፣ በየመንገዱ ማንቁርት እያነቀ እንዳይጥል እፈራለሁ እያሉ ለማስፈራራት ከሞከሩበት ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ነው። ይህና ሌላው ጉዳይ ተዳምሮ በተለየ መንገድ ብርቱካን ሚደቅሳ ለመሳሰሉ የሕዝብን አደራ የተሸከሙ ሰዎች እንቅልፍ ሊነሳ የሚገባው አደገኛ አካሄድ ነው።

የምክትል ፕሬዘደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤልን ንግግር እውነተኛና ዕድሜ ጠገብ የክልሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጽኑ ሲኮንኑት፣ ሣልሳይ ወያነን የመሳሰሉ በተለጣፊነት የሚታሙ አዲስ መጤ ድርጅቶች ግን ማስጠንቀቂያውና ዛቻው እነማንን እንደሚመለከት በግልጽ መነገር ነበረበት እያሉ ‘እኛ ሰላም ነን’ በሚል ዓይነት ትምክህት እንደተቀበሉት ዶቸቨለ (በጀርመን ድምጽ) ላይ ሰምተናል። በሣልሳይ ወያኔዎች አመለካከት፣ ይህ ማስጠንቀቂያ እነ አብርሃ ደስታንና ቡድናቸውን፣ እነ አረጋዊ በርሄን (ዶ/ር) እና ቡድናቸውን ብቻ የሚመለከት ተደርጎ ተወስዷል።

ነገር ግን ሕወሐት በመሪው (በደብረጽዮን ገብረሚካኤል) አማካኝነት በከፍተኛ ቁጣና በኃያል ጩኸት ያስጠነቀቀውና የዛተባቸው እዚህ ግባ የሚባል ብዛት ያለው ደጋፊ የሌላቸውን እነ አረናን ነውን? ለዚህ ጥያቄ ‘አዎ!’ የሚል መልስ መስጠት አደገኛ መዘናጋትን የሚሳይ ነው።

ሕወሐት ራሱን ሥልጣን ላይ ለማቆየት ሲል፣ በሥልጣኑና ትግራይ ውስጥ በመሸገበት የምቾት ምሽጉ ላይ የሚያነጣጥርን ማንኛውንም ጠላት፣ የትግራይ ሕዝብን ጨምሮ ከመምታት ወደ ኋላ እንደማይል ማስጠንቀቂያ እየሰጠ መሆኑን መገመት ተገቢ ነው። ማስጠንቀቂያው ፖሊስን፣ ፍርድ ቤትን፣ ሕግንና ሰብዓዊ መብትን ችላ ብሎ ሊካሄድ የሚችል ስውር እርምጃን፣ ሐሰተኛ ውንጀላን፣ ቀሳፊ አደጋዎችን ወዘተ…. ሊያስከትል ይችላል።
ግዛቸው አበበ gizachewabe@gmail.com

ቅጽ 2 ቁጥር 62 ጥር 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here