ማክሰኞ መስከረም 14 ቀን 2017 (አዲስ ማለዳ) ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ፤ ጄነራል ጻድቃን ገ/ትንሳኤን ስልጣን ለመጠቅለል በማቀድና የቆየ ቂም ለመወጣትአስቧል ሲሉ ከሰዋል።
ከቀናት በፊት በመቀለ በተካሄደ አንድ ስብሰባ ላይ ደብረጽዮን ህወሓትን ለማጥፋት፣ ስልጣን ለመጠቅለል የሚንቀሳቀሱ ተብለው የተገለፁ አመራሮችን በስም እየተጠቀሱ ወቀሳ ሲሰነዘርባቸው ተሰምቷል።
በዚሁ መድረክ ደብረፅዮን (ዶ/ር) ፥ የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት የሆኑት ጀነራል ፃድቃን ገብረ ትንሳኤን፥ ስልጣን ለመጠቅለል በማቀድ፣ የቆየ ቂም በመወጣት እና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች በማንሳት እንዲሁም ከዚህ በፊት በይፋ ያልተሰሙ መረጃዎች በመግለፅ ሲተቹ ተደምጠዋል።
በንግግራቸው እርሳቸው የሚመሩትን ህወሓት ሰላም የማይፈልግ አድርጎ የማቅረብ የተሳሳተ ፍረጃ ከትግራይ ባለስልጣናት በኩል እየቀረበበት መሆኑን ገልጸው ” ይህ ውሸት ነው ” በማለት አጣጥለዋል።
ደብረፅዮን አክለውም ” ለምሳሌ በደቡባዊ ዞን በተደረገ መድረክ ጀነራል ጻድቃን እኛ ሰላም እንፈልጋለን፣ እነሱ የሚሹት ጦርነት ነው ሲል ሰምታችሁታል።
“በጦርነቱ ወቅት ደሴ ተሻግረን ሰሜን ሸዋ ስንጠጋ፥ ድርድር ያስፈልጋል ወይ ሲባል እኔ አዎን ያስፈልጋል ነው ያልኩት። በሰላም ሊፈታ ስለሚገባው።” እሱ ግን ከማን ጋር ነው የምንደራደረው፣ ውጊያው አልቋል ሲል የነበረ ነው ሲሉም ጄኔራሉን ተችተዋል ።



