ኢትዮጵያ አዲስ የካንሰር ሕክምና መሣሪያ ልታስገባ ነው

0
438

ከዓለማቀፉ የአውቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ በተገኘ ድጋፍ ‹ሳይክሎትሮን› የተሰኘ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነ የካንሰር ምርመራ እንዲሁም ሕክምና ለማድረግ የሚያስችል መሣሪያ ለመግዛት ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ተገለፀ።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው መሣሪያው፣ የካንሰር ምርመራን ለማከናወን ከማገዙም በላይ የካንሰር ሕክምና እንዲሁም የኩላሊት ንቅለ ተከላ ያደረጉ ግለሰቦችን የጤና ሁኔታ ለመከታተል እንደሚረዳ ተገልጿል።
አሁን ወደ አገር ውስጥ የሚገባው መሣሪያ እስካሁን የካንሰር ምርመራ እና ሕክመና ከሚደረግበት መንገድ በተለየ ሁኔታ ምርመራ እና ሕክመና ለማድረግ የሚያስችል ነው። ለመሣሪያው በሚገነባው ቤተ ሙከራም የመሣሪያውን የምርመራ ውጤት መሰረት ባደረገ መልኩ መድኃኒቶችን ለማምረት የሚያስችሉ ሌሎች የሕክምና መሣሪያዎች በቀጣይ ሦስት ዓመታት ወደ አገር ውስጥ እንደሚገቡ ታውቋል።
ግዢው በአውቶሚክ ኃይል ኤጀንሲው በሚደረግ የገንዘብ ድጋፍ የሚፈፀም ነው። ከገንዘብ ድጋፉ በተጨማሪ የማማከር እንዲሁም ለባለሙያዎች ሥልጠና ለመስጠት የሚያስችል ስምምነት ላይ መደረሱን እና ለነዚህ ሥራዎችም በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ድጋፍ እንደሚገኝ በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰርና የካንሰር ስፔሻሊስት አብዱ አደም (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ በመገንባት ላይ በሚገኘው ባለ ዘጠኝ ወለል የካንሰር ማእከልን ዓለም አቀፉ የኒዩክሌር ድርጅት አባላት ጉብኝት በማድረግ፣ ኢትዮጵያ ካንሰርን ለመከለከል የምታደርገውን ጥረት ለማገዝ ኤጀንሲው መሣሪያውን ለመግዛት የሚያስችለውን የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱ ታውቋል።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በመገንባት ላይ ያለው የካንሰር ማእከል 250 አልጋዎች ይኖሩታል ያሉት አብዱ፣ ‹‹የኒዩክለር ሕክምና ማእከል እና የራሱ ቤተ ሙከራ ይኖረዋል። አሁን ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት መሣሪያዎች ካንሰርን በጨረር ሕክምና እና በ ኬሞቴራፒ እንዲሁም ራዲዮፋርማሎጂ ለማከም የሚረዱ መድኃኒቶችን ለማምረት የሚያስችል አቅም ይኖረዋል›› ብለዋል።
ሌሎች የካንሰር ማእከላት ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በጅማ፣ መቀሌ፣ ጎንደር፣ ሀሮማያ፣ ሐዋሳ በመገንባት ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ማእከላት በአዲስ አባባ በሚገኙ ሕክምናው በሚሰጥባቸው እንደ ጥቁር አንበሳ እና ጳውሎስ ባሉ ሆስፒታሎች የሚስተዋለውን ከፍተኛ ወረፋ ለማስቀረት ይረዳል ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ ቤተ ሙከራ የሚመረቱ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቁ የጨረር ሕክምናን ለማድረግ የሚረዱ መድኃኒቶች፣ ወደ ክልሎች የማሰራጨት ሐሳብ መኖሩን የገለፁት አብድ፣ ብዙ ታማሚዎች ይህንን ሕክምና ፍለጋ ወደ ተለያዩ አገራት በመሄድ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ የካንሰር ታማሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መምጣቱ ተገልጿል። በየዓመቱም 65 ሺሕ ሰዎች እንደ አዲስ በካንሰር የሚጠቁ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥም 40 ሺሕ የሚሆኑት ለሞት ይዳረጋሉ።
አዲሱ መሣሪያም በየዓመቱ እንደ አዲስ በበሽታው ከሚያዙ 65 ሺሕ ሰዎች መካከል ከ50 እስከ 60 በመቶ የሚሆኑትን ለማከም እንደሚረዳ ይጠበቃል።
የጨረር እና የኬሞቴራፒ ሕክምና ጥቁር አንበሳን ጨምሮ በጳውሎስ ሆስፒታል በጊዜያዊነት በመሰጠት ላይ ይገኛል። ካለው ከፍተኛ ወረፋ አንፃር አንድ ታማሚ በተለይም የጨረር ሕክምና ለማግኘት ከሦስት ወራት እስከ አንድ ዓመት ሊጠብቅ እንደሚችል፣ ይህም በሽታወን ወደ ከፋ ደረጃ እንደሚያደርሰው አብዱ ገልፀዋል።
አሁን ወደ ማእከሉ የሚመጣውም መሣሪያ ከካንሰር በሽታ በተጨማሪ እንደ ኩላሊት፣ የአጥንት የመቅኔ ካንሰር ምርመራ እና የልብ ምርመራዎችን በቀላሉ ለማድረግ ያስችላል የተባለ ሲሆን፣ የታማሚዎችን የካንሰር ደረጃ በቀላሉ ለመለየት ይረዳል።
በአደጉት አገራትም ጭምር በስፋት እንደማይገኝ፣ በአፍሪካም ጥቂት አገራት ብቻ የመሣሪያው ባለቤት መሆናቸው ተገልጿል። ይህንንም መሰረት በማድረግ ኢትዮጵያን የሕክመና ቱሪዝም መዳረሻ በማድረግ ታማሚዎች ለሕክምና ወደ ውጪ አገራት ሲጓዙ የሚያወጡትን ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ በአገር ውስጥ ለማስቀረት ያግዛል ተብሏል።
በዘርፉ የሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረት እንደሚስተዋል የገለፁት አብዱ፣ በካንሰር ላይ ስፔሻላይዝ ያደረጉ ሐኪሞች ቁጥር ከ 13 አይበልጥም። ይህንን ችግር ለማቃለል ጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል በካንሰር ሕክምና 37 ስፔሻሊስቶችን እያስተማረ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የጨረር ሕክምና መሣሪያ ባለሙያዎች በኩልም ከፍተኛ እጥረት እንዳለ ገልፀው፣ ‹‹አሁን ያሉት ባለሙያዎች አምስት አይሞሉም። የካንሰር ሕክምና ባለሙያ ብቻውን ሕክምናውን መስጠት አይችልም። ለአንድ መሣሪያ ኹለት ባለሙያ ያስፈልግ ነበር።›› ያሉ ሲሆን፣ አሁን ከኤጀንሲው ጋር የተደረገው ስምምነት እነዚህን ባለሙያዎች ማሠልጠንንም የሚጨምር ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የጡት ካንሰር በስርጭቱ ከፍተኛውን ደረጃ የሚይዝ ሲሆን፣ በአገራችን በካንሰር ከተጠቁ ሰዎች መካከል 33 በመቶ የሚሆነውን ይሸፍናል። የማሕጸን በር ካንሰር፣ በወንዶች በኩል ደግሞ ፕሮስቴት ካንሰር ከፍተኛ የታማሚ ቁጥር ሲኖራቸው፣ የሳንምባ ካንሰርን ጨምሮ በኢትዮጵያ በስፋት የሚስተዋሉ የካንሰር አይነቶች ናቸው።

ቅጽ 2 ቁጥር 62 ጥር 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here