ለኹለት ዓመት በሶማሌ ክልል የቆየው የህዳሴ ግድብ ዋንጫ ለአዲስ አበባ ተሰጠ

0
534

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ ከሶማሌ ክልል ተከስተው በነበሩ የጸጥታ ችግሮች የታሰበውን ያህል መንቀሳቀስ አለመቻሉን ተከትሎ ክልሉ ዋንጫውን ለአዲስ አበባ ማስረከቡ ተገለፀ።
ዋንጫው ባለፉት ኹለት ዓመታት በሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ስር የቆየ ሲሆን፣ በክልሉ በነበሩ ተደጋጋሚ ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች የታሰበውን ያህል መንቀሳቀስ ባለመቻሉ ኅዳር 29/2012 የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በተከበረበት ወቅት የሶማሌ ክልል ለአዲስ አበባ ከተማ ማስረከቡ ተገልጿል።
ዋንጫው በክልሎች በአማካይ አንድ ዓመት ለሚሆን ጊዜ እንደሚቆይ የተገለፀ ሲሆን፣ ዋንጫው በሶማሌ ክልል በነበረበት ወቅት በተፈጠሩ ግጭቶች እና የአመራር ለውጦች ምክንያት ትኩረት ተነፍጎት ለኹለት ዓመታት ያለ እንቅስቃሴ መቆየቱ ታውቋል።
የክልሉ መንግሥት ባለፉት ጊዜያት የተፈጠሩ አለመረጋጋቶችን አና የፀጥታ ችግሮችን መፍታት ላይ ትኩረቱን በማድረጉ፣ ዋንጫው በክልሉ በሚፈለገው ደረጃ ያልተንቀሳቀሰ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ ክልሉ ዋንጫውን ለአዲስ አባባ ከተማ ማስረከቡን የህዳሴው ግድብ ብሔራዊ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኃይሉ አብርሃም ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።
በአዲስ አባባ ከተማም ለአንድ ዓመት የሚቆየው ዋንጫው ለግድቡ ግንባታ ማጠናከሪያ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ ኹነቶች ለማሰናዳት እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ከአዲስ አባባ ከተማ የህዳሴው ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ለማወቅ ተችሏል።
ከእነዚህም መካካል በከተማዋ የሚደረገው ታላቁ ሩጫ ከ ብሔራዊ ማስተባባሪያ ጽሕፈት ቤቱ ጋር በጋራ የሚደረግ በመሆኑ፣ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ገቢ ለማሰባሰብ እቅድ መኖሩን እንዲሁም የተለያዩ የቦንድ ሳምንቶችን ለማከናወን እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን አዲስ አባባ ከተማ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዘውዱ ገብረኪዳን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ባለፉት ኹለት ዓመታት ስለ ግድቡ ሁኔታ ለኅብረተሰቡ ሲተላለፍ የነበረው መረጃ የተሳሳተ እና ግልጽነት የጎደለው ነበር ያሉት ኃላፊዋ፣ ኅብረተሰቡ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሲንከባከበው እዚህ ያደረሰው በመሆኑ ሲተላለፉ በነበሩ የተዛቡ መረጃዎች ቅሬታ ውስጥ ገብቷል ብለዋል። አክለውም በመጪው አንድ ዓመት የተረጋገጠ እና ወቅቱን የጠበቀ መረጃ ለኅብረተሰቡ ለማድረስ ይሠራል ብለዋል።
በአዲስ አባባ በሚገኙ ክፍለ ከተሞች እና ተቋማት ዋንጫው ተራውን ጠብቆ እንዲዞር ይደረጋል ያሉት ዘውዱ፣ በርካታ የገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል። አሁን ላይ ግን ምን ያህል ገንዘብ ለመሰብሰብ እንደሚቻል መናገር አይቻልም ሲሉም ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።
በ 2008 በከተማዋ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተጀምሮ የነበረው ‹‹የህዳሴው አፀድ›› የተሰኘ በተማሪዎች የሚከናወን የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።
ዋንጫው በክልሉ በቆየባቸው ጊዜያት አምስት ሺሕ ሰዎች የተሳተፉበት የጎዳና ላይ ሩጫ መደረጉን የገለፁት የህዳሴው ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኃይሉ፣ ክልሉ ዋንጫውን ባስረከበበት ወቅት 18 ሚሊዮን ብር ገቢ ማድረጉንም አስታውቀዋል።
ኃይሉ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት፣ እስከ አሁን ሕዝቡን በማስተባባር ለግድቡ ከ13 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል። በ2012 የመጀመሪያ አምስት ወራትም 265 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን፣ ከባለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው ብለዋል።
ለዚህም በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የታየው ቦንድ ግዢ መቀዛቀዝ እና በክልሎች ያለው አለመረጋጋት ኅብረተሰቡ ለግድቡ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ አነስተኛ እንዲሆን ያደረገው ሲሆን፣ የክልልች ተሳትፎ ከምን ጊዜውም በላይ መቀዛቀዙን ብሔራዊ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል።
አዲስ ማለዳ የሱማሌ ክልል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊን በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር በስልክ ተደጋጋሚ ሙከራ ብታደርግም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 62 ጥር 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here