ግዙፍ የቻይና የጨርቃ ጨርቅ አምራች በኢትዮጵያ ሥራ ሊጀምር ነው

0
592

‹ሸንቴክስ› የተሰኘ ግዙፉ የቻይና የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት አምራች ድርጅት በቦሌ ለሚ ኹለት ኢንዱስትሪያል ፓርክ ለማምረት የሚያስችለውን የኪራይ ውል መፈራረሙ ተገለፀ።
በቻይና ኹለተኛው ግዙፍ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት አምራች የሆነው ድርጅቱ፣ በኢትዮጵያ ከ 65 ሚሊዮን ዶላር በላይ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ መስማማቱን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገልጿል። በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በ10 ሄክታር መሬት ላይ ሼዶችን በራሱ ወጪ በመገንባት ወደ ሥራ ለመግባት መስማማቱን የኢንዱስትያል ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሌሊሴ ነሚ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የሼዶቹን ግንባታ እስከ ፈረንጆቹ 2020 መገባደጃ በማጠናቅቅ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለፁት ሌሊሴ፣ ለ 4 ሺሕ ሰዎች የሥራ እድል ለመፍጠር እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ መኮንን አበበ፣ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ ጥጥ ለማምረት የሚያስችል አቅም ስላላት ኢንቨስተሮች ጨርቃ ጨርቅን ከማምረት በተጨማሪ እንደ ጥጥ ያሉ የምርት ግብዓቶችን ማምረት ላይ እንዲሰማሩ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
እንደ ሻንጋይ ቴክስታይል ዲኮሬሽን ኮርፖሬሽን ያሉ ግዙፍ ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው፣ በወጪ እና ገቢ ምርቶች ላይ የሚስተዋለውን አለመመጣጠን የወጪ ንግዱን በጨርቃ ጨርቅ እና በአልባሳት በመደገፍ ያለውን ክፍተት በመጠኑም ቢሆን ለመቅረፍ ያስችላልም ተብሏል።
የውጪ አገራት አምራቾቹ በዘርፉ ያላቸውን ልምድ አገር ውስጥ ለማስቀረት እና በርካታ የሥራ እድሎችን ለመፍጠር እንደሚረዳ የተናገሩት መኮንን፣ ሸንቴክስ ወደ ማምረት ከገባ በኋላ ምን ያህል ምርቶችን ወደ ውጪ እንደሚልክ ከመናገር ተቆጥበዋል።
በቀላሉ ሠልጥኖ ወደ ሥራ መሰማራት የሚችል ሰፊ ወጣት ኃይል መኖሩ እንዲሁም ኢትዮጵያ በጨርቃ ጨርቅ እና የአልባሳት ምርቶችን ወደ አውሮፓ እና አሜሪካ ከቀረጥ ነፃ የምትልክባቸው አማራጮች መኖራቸው፣ በርካታ የውጪ አገራት አልሚዎች በኢትዮጵያ ለመሥራት ፍላጎት እንዲያሳዩ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
እንዲሁም በኢትዮጵያ ያለው የኤሌክትሪክ ክፍያ ዋጋ ከሌሎች አገራት ጋር ሲነፃፃር አነስተኛ መሆኑ የውጪ አገራት አልሚዎችን ለመሳብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ገልፀዋል። ሆኖም በኢንዱስትሪያል ፓርኮች ያለው የኤሌክትሪክ አቅርቦት ውስንነት እና መቆራርጥ፣ ፋብሪካዎቹ የሚጠበቅባቸውን ያህል እንዳያመርቱ ከማድረጉም በተጨማሪ ማሽነሪዎችን ለብልሽት በመዳረግ ላይ ነው። በተጨማሪም ያለው ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ እጥረት በዘርፉ ላይ ያሉ ችግሮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
እነዚህም ችግሮች ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም እያሳጡ ነው ያሉት መኮንን፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከመሰረተ ልማት ጋር የተያያዙ ድጋፎችን እንዲሁም የኢንዱስትሪያል ፓርኮችን ለአልሚዎች ምቹ ለማድረግ በመሠራት ላይ ነው ብለዋል።
በተጨማሪ አልሚዎች በኢንዱስትሪያል ፓርኮች ውስጥ ሁሉንም አገልግሎቶች በአንድ መስኮት የሚያገኙበትን እድል ለማመቻቸትም አሁንም ከውጪ አገራት ለሚመጡ ሠራተኞች የሥራ እና የመኖሪያ ፈቃድ እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሠራ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።
የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ በአገሪቱ ከሚገኙ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ውስጥ ቅድሚያ የተሰጠው ዘርፍ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያትም አገሪቱ እየለማ ያለ ሰፊ የተማረ ወጣት ጉልበት ያለባት መሆኑ፣ እንዲሁም በየ ክልሎች እየለሙ ያሉ ፓርኮች አልሚዎችን ለመሳብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሆነ ከኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
በኢትዮጵያም ከ 200 በላይ በጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ መካከለኛ እና ከፍተኛ ፋብሪካዎች ሲኖሩ፣ በውስጣቸውም ከ100 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 62 ጥር 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here