በቤኒሻንጉል እና በኦሮሚያ የቴሌኮም አገልግሎቶች በከፊል ተቋርጠዋል

0
763

በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች የቴሌኮም አገልግሎቶች እንደተቋረጡ የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ገለፁ።
በምሥራቅ እና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች እንዲሁም አሶሳ አዋሳኝ ዞኖች ላይ ያጋጠመው አለመረጋጋትና የጸጥታ መደፍረስ አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት የፋይናንስና ገንዘብ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አብዱላሂ ሶጃር ለሥራ ከአሶሳ ወደ ነቀምት በሚጓዙብት ጊዜ መገደላቸዉን ተከትሎ፣ በክልሉ በአሶሳና አካባቢው ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች ተከስተዋል።
ከእነዚህ ግጭቶች መከሰት በኋላም በአንዳንድ አካባቢዎች የኢንተርኔት አገልግሎት እንደተቋረጠ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ቢነሳ ተረፈ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ከሰሞኑ እነዚህ ከተሞች ከፍተኛ የጸጥታ ቀውስ ውስጥ መሆናቸው ይታወቃል ያሉት የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች፣ የሰላሙ ሁኔታ ከሚገባው በላይ አስጊ ደረጃ ከመድረሱም በላይ ከተማዋ አሁን ባለው ሁኔታ አልፎ አልፎ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ብዛት እየጨመረ እንደሆነም ገልጸዋል።
ከተማዋ ኮማንድ ፖስት ስር ነው የምትገኘው ያሉት ነዋሪዎቹ፣ ስጋት እና ፍርሃት ውስጥ እንዳሉ ተናግረዋል። ኮማንድ ፖስቱ ከሚገባው በላይ ቁጥጥር እያበዛ ነው፤ በዛም ምክንያት ሰው መውጣት እና መግባት አስፈሪ የሆነበት ደረጃ ላይ ነን ብለዋል ።
ነዋሪዎቹ እንደገለጹት፣ ከትላንት በስትያ በነቀምቴ ካቶሊክ በመባል የሚታወቀው የወጣቶች ሞተር እና የመኪና መለማመጃ ስፍራ አካባቢ ባሉ ወጣቶችና ግብረ ኃይሉ መካከል በተፈጠረ ግብግብ የሞት አደጋ መድረሱንም ጠቅሰዋል።
ነዋሪዎቹ እንዲህ ዓይነት ችግሮች ሲከሰቱ መንግሥት በአፋጣኝ ጣልቃ ገብቶ ካላረጋጋ በዞኑ ኢንተርኔት መቋረጡ ብሎም የቴሌኮም አገልግሎቱ መቋረጡ ከሚያስከትለው ስጋት በላይ፣ የትራንስፖርት እንቅስቃሴው መገታቱ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ከመገደቡም በላይ መረጃ አግኝተው ጥንቃቄ ለማድረግ እንደተቸገሩ ገልጸዋል።
ነቀምቴ ላይ ባንክን ጨምሮ የተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች እንደቀጠሉ ናቸው። ነገር ግን ምዕራብ ወለጋ፣ ደምቢ ዶሎ እና አሶሳን ጨምሮ የኢንተርኔት እና የስልክ አገልግሎት መቋረጡንና ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የምዕራብ ቀጠና ቴሌ በበኩሉ ለቀረበለት ቅሬታ ‹‹እኛ የምናውቀው ነገር የለም። የበላይ አካል ጠይቁ›› እንዳለ ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የኦሮምያ ክልል የሕዝብ ግንኙነቱ ቢነሳ እንደገለጹት፣ የቴሌኮም አገልግሎቱ መቋረጡን በማስመልከት የሚመለከታቸው አካላት በጉዳዩ ላይ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም እስከ አሁን ምንም አይነት መግለጫ አለመሰጠቱን ተናግረዋል።
ከተማዋ በኮማንድ ፖስት ቁጥጥር ስር በመሆኗ ምንም ነገር መግለጽ እንደማይቻል ተናግረው፣ ከጉዳዩን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው መከላከያ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንደሚሰጥ ይጠበቃል ብለዋል። በተጨማሪም በአካባቢው ላይ የትራንስፖርት መቋረጥ አለ የሚባለውን ቅሬታ እንደማያውቁ ገልጸው፤ የኢንተርኔት እና የቴሌኮም አገልግሎት መቋረጡን በተመለከተ ኢቲዮ ቴሌኮም መግለጫ የሚሰጥ መሆኑን አስታውቀዋል።
አዲስ ማለዳ ይህንን ዘገባ እስካጠናቀረችበት ጊዜ ድረስ ኢቲዮ ቴሌኮም በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት መግለጫ አልሰጠም።

ቅጽ 2 ቁጥር 62 ጥር 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here