ረቡዕ ኅዳር 25/2017 (አዲስ ማለዳ) በደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ህወሓት ትላንት ምሽት ባወጣዉ መግለጫ ለአቶ ጌታቸው ረዳ ሰጥቷቸው የነበረውን የፕሬዚዳንትነት ውክልና ማንሳቱን ገልጿል፡፡
በመሆኑም በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት እንዴት እና በማን እንደሚተኩ ከፌደራል መንግስት ጋር እየተወያየበት እንደሚገኝ አስታዉቋል።
“የህዝብ ውክልና የያዙ ምክር ቤቶችን እውቅና በመንሳት እና ውሳኔዎቻቸውን በመጣስ በዘፈቀደ አስተዳደራዊ እና ህዝባዊ ስራዎች እያደናቀፈ ይገኛል ” ሲልም “ቡደኑ” እያለ የገለጸውን በጌታቸው እረዳ የሚመራውን የጊዜያዊ አስተዳደር ኮንኗል፡፡
” ህዳር 23ቀን 2017 ዓ.ም በመቐለ ምክር ቤት የተሾሙትን አመራር በግርግር ከፅህፈት ቤቱ በማውጣት በራሱ ምስለኔ የአስተዳደሩ ፅህፈት ቤት ለመቆጣጠር መክሯል ” ብሏል።
እንዲሁም ‘’የህዝብ እና የመንግስት ከፍተኛ መገለጫ የሆነውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመጣስ በህዝብ ላይ አምባገነንነት ለመጫን በሙሉ አቅሙ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል’’ ሲልም ወንጅሏል፡፡
በመጨረሻም” ህገ-ወጥ ሙከራው ከግለሰባዊ አምባገነንነት የሚነሳ ነው ” ያለው በደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ህወሓት ፤ አባላቱ ትግላቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ በማስታውስ የፀጥታ እና የፍትህ አካላት ህጋዊ ተጠያቂነት ህግ እና ስርዓት እንዲያስከብሩ በማለት አሳስበዋል።



