የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገቢን ለማሳደግና ወጪን ለመቀነስ የሚያስችል የማማከር ሥራ ለማከናወን ኤ ኤፍ ሜርካዶስ እና ኤ ኤፍ ኮንሰልት (AF-Mercados and AF Counsult) ከተሰኙ የስፔን ኩባንያዎች ጋር ለአንድ ዓመት የሚቆይ የ68 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ስምምነት ተፈራረመ።ስምምነቱ የተካሄደው ከገቢ ማሳደግና ወጪ ቅነሳ ጋር በተያያዘ የእያንዳንዱ የሥራ ዘርፍ ያለበትን የአሰራር ሁኔታ ጥናት ለማጥናት፣ ጥናቱን መሰረት በማድርግ ገቢን እንዴት ማሳደግ እንደሚቻልና እንዴት ወጪን መቀነስ እንደሚገባ አዲስ የአሰራርና፣ ወደፊት ተቋሙ የሚመራባቸው የተለያዩ የአሰራር ማንዋሎችንና ፖሊሲዎችን ለማዘጋጀት ነው። አልፎም ሥልጠና ለመስጠት እንደሆነ ተገልጿል። ይህን ሥራ ኹለቱ ኩባንያዎች በጥምረት እንደሚያከናውኑትም ታውቋል።የፊርማ ስነ ስርዓቱን የኢትዮጵያ ኤልክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ኢንጅነር አብርሃም በላይ እና የኤ ኤፍ ሜርካዶስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚጉኤል ሄርናንዴዝ ተፈራርመዋል። ተቋሙ ገቢውን ለማሳደግ የተለያዩ አማራጮችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ሲሆን፣ ይህ ስምምነት የተቋሙን ገቢ ለማሳደግ እና ወጪውን ለመቀነስ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ተብሏል። ገንዘቡ ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር የሚሸፈን ሲሆን፣ የተቋሙን የገቢ እና ወጪ ስርኣትን በዘመናዊ መንገድ ለማስተካከል ጉልህ ሚና ይኖረዋል ተብሏል። ኩባንያዎቹ ከዚህ በፊት በምሥራቅ አፍሪካ በኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክቶች ላይ በማማከርና በሌሎች ጉዳዮች ላይ የበርካታ ዓመታት ልምድ እንዳላቸው ተገልጿል።ቅጽ 2 ቁጥር 63 ጥር 9 2012



