በዘንድሮው ጉዞ አድዋ 60 ተጓዦች ይሳተፋሉ ተባለ

0
948
የአድዋን ድል ለመዘከር የሚከናወነው ጉዞ አድዋ ሰባተኛ ዙር ተጓዦች ጥር 9/2012 ከአዲስ አበበ በመነሳት 1 ሺሕ 10 ኪሎ ሜትሮችን በእግራቸው ለማቆራረጥ መዘጋጀታቸው ተገለፀ። ለሰባተኛ ጊዜ በሚደረገው ጉዞ አድዋ፣ ከአዲስ አባባ ተነስቶ እስከ አድዋ ድረስ 1 ሺሕ 10 ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍን ሲሆን፣ 45 ቀናት የሚፈጀውን ጉዞ ለማከናወን 60 በጎ ፈቃደኛ ተጓዦች መዘጋጀታቸው ታውቋል። 55 ተጓዦች ከአዲስ አባባ ከተማ እንዲሁም ሌሎች ተጓዦች ከ ሐረር፣ ወለጋ እና አዳማ ጉዞውን ለማከናወን አዲስ አበባ ገብተዋል። በጉዞው በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ታሪካዊ ስፍራዎች ጉብኝት ይደረጋል። ተጓዦችን ለመመዝገብ ከታኅሳስ ሦስት ጀምሮ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀን ምዝገባ ሲከናወን እንደነበር እና በምዝገባውም ላይ በሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች እንደነበሩ የጉዘው አስተባባሪ ምስክር ከበደ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል። ተጓዦችንም ለመለየት ሙሉ የጤና ምርመራን ጨምሮ የታሪክ ዕውቀት በመለያነት በመጠቀም የመጓዝ ፍላጎት እና ቁርጠኝነት ያላቸው 120 ተለይተው የነበረ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ለመጓዝ ፍቃደኛ የሆኑ 60 ሰዎች ጉዞውን ለማከናወን ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸው ታውቋል። በእለቱም ትልቅ የሽኝት መረሃ ግብር በአዲስ አባባ መስተዳደር ግቢ ውስጥ የተዘጋጀ ሲሆን፣ የአርበኞች ማኅበር አባላት በከተማዋ የሚገኙ ቴአትር ቤቶች እና የተጓዥ ቤተሰቦች የሚገኙበት እንደሚሆን ይጠበቃል። ከመርሃ ግብሩ መጠናቀቅ በኋላም እስከ አድዋ ድልድይ ድረስ ተጓዦችን ለመሸኘት መርሃ ግብር መያዙን ምስክር ገልፀዋል። ጉዞ አድዋ በሕይወት ዘመን አንድ ጊዜ የሚደረግ ጉዞ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም የተጓዙ ወጣቶች በኪሎ ሜትሮች እና በአካባቢዎች በመከፋፋል መንገድ የማሳየት አገልግሎት እንደሚሰጡ ተገልጿል። ቅጽ 2 ቁጥር 63 ጥር 9 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here