የክፍያ መንገዶች የስድስት ወራት ገቢው በ61 ሚሊዮን ብር ጨመረ

0
733

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ የ2012 በጀት ዓመት በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት የሰበሰበው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ 61 ሚሊዮን ብር ጭማሪ በማሳየት 191 ሚሊዮን ብር ደረሰ።

በግማሽ ዓመት ውስጥ በአዲስ-አዳማ እና በድሬዳዋ-ደዋሌ የክፍያ መንገዶች በድምሩ አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ተሽከርካሪዎችን በማስተናገድ 181 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል። ቀሪ አስር ሚሊዮን ብር ገቢ ደግሞ የድሬ ዳዋ- ደዋሌ መንገድ በ ሰኔ 2011 ሥራ በመጀመሩ ምክንያት የተንከባለለ ገቢ መሆኑን ኢንተርፕራይዙ ገልጿል።

በተጨማሪም ከማስታወቂያ ቦታዎች ኪራይና ከተሽከርካሪ ማንሻና መጎተቻ አገልግሎቶች 10 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ኢንተርፕራይዙ ለአዲስ ማለዳ የላከው ሪፖርት ያሳያል። ለገቢው መጨመርም የድሬዳዋ-ደዋሌ መንገድ ወደ ሥራ መግባት እንደ ምክንያት የተገለፀ ሲሆን፣ በመንገዱ ላይ ያለው የክብደት ቁጥጥር ውጤታማነት አስተማማኝ አለመሆኑ እና ከክብደት በላይ ጭነው የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች በመንገዱ ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን የኢንተርፕራይዙ የሕዝብ ግንኙነት ባለሞያ ሮቤል አያሌው ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

በ2012 የበጀት ዓመት በፍጥነት መንገዶቹ ላይ የደረሱ አደጋዎች ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በግማሽ የቀነሰ ሲሆን፣ ለዚህም ዋናው ምክንያት በመንገዱ ክልል ውስጥ የ24 ሰዓት የመንገድ ላይ ቁጥጥር በማድረግ እና ለሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ተከታታይ ትምህርቶች በመስጠታቸው መሆኑን ሮቤል ጨምረው ተናግረዋል። በትራፊክ አደጋ የሚደርስ ሞትም ባለፈው ዓመት ከደረሰው 12 አደጋ በስድስት ዝቅ በማለት፣ ስድስት ሆኖም ተመዝግቧል።

ኢንተርፕራይዙ ለሌሎች የመንገድ ፕሮጀክቶች ትምህርት በሚሰጥ መልኩ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት አስጠብቆ ቀጥሏል ያሉት ሮቤል፣ በመንገዱ አካፋይ ላይ የሚገኙ ንብረቶችን በወቅቱ በመጠገን እና ከተተከሉ 27 ሺሕ ችግኞች ውስጥም ከ 85 በመቶ በላይ የሚሆነውን ማፅደቅ መቻሉን ኢንተርፕራይዙ አስታውቋል።

የጥገና አቅሙን በማሳደግ ከ10 ኪ.ሜ በላይ የመንገድ መስመሮችን በአገልግሎት እድሜ ማብቃት እና በአደጋ ምክንያት በመንገድ ንብረቶች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን በመጠገን የመንገዱ ምቾት እና ደኅንነት እንዳይጓደል መሥራቱንም ለአዲስ ማለዳ ገልጿል። የኢትዮጽያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ከ መስከረም 4/2007 ጀምሮ አገልገሎት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን፣ የቅድመ ክፍያ አገልገሎት መጀመሩንም ሮቤል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የትራፊክ ደንቦች መከበራቸውን የሚቆጣጠረው ኢንተርፕራይዙ፣ ከተቀመጠው የፍጥነት ገደብ በላይ የሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር እየሠራ መሆኑም ተጠቅሷል። የአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ በቻይናና በኢትዮጵያ የጋራ ትብብር በ11 ቢሊዮን ብር የተገነባና 80.4 ኪሎ ሜትር ርዝመት ሲኖረው፣ በአንድ ጊዜ ስድስት ትይዩ መኪናዎችን ማስተናገድ የሚችል ነው።

በተጨማሪም በግንባታ ላይ ለሚገኘው የሞጆ-ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ ኢንትርፕራይዙ የማማከር ሥራ እያከናወነ ሲሆን፣ ሲገባደድም ተቀብሎ የሚያስተዳድር ይሆናል። የሞጆ ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ በ13.5 ቢሊዮን ብር እየተገነባ ይገኛል። ርዝመቱም 202.5 ኪሎ ሜትር ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 63 ጥር 9 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here