በዩኒቨርሲቲዎች በግማሽ መንፈቅ ብቻ የ 12 ተማሪዎች ሕይወት አለፈ

0
452

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በ22 ዩኒቨርሲቲዎች ባካሄደው ምርመራና ቅኝት፣ በግማሽ ዓመት ውስጥ ብቻ የ 12 ተማሪዎች ሕይወት ማለፉን ይፋ አደረገ። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከአማራና ኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች የተወጣጣ ቡድን በማሳተፍ ባካሄደው ቅኝት መቱ፣ ወለጋ፣ ደምቢዶሎ እና ድሬድዋ ለመማር ማስተማር ምቹ ያልሆኑ እና ሰላም የሌላቸው በማለት ለይቷል። በቀይ ምድብ ውስጥ ከገቡት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የሆነው ድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ፣ ካሉት 650 የወንዶች ዶርም፣ 600 ገደማ የሚሆነው በሮቹ በግጭት ወቅት የተሰባበሩ በመሆናቸው ለተማሪዎች አስጊ እንደሆነም ተገልጿል።

በድሬድዋ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደውን ቅኝት የመሩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስቴር ድኤታ ጫላ ለሚ፣ ዩኒቨርሲቲው ለትምህርት የሚመች አካባቢ የሌለው እንደሆነ ይገልፃሉ።

ሐሮማያ፣ ባህር ዳር እና ወልዲያ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ በቢጫ ምድብ ውስጥ የተካተቱ ሲሆን፣ ይህም ያላቸው የፀጥታ ሁኔታ አንፃራዊ የሚባል እና ለመማር ማስተማር ሳንካ ያለባቸው ናቸው ተብሏል። በአጠቃላይም በፀጥታ ችግሮች ምክንያት ከ 35 ሺሕ ተማሪዎች በላይ ከትምህርት ገበታቸው ላይ እንደማይገኙ የተገለፀ ሲሆን፣ እነዚህንም ለመመለስ መሠራት እንደሚገባው ተገልጿል።

በመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት በተከሰቱ ግጭቶች ላይ ተሳትፎ ነበራቸው የተባሉ 640 ተማሪዎች ላይ ከአንድ ዓመት ትምህርት እገዳ እስከ ትምህርት ገበታ መሰናበት ድረስ የሚደርሱ የተለያዩ ቅጣቶች መተላለፋቸውንም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሕዘብ ግንኙነት ኀላፊ ደቻሳ ጉርሙ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በተጨማሪም በ41 መምህራን እና በ240 የአስተዳደር ሠራተኞች ላይ አስተዳደራዊ ቅጣቶች መጣላቸውንም አክለዋል።

የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማሪያም እንዳሉት፣ በተደረገው ቅኝት ከ 85 በመቶ በላይ የሚሆኑት ዩኒቨርሲቲዎች በተወሰዱ እርምጃዎች አማካኝነት የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማከናወን የሚቻልባቸው ሆነው መገኘታቸውን ተናግረዋል። ቡድኑ ባቀረበው የቅኝት ሪፖርትም፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የምክክር መድረኮችን በማዘጋጀት ለግጭቶቹ ምክንያት የሆኑ መሠረቶች ላይ መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል።

እንዲሁም የሀይማኖት ተቋማት ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ነፃ በመሆን ሰላም የሚያውኩ ተማሪዎችንም ማስተማር እንደሚገባቸው አስቀምጧል። የፍትህ አካላት ሚዛናዊ በመሆን ሕግን እንዲያስከብሩና መገናኛ ብዙኀንም ግጭት ቀስቃሽ ዘጋባዎችን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዙሪያ ከመሥራት እንዲቆጠቡም አሳስቧል።

የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ደቻሳ፣ በደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ በስጋት ምክንያት ቡድኑ መሥራት የሚገባውን ያህል እንዳልሠራ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ነገር ግን በአካባቢው ታግተዋል ስለተባሉ ተማሪዎች ጉዳይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የ35 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆን በአገሪቱ ያለው ሰላም አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን እና የአገሪቱን እድገት የሚጎዳ መሆኑን በዩንቨርሲቲ ግጭት አፈታት ላይ ዶክተሬታቸዉን እየሠሩ የሚገኙት መስፍን አዋዜ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ‹‹የ35 ሺሕ ተማሪዎች መፈናቀል ከጦርነት አሳንሰን የምናየዉ አይደለም›› ሲሉ አክለዋል። መስፍን ሲናገሩ የብሔር እና የሀይማኖት

ጉዳዮች በዩንቨርሲቲዎች ግጭት እንዲፈጠር የሚያደርጉ መሆናችዉን ገልፀዉ፤ በእነዚህ ጉዳዮች በዩንቨርሲቲዎች ግጭት እንዳይፈጠር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሠራት አለበት ይላሉ። መፍትሔውም እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል ጥናት ማድረግ፣ በየደረጃዉ አመርቂ ውይይቶችን ማከናወን እና በተማሪዎች ደኅንነት ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሆነና በመንግሥት ደረጃም ጥናቶችን አድርጎ ሕጋዊ ማዕቀፎችን ማስቀመጥና መተግበር እንደሚገባ መስፍን ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ማብራሪያ ገልፀዋል።

‹‹ወደ ፊትም ለግጭቶች መነሻ የሆኑ ነገሮችን በጥልቀት ማጥራትና እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል ጥናት መደረግ አለበት›› ሲሉ መስፍን ሐሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 63 ጥር 9 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here