የጫት ሱስና ማኅበራዊ ኪሳራው

0
982

ሱሰኝነት በወጣቱ ላይ በተለያየ መንገድ ከባድ ተጽእኖ ሲያሳድር ይስተዋላል። ይህም ከሥራ አጥነት ጋር ሲገናኝ ለአገር የበለጠ ጥፋት እንደሚያደርስ የሚያነሱት መርከቡ ምትኩ፤ ይልቁንም ማኅበራዊ ትስስሮችን፣ የመከባበርንም እሴት እየነጠቀን ነው ሲሉ ይሞግታሉ። ወጣቱን ወደዚህ መንገድ የሚገፉ ኢ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍሎችና አድሎአዊ የሆኑ አማራጭ እድሎች ከመሠረታው ሊስተካከሉ ይገባል በማለትም ሐሳባቸውን አካፍለዋል።

በፊት ጊዜ የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና ነበር የሚባለው.. ጊዜው ተቀይሮ የኢኮኖሚ ዋልታ – በርጫ በርጫ ከሆነ ግን ከራርሟል። አልሰማችሁም? ‹በርጫ ምንድነው?› ጫት። ከኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች ጥናት የሚቸከልበት፤ ከቀበሌ እስከ ቤተመንግሥት በሹመኞች ለአገር ዱዓ የሚደረግበት ትልቅ ሃብት ነው፤ በርጫ ማለት። ይኸው ለአከፋፋዮች በመኪና፣ ለተጠቃሚዎች በሞተር ሳይክል ፈጥኖ ከተፍ የሚል የትራንስፖርትም ሆነ የአቅርቦት ችግር የሌለበት የአገራችን ተወዳጅ ቅጠል ከሆነም ቆይቷል። ከማሳው በተቆረጠ በሰዓታት ጊዜ ውስጥ በአውሮፕላን ሽው ብሎ ዱባይም ለንደንም ደርሶ ፓውንድ የሚያስዝቀን አረንጓዴ ወርቃችን እንደሆነም የሚታወቅ ሃቅ ነው።

ወዳጆቼ! ግን ይሄ ጫትና ሽሻ የሚባል ነገር እንዴት ሙሉ አገራችንን እየተቆጣጠራት እንደሆነ ተገንዝባችኋል። በምሥራቁ የአገራችን ክፍል ብቻ ይዘወተር የነበረው የጫት መቃም ልምድ በሚገርም ፍጥነት አዲስ አበባን ሙሉ በሙሉ አጥለቅልቆ ጫት መቃም እንደ ነውር ይታይ በነበረባቸው የሰሜኑ የኢትዮጵያ ከተሞች ሳይቀር በፋሽን መልክ የመዛመቱን ችግርስ ልብ ብላችኋል? አዲስ አበባንማ ተውት፤ ከዳቦ ቤቶች በላይ የጫት ቤቶች ቁጥር እንደሚበልጥ ልብ ብሎ የታዘበ የሚያውቀው እውነት ነው። ከጫት ቤቶች ጀርባ ካሉት ማስቃሚያ ቤቶች ጋር ማለቴ ነው። ከሁሉም ደግሞ የሚገርመኝ፤ አሁን አሁን እየተለመደ የመጣው ከጫት ቤቶች ጀርባ ብቻ ሳይሆን ከምሽት ጭፈራ ቤቶች ጀርባ ጫት ማስቃሚያና ሽሻ ማስጨሻ ቤቶች ፋሽን እየሆኑ የመምጣታቸው ነገር ነው፡፡ ገብታችሁ እኮ ጫቱንም ሽሻውንም ሌላውንም ሌላውንም ብላችሁ ነው ወደ ዋናው ሳሎን ባር፤ ወደ መጠጥ ቤቱ የምትመለሱት፡፡

እንጂ እንደገቡ ጠርሙስ የለም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም እንዲሁ በፉክክር መልኩ የተጀመረው የማስቃምና የማስጨስ ጉዳይ በተራ መጠጥ ቤቶች ሳይቀር እየተለመደም መጥቷል። ግን ስለዚህ ስለ ሱሳሱስ ካነሳን አይቀር … አይ! ይሄ እንኳን ቀልድ ነው ካላላችሁኝ…እዚሁ አገራችን ውስጥ የሆነ አንድ እውነተኛ ታሪክ ልንገራችሁ። አንድ አስረኛ ክፍል የሚያስተምር አጫሽ መምህር ነው። እያስተማረ እያለ በመሃል ማጨስ ይፈልግና ከክፍል ይወጣል። ከዚያ ሲጋራ አውጥቶ ሊለኩስ ሲል ከኪሱ ክብሪት ያጣል። ከዚያም ምናልባት ክብሪት የያዘ ተማሪ ካለ ብሎ ወደ ክፍሉ ይመለስና ‹‹ክብሪት የያዘ ተማሪ አለ እንዴ?›› ይላቸዋል፤ ተማሪዎቹን። በዚህ ጊዜ ከአንዱ ተማሪ ውጭ ሁሉም እጃቸውን ያወጣሉ።

መምህሩም በመደናገጥ የሚለው ጠፍቶበት ያንን እጁን ያላወጣውን ተማሪ ‹‹ቆይ አንተስ ለምንድነው እጅህን ያላወጣኸው?›› ይለዋል። ተማሪውም መልሶ ‹‹አይ! ቲቸር እኔ ላይተር ነው የያዝኩት ብዬ ነው›› ብሎት እርፍ አለ፤ አሉ። የክፍሉ ተማሪም፣ መምህርም አጫሽ። ይህ ነው እንግዲህ አገራችን ያለችበት ደረጃ። ግን እንደዚህ ዓይነት አጓጉል ሱስ ውስጥ ወጣቱ በስፋት እየተዘፈቀ የወደፊት አገር ተረካቢ ትውልድ እየተበላሸ ያለው በምን ምክንያት ነው? ለምንስ ነው ወጣቱ ጫት እየቃመና ስለ ባህር ማዶ ኳስና መዝናኛ እያወራ፣ ራሱን አፍዝዞና አደንዝዞ የሚውለው? የቀረው የመረረውስ አገር ለቅቆ የሚሰደደው በአገሩ ምን አጥቶ ነው? ብሎ የሚጠይቅ የለም።

ማኅበረሰቡም መንግሥትም ይህንን እያዩ ዝም ብለዋል። ነገሩ እነሱ ዝም ካላሉ በየከተማው ያሉ የተወሰኑ ኤፍ ኤም ራድዮኖችና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ስለ ኳስና ስለ አሉባልታ ሲያወሩለት የሚውሉት አድማጭ ከየት ያገኛሉ ብላችሁ ነው። እዚህ ላይ ግን እኔም እንደ ግለሰብ በተለይ ዝምታውን በተመለከተ መንግሥትን በጣም መታዝቤን ልጠቅስ እወዳለሁ። ይህን በዝምታ ማለፍ እንደ መፍቀድ ይቆጠራልና፤ በዚህ ዓይነት ሌሎች ከባድ ናቸው የሚባሉ የሃሺሽ ዓይነቶችም በተመሳሳይ ሊስተናገዱ ይገባል የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። ‹‹አዎ! ጫት ደግሞ ሰው ፈሪ ነው የሚያደርገው።›› የሚሉ አይጠፉም። ግን የሱስ ትንሽና ትልቅ የለውም።

እንደ ሜክሲኮ እፅ ነጋዴዎች የተደራጀ የማፍያ ቡድን ተፈጥሮ ለሥልጣኔ ያሰጋኛል ብሎ ፈርቶ ካልሆነ በቀር፤ በተለይ ወጣቱ በጫት ብቻ እንኳ ሕይወቱ ተጎሳቁሎ እየታየ ነው። እነዚህ ‹ትልልቅ› የሚባሉት የሃሽሽ ዓይነቶች ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት በአብዛኛው በዲፕሎማት ሻንጣ ነው ይባላል። ደግሞ ‹ይባላል› ነው ያልኩት እንጂ ‹ነው› አላልኩም፤ ከመንግሥት ጋር እንዳታጣሉኝ። ለሚያስተውል ሰው እየሆነ ያለው ሁሉ በጣም ያሳዝናል። አንድ ወጣት ነገሩን ሁሉ ትቶ ዞር ዞር ብሎ ገንዘብ ለቃቅሞ፣ ያገኘውን ሸቃቅሎ ጫት ይዞ ቁጭ የሚለው መለወጥና ማደግ፣ ራሱንም ማሻሻል ሳይፈልግ ቀርቶ አይመስለኝም። ይልቁንም መኖር ደክሞት፣ ተስፋ ቆርጦ ነው። በመንግሥትም በማኅበረሰቡም ተስፋ ባለማግኘቱ ነው። የነገ ሕይወቱ ዕደል ዕጣ ፈንታው ሁሉ በባለሃብቶችና በባለ ሥልጣናት በሚወሰንለት ምስኪን ማኅበረሰብ ውስጥ የተፈጠረ፣ አማራጩን ያጣ በደ-መነፍስ የሚኖር የተገፋ ትውልድ ስለሆነ ነው።

ስለዚህ ጉዳይ ለማሰብና ለመጻፍ ያነሣሣኝ ነገር በማኅበረሰባችን ውስጥ ከመቻቻል ከመከባበርና ከአብሮነት እሴቶቻችን ሙሉ በሙሉ ያፈነገጠ ሱሰኛና ወለፈንዲ ትውልድ እየተፈጠረ በመሆኑ ነው። ይህንን ሐሳቤን የሚያጠናክርልኝን አንድ ትዝብቴንም ላጫውታችሁ። አዲስ አበባ ጦር ኃይሎች አካባቢ ነው። ሱቅ በር ላይ የስልክ ካርድ ልገዛ ቆሜአለሁ። እዚያው አካባቢ ከሱቁ በረንዳ ኹለት ወጣት ልጆች ተቀምጠው ጫት ይቅማሉ። እዚያው አካባቢ የሚለምኑ አንድ ሼህ ያሲን የሚባሉ ትልቅ አዛውንት ደግሞ ከወጣቶቹ ራቅ ብለው ደክሟቸው ተቀምጠዋል። ከሚቅሙት ወጣቶች አንዱ በመሃል “ሼህ ያሲን ሼህ ያሲን” ብሎ ተጣርቶ አቤት ሲሉት አጸያፊ ስድብ ይሰድባቸዋል።

እርሳቸውም ደንግጠው “ምን አልክ አንተ ባለጌ! እኔ ትልቅ ሰው አይደለሁ? እንዴት እንደዚህ ትሰድበኛለህ?” ይሉታል። ልጁም መለስ ያደርግና ይቅርታ ይጠይቃል። ይቅርታው ግን ስለ እርሳቸው ክብርና ሊያደርግ ስለማይገባው ስድብ አልነበረም፤ ይልቁንም ስድቡን በአንቱታ ቀይሮ ዳግም እኚያን አባት አሳዘናቸው። እኔ ይህንን ስሰማ ሽምቅቅ አልኩ። ይሄ ወጣት መቀለዱ ነው የሚል ይኖራል። ግን እንደዚህ ዓይነት ምክንያት አልባ፣ ከየት ተነሱ ቢባሉ መነሻቸው የማታወቅ፣ መድረሻቸውም ያልተለየ ንግግሮች፣ የመከባበር እሴቶቻችን መጥፋትና የሰብዓዊነታችን መንጠፍ ትልቅ ማሳያ ናቸው።

ደግሞ አንድ ሰው የሌሎች ሰዎችን ክብር የሚያወርደው ለራሱ ያለው ክብር ሲወርድ ነው። የዚህ አይነት የሰብዓዊነታችን መንጠፍ፣ የመከበበር እሴቶቻችን መጥፋትና የማንነታችን መዝቀጥ ምክንያቱ ደግሞ ከወጣቶቹ የሥራ ማጣት፣ ተስፋ መቁረጥና ከ‹ነገ ምን እሆናለሁ ፍርሃት› እንዲሁም ነገን በተስፋ ለማየት ካለመቻል የሚመነጩ ናቸው። አንድ ወጣት ሠርቶ መለወጥ እንዳለበት አምኖ፣ በሙሉ ጊዜው እውቀቱንም ጉልበቱንም ተጠቅሞ ካሰበበት ለመድረስ ሲጣጣር ኖሮ መሃል ላይ ሲደርስ ንግድ በቤተሰብ፣ ሥልጣን በብሔር፣ እድል በትውውቅ፣ የትምህርት ‹ማስረጃ› በገንዘብ መሆኑን ሲያውቅ፤ ብዙው ስኬት በአቋራጭ እንጂ በሥራ አለመሆኑን ሲገነዘብ በራሱ ተስፋ ይቆርጣል።

ያለፈ ጊዜውም በከንቱ ያባከነው ሲመስለው ይቆጨዋል። ከዚያም እንደገና ቆም ብሎ አማራጩን ያስባል። ዕድሜው በሥራ መገባደዱን ወደ ፊትም እንዲሁ ያለ ለውጥ እድሜው እስኪያልቅ ድረስ እንደሚኖር ሲገነዘብ፣ የቀድሞ አመለካከቱ ሙሉ በሙሉ ይቀየራል። ቀድሞ ለሚያውቃቸው የአገር ፍቅር፣ ታታሪ ሠራተኛነት፣ ሰውን ማክበር… ወዘተ ለሚሉ ሥነምግባራት ሁሉ ባይተዋር ይሆናል። ሰውን፣ ታሪክን፣ ሃይማኖትን ማጣጣል ይጀምራል። ከዚያ የማንነት ቀውስ፣ የስብዕና መንጠፍ ውስጥ ይገባል። የዚህ ችግር ውጤት ተቋዳሽ ደግሞ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ነው። ባለሀብት ነኝ፣ ባለሥልጣን ነኝ በሚል እንዲሁም ራሳቸውን ባልዋሉበት የክብርና የእውቀት ሰገነት ላይ ሰቅለው ከሌላው ማኅበረሰብ ለጊዜው የተሻሉና የተለዩ መስሎ የሚታያቸውም ቢሆኑ፣ የችግሩ ተቋዳሽ ከመሆን አይድኑም።

አንድ ሰው በእውቀት፣ በስራ ትጋትና በጥረት ውስጥ አልፎ የፈለገበት የሚደርስበትን ፍትሃዊ መንገዶች በገንዘብና በሥልጣን ኃይል ተፅዕኖ የተገዙበት ዜጋ፣ በሚደርስበት የሥለ ልቦና ጫና እንዲሁም ያንን በሚከተለው ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ምክንያት ‹የተለየን ነን› ለሚሉት፣ ለእነርሱም ለልጆቻቸውም የሚተርፍ አልፎ ሁላችንንም አብሮ ወደ ማንወጣው የማንነት ቀውስ ውስጥ የሚያስገባን ችግር ነው። የከሰረ ትውልድ፣ የተበላሸ ማኅበረሰብ አንድ ጊዜ ከተፈጠረ ደግሞ፣ እንዲሁ የውድቀት ቅብብሎሹ ወደ ልጅ ልጅ የሚተላለፉ በሽታ ነው የሚሆነው። ስለዚህ፤ ይሄ ችግር ሁላችንንም ስለሚመለከት ከላይ የተጠቀሱትን የችግሩን መንስኤዎች በማጥፋት የሚከባበር፣ ጥሩ የሥራ ባህልና ተስፋ ያለው ማኅበረሰብ ሆነን ለመዝለቅ የችግሩን ፈጣሪዎች ሁላችንም ባለን አቅም ልንታገላቸው ይገባል እላለሁ። አይመስላችሁም?

መርከቡ ምትኩ
agyos19@gmail.com

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here