የሕግ የበላይነት ከአንድ ወንዝ ብቻ አይቀዳም!

0
484

ከደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው በመጓዝ ላይ ሳሉ የታገቱ ተማሪዎችን ዜና መሰማት ከጀመረ ሰባት ሳምንታት ተቆጠሩ። ተማሪዎቹ ተይዘው አንድ ወር ከቆዩ በኋላ ነበር ጉዳዩ እንደ አዲስ በማኅበራዊ ሚዲያ መዘዋወር የጀመረው። በተለይም ከአጋቾች እጅ ጠፍታ ቤተ ዘመዶቿ ጋር መድረስ የቻለችው ወጣት፣ ለመገናኛ ብዙኃን ታሪኩን ማስረዳት ከጀመረች በኋላ የእገታው ጉዳይ የመገናኛ ብዙሃኀኑም ሆኑ የማኅበራዊ ሚዲያው ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል።

አርብ ጥር 7/2012 ምሽት ላይ ከዶቼ ቬሌ ጋር በጉዳዩ ላይ ቃለምልልስ ያደረጉት የኦሮሚያ የኮሙኒኬሽን ገዳዮች ቢሮ ኃላፊ ጌታቸው ባልቻ፣ ታጋቾቹ ወደ ደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ እንደተመለሱ ገልጸዋል። በእገታው ዙሪያ ያሉት ሃቆች ፍንትው ብለው መውጣት ላለመቻላቸውም ከወረዳ እስከ ፌደራል ያለው እና በሕግ ለጉዳዩ በቀጥታ ተጠያቂ የሚሆነው የሥራ ኃላፊ እንዳላዩ እና እንዳልሰሙ ሆነው ከርመዋል። ድምጹ እየበረታ ሲመጣ ደግሞ በማስረጃ ሊደገፍ ያልቻለ መረጃ በመስጠት የታጋች ልጆችን ቤተሰቦች ለስቃይ የዳረገ ነበር። ለወትሮው መረጃ በመስጠት የማይታሙት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሬስ ሴክሪታሪያት ኃላፊ ንጉሡ ጥላሁንም፣ በመንግሥት ሚዲያ ቀርበው የማይረጋገጥ እና ከእርሳቸው ወደ ሚዲያው ብቻ በአንድ መስመር የፈሰሰ መረጃ ጣል አድርገው ጠፍተዋል።

የእጅ ስልካቸውም ለአንድ ሳምንት ሳይነሳ ከርሟል። ታዲያ ይህ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ እስከ ታችኛው የወረዳ አስተዳደር ያለው የመንግሥት አካል ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ትክክለኛ ምላሽ ሊያገኝ ያለመቻሉ፣ መንግሥት አለበት የሚባለውን ድክመት በግልጽ የሚያሳይ ነው። የሕግ አስፈጻሚ እና የደኅንነት አካላትም ቢሆኑ ፈጣን ምላሹ ቀርቶ የሚመለከታቸው ለመምሰል ምንም ዓይነት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ያለማሳወቃቸው፣ በአገሪቷ የተንሰራፋው ሕገ ወጥነት አስገራሚ እንዳልሆነ የሚጠቁም ነው።

በዚህ እገታ ብቻ ሳይሆን በየጊዜው በሚከሰቱ ሌሎችም የዩኒቨርሲቲዎች ረብሻዎች እንዲሁም የፖለቲካ እና የሃይማኖት መሠረት ያላቸው ጥቃቶች ውስጥ መገንዘብ የሚቻለው፣ የመንግሥት መዋቅር ውጤታማነት እያነሰ መሔዱን ብቻ ሳይሆን እንደ ማኅበረሰብ እሴቶቻችን እና መስተጋብሮቻችን እየፈረሱ መምጣታቸውን ነው። የመንግሥት መዋቅር በእኛው በኅበረተሰቡ የሚገነባ እንጂ መቼ ከሰማይ አልወረደ? በየሳምንቱ አስደንጋጭ የሆኑ ወንጀሎች በቡድን እና በተናጠል እንደተፈጸሙ መስማት መደበኛ የሕይወት አካል እየሆነ በመጣባት አገራችን ኢትዮጵያ፣ በጠንካራ ማኅበራዊ መስተጋብር እና መንፈሳዊ እምነት የተገነባው ሰብዓዊነት በፍጥነት እየተሸረሸረ ነው።

ይህ ዘመን ነጋዴው እኔ ብቻ ልክበር በሚል ስሜት በብዙ እጥፍ የሚያተርፍበት፣ ፖለቲከኛው ለአገር ሳይሆን ለግል ሥልጣን ወይም ጥቅም ሕዝብ የሚያባላበት፣ የመንግሥት ሠራተኛው በቀላሉ በሙስና የሚታለልበት፣ ፖሊስ ወገንተኝነት የሚያሳይበት፣ የሃይማኖት አባቶች በምዝበራ የተሰማሩበት፣ ዜጎች በተለያዩ ጉዳዮች ተከፋፍለው የሚቆራቆዙበት ነው። ጉቦ አልበላም ብሎ ከሚያልፍ ይልቅ የማጭበርበሪያ መንገድ አዘጋጅቶ ከሕዝብ የሚዘርፍ እንደ ጎበዝ የሚቆጠርበት፣ ጨዋነት እንደ ፈዛዛነት እና እንዳለመንቃት የሚታይበት፣ እምነትን ማጉደል በሰፊው የሚጠበቀው ባህሪ እንጂ የጥቂት ባለጌዎች ባህሪ ተደርጎ የማይታይበት፣ ከፋፋይነት እንደ ተቆርቋሪነት፣ ዘረኝነት እንደ ጀግንነት፣ ህሊናን መሸጥ እንደ ተራማጅነት የሚቆጠርበት ዘመን ላይ ነን ያለነው። ማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ እንደገባን የሚጠቁም ብዙ ሌሎችም ምልክቶች ቢኖሩም፣ በየሳምንቱ የሚታዩትን ችግሮች መፍትሔ ከመፈለግ ጎን ለጎን አጠቃላይ ሁኔታውን ተገንዝቦ መፍትሔ ማፈላለግ ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ ነገር አይደለም።

በአገሪቷ ባሉ ቁጥራቸው በርካታ በሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ትምህርት ተቋርጦ ተማሪዎች ጥሮ ግሮ ለቁምነገር ሊበቁልኝ ነው ወደሚላቸው ቤተሰብ ከመመለሳቸውም በላይ፣ ሌላ ክልል መሔድ በራስ ሕይወት እንደመወሰን ሲሆን፣ ማንም ተጠያቂነቱ የማይመለከተው የማኅበረሰብ አካል ሊኖር አይችልም። በያዝነው ሳምንትም የመንግሥት ግዢ እና የንብረት ማስወገድ አገልግሎት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫም፣ የመንግሥትን የግዢ መመሪያ ተከትለው ግዢ በማይፈፅሙ ተቋማት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ እና ለሕዝብ ሃብት መባከንም ምክንያት ሆኖ መቀጠሉን አስታውቋል። በየ ዓመት የበጀት ጫመት መዝጊያ በሚቃረብበት እና የቀጣይ ዓመት በጀት ረቂቅ በሚዘጋጅበት ጊዜ ሁሉ የሚሰማው ይሄ መፈክር እያለ፣ የግዢ ሂደቱን ያልተከተሉ ተቋማትን በዓመቱ መጨረሻ ዋና ኦዲተር በሪፖርቱ አጠቃሎ ይዞ ይወጣል። በፌደራል ተቋማት ደረጃ ሳይቀር የተሰንራፋው ይህ ከሕግ ውጪ መሆን የነገሠበትን ሥራ የመምራት አዝማማያ በየደረጃው እየተባባሰ የሚሄድ ነው። ታዲያ ሕግን እንደ አስተያየት የሚቆጥረው ይህ የመንግሥት መዋቅር፣ ነገሩ ልኩን ከሳተ በኋላ እና ንብረት ከባከነ ወዲያ ባለሥልጣኑን ከሥልጣኑ በማንሳት ለመቅጣት ሲሞክር ይታያል።

የተመዘበረው ገንዘብ የአገሪቱን ህልውና የሚገዳደር ሲሆን፣ ዐይን ሲያወጣም በሙስና ወነረጀል በመቅታት ለሕዝብም ለተከሳሾቹም ያን ያህል የማይጠቅም እርምጃ ይወሰዳል። ግብርን መሰወር የእለት ተእለት ተግባር የሆነበት የንግድ ስርአት የያዘው የንግድ ማኅበረሰብ፣ ሙሰኛ ባለ ሥልጣኖችን ሲያማርር ይስተዋላል። በአዲስ አበባ ከተማ ተባብሶ የቀጠለው የትራንስፖርት ችግር አሁን አሁን ሃይ ባይ ያጣና የተዘጋ ዘርፍ ሆኗል። ከሥራ መውጫ ሰዓቶች ላይ ሆን ተብሎ የታክሲ ስልፍ እንዲፈጠር በማድረግ እና ለዐይን ያዝ ሲያደረግ ከመደበኛ ክፍያው ላይ እጥፍ በመጨመር መጠየቁ የተለመደ ነው። ከዓመት በፊት ከ ሦስት ሰዓት በኋላ ሕግ የለ፣ የሚለው አባባል አሁን ከአንድ ሰዓት በኋላ ሆኖ በኑሮ ውድነት ለሚያሰቃየው ሰርቶ አደር በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኗል። ታዲያ ‹‹መንግሥት ሕግ ማስከበር አቅቶታል›› በሚል የጋራ ምክንያት በየጉያችን የያዝውን የየግላችንን ስርአት አልበኝነት ለመሸፈን ማዋሉ ዳፋው መልሶ ለራስ ነው።

በሚሊዮኖች የሚቆጠረው የመንግሥት ሠራተኛ ሥራውን በአግባቡ ቢሠራ እና በሥራ ገበታው ላይ በሰዓቱ ባለመገኘቱ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ መምራት አልቻሉም›› ማለቱ በገዛ ጉድፍ ላይ ምጸት ነው። ከድሃ ባለጉዳይ ላይ የነጠቁት የሙስና ገንዘብ ‹‹የመግዛት ዋጋው ወረደ እኮ›› ማለት ስንዴ ዘርቶ ጤፍ ካላጨድኩ ማለት ነው። ግብርን በአግባቡ ለመክፈል ሳይፈልጉ ሆስፒታል እና መንገድ በአውሮፓ ደረጃ ካልቀረበልኝ ማለት ዘበት ነው። ስለዚህም አንዳንዴ ያጋጠሙንን ችግሮች ከኪሳችን በተዋጣው ግብር ደጉምን ያቆምናቸው የፀጥታ ተቋማት የማይፈቱት እና በማኅበራዊ መስማማት ልናስወግደው የሚገባ የሞራል ውድቀት እንጂ ‹‹መንግሥት›› የመጣብን ጣጣ አይደለም። ማኅበራዊ መስተጋብራችን፣ ፖለቲካውም ሆነ ኢኮኖሚው እንደ ግለሰብ አእምሮአችንን ለህሊና በማስገዛት የወረወርነው ድንጋይ ዞሮ እንደሚመታን ካላሰብን አዙሪቱ ይቀጥላል። ስለዚህ የሕግ የበላይነትን ለመመለስ ሕግ ሰምተን የምንተወው ምክር ሳይሆን እየመረረን የምንውጠው ሀቅ ይሁን!

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here