በደቡብ ክልል የተነሱ የክልልነት ጥያቄዎችን የሚያጠናውን ቡድን አባዱላ ገመዳ እንዲመሩት ተመረጡ

0
602

ከዚህ ቀደም ተሞክሮ ውጤት ያልሰጠ አማረጭን በድጋሚ ማቅረብ ጊዜ መግደል ነው

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) በደቡብ ክልል የተነሱ የራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት ያቋቋሙትን ኮሚቴ የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስቴር እና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንት የነበሩት አባዱላ ገመዳ እንዲመሩት ተመረጡ። ከተለያዩ ብሔሮች የተወጣጡ እና ምሁራንን ያጠቃለለው ይህ ኮሚቴ 80 አባላት ሲኖሩት በክልሉ የተነሱ በደቡብ ክልል የክልልነት፣ የዞንነት፣ ልዩ ወረዳ የመሆን፣ የብሄረሰብ ማንነት ጉዳይ ጨምሮ የልማት እና የመከልከም አስተዳደር ጥያቄ የሚቀርቡትን ለይቶ የሚያቀርብ ኮሚቴ እንደሆነ ታውቋል። የወላይታ ብሔርን በመወከል በኮሚቴው አባል የሆኑት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምህር አሸናፊ ከበደ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ግለሰቦቹ የተመረጡት የህብረተሰቡን ጥያቄ ለማቅረብ እና ቅሬታቸውን ለማስተላለፍ ቅርብ በመሆን ወይም ተጽኖ ፈጣሪ ናቸው ተብሎ በመታመኑ ነው።

 ከዚህ በፊት የክልልነት ጥያቄን በተመለከተ የክልሉ ገዢ ፓርቲ ደኢህዴን አካሂዶት የነበረው የጥናት ውጤት በትክከለኛ መንገድ ባለመመራቱ እና ጥናቱን ሲመራው የነበረው ክልሉን ይመራው የነበረው ፓርቲ ስለነበረ በገለልተኝነት የመስራት ነፃነት ስለማይኖረው ውጤታማ እንዳይሆን አድርጎታል ሲሉ አሸናፊ ተናግረዋል። አሁን የተዋቀረው ኮሚቴ ዕቅዱን ካወጣ በኋላ በዛ መሰረት የደረሱበትን ለህዝቡ ማሳወቅ እንደሚጀምሩም ጨምረው ተናግረዋል። የወላታ ብሄራዊ ንቅናቄ(ወብን) የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ተከተል ላቤና ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት በደቡብ ክልል ውስጥ ሲነሱ የቆዩት የአደረጃጀት ጥያቄዎች ሕገ መንግስቱን መሰረት አድርገው የተነሱ በመሆናቸው ሊመለሱ ይገባቸዋል ብለው እንደሚያምኑ ተነግረዋል።

ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ያስቀመጡት አቅጣጫ ትክከል አደለም ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል። ‹‹ከዚህ ቀደም ተሞክሮ ውጠት ያልሰጠ አማራጭን በድጋሚ ማቅረብ ጊዜ መግደል ነው›› ብለው ‹‹ ይህም ተገቢነት የሌለው ኢ-ሕገ መንግስታዊ የሆነ አካሄድ ነው›› ሲሉ ተናግረዋል። ‹‹ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ የክልልነት ጥያቄ ካቀረቡ 11 ዞኖች የሲዳማ ሲቀነስ የቀሩት 10 ቢሆኑም ጥያቄ ካላነሱት ጋር ቀላቅለው አብሮ ኮሚቴ ማዋቀር ማለት የጥያቄ አቅራቢዎችን ድምጽ ማፈን ነው›› ብለው እንደሚያምኑም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ይህም መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ ተጨማሪ ችግር ሊያመጣ ይችላል ብለው እንደሚሰጉም የወብን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ተከተል ይናገራሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰብአዊ መብቶች እና የፌደራሊዝም ረዳት ፕሮፈሰር የሆኑት ሲሳይ መንግስቴ (ዶ/ር) ይህንን ኮሚቴ በግላቸው እንደማያምኑበት ገልጸው ‹‹የችግሩን ዋና መሰረት የሚፈታው በጊዜያዊነት በሚቋቋሙ ኮሚቴዎች ሳይሆን በዘላቂነት ታይቶ በፌደራል ደረጃ ባለው የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ነበር›› ብለዋል።

ነገር ግን ኮሚሽኑ ይሄን ስራ ቶሎ እንዲጀምር አለመደረጉ እና አሁንም በአጥጋቢ ሁኔታ ስራውን እየሰራ አለመሆኑ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው ብለዋል። ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ጥናት ተጠንቶ ውጤት አለማምጣቱን ፕሮፌሰሩ ገልጸው አሁንም ህብረተሰቡ ባልወከላቸው ሰዎች ስራውን መሰራቱ መፍትሄ አያመጣም ሲሉ ኮሚቴውን ተችተዋል። መንግስት የመለመላቸው ግለሰቦች የሚሰሩት ጥናት ትክክለኛውን የህብረተሰብ ችግር ማውጣት ያልቻሉ ናቸው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በደኢህዴን የተሰራው ጥናት በክልሉ የሚነሱትን የክልልነት ጥያቄዎችን ጨምሮ የተለያዩ ቅሬታዎችን ለመዳሰስ ሞክሮ ነበር። የጥናቱ ዋና አላማ ከነበሩት ውስጥ የደቡብ ብሔር በሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል መንግስት አመሰራረት ሂደትን መዳሰስ፣ የክልሉ ህዝቦች አብሮ በቆየባቸው ዓመታት ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶች መዳሰስ እና በክልሉ የሚነሱ አደረጃጀት ጥያቄዎች መንስኤያችውን ማጥናት ዋና ዋና ተግባራቱ ነበሩ።

ቅጽ 2 ቁጥር 64 ጥር 16 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here