የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ዕድገት – ሀብት ወይስ ስጋት?

0
1216

መንገዶች፣ የገበያ ቦታዎች፣ ከከተማው ውጪ ጉዞ የሚደረግባቸው የአውቶብስ መናኽሪያዎች፣ የእምነት ተቋማት ወዘተ ከእለት እለት የሚንቀሳቀሱባቸው ሰዎች ብዛት እየጨመረ ነው። አዲስ አበባን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ ከተሞችም ፍልሰትን የሚያስተናግዱ በመሆኑ፣ ግርግሩና መጨናነቁ ሕዝብ እየበዛ ለመሆኑ ማሳያ ሆነዋል። ባለሙያዎች በሰጡት ትንበያ መሠረት ደግሞ በ2050 የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት 200 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሏል። በቀን ሦስት ጊዜ መመገብ ከባድ በሆነባት አገር አሁን ካለው በላይ ሕዝብ መሸከም ቀላል እንደማይሆንላት መገመት ቀላል ነው። ያም ሆኖ የአምራቹ ኃይል ወይም ወጣቱ እየበዛ መሆኑም ጥሩ አጋጣሚ ነው የሚል ሙግትም አለ። በኹለቱ መካከል በጥርጣሬና በማመን ውስጥ እየዋዠቁም፤ የሕዝብ ብዛት ስጋትም ሀብትም የሚሆነው ከአያያዛችን ነው በማለት መንግሥትን የሚያሳስቡ አሉ። እነዚህን ነጥቦች በሚመለከት የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ባለሞያዎችን በማናገር፣ ጉባኤዎች ላይ በመታደም እንዲሁም ዘገባዎችን በማገላበጥ ነገሩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጋዋለች።

የዓለም ሕዝብ ቁጥር ብዛት እየጨመረ ይገኛል። በአውሮፓ የተሠራ አንድ ጥናት እንደሚያመላክተው፤ የዓለም ሕዝብ በ1792 ከነበረበት አንድ ቢሊዮን አሁን ላይ ወደ 7.7 ቢሊዮን ተጠግቷል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ይህን የሕዝብ ቁጥር መጨመር በቢሊዮን መለስ ብሎ ሲያሰላ፤ በ1795 ዓለም የመጀመሪያውን አንድ ቢሊዮን ሕዝብ አስተናግዳለች ይላል።

ቀጥሎ የሕዝብ ብዛት ኹለት ቢሊዮን ለመድረስ 124 ዓመታት ወስዶበታል። ይሁንና አካሄዱ በዛ ርቀት አልቀጠለም። ከኹለት ቢሊዮን ላይ ሌላ አንድ ቢሊዮን ለመጨመር የ33 ዓመት ጊዜ ብቻ ወስዷል። ቀጥለው ላሉት ቢሊዮኖች ለእያንዳንዳቸው ደግሞ 12 ዓመታት ልዩነት ብቻ ወስዷል። ከዚህ በኋላ አሁን ካለው ፍጥነት በባሰ የሕዝብ ብዛት እንደሚጨምር ይገመታል። በአኅጉረ አፍሪካ የምትገኘው ኢትዮጵያም በዚህ የዓለም ሕዝብ ቁጥር መጨመር ላይ አስተዋጽኦና ድርሻ ካላቸው አገራት መካከል ናት።

ምንም እንኳ ሕዝብ ቆጠራ በቅርቡ የተከናወነ ባይሆንም፤ የቀደመውን በመመልከትና የወደፊቱን ከዛ አንጻር በመገመት በ2050 የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ኹለት መቶ ሚሊዮን እንደሚገባ ከወዲሁ ተተንብይዋል።

የሕዝብ ብዛት – አስፈሪ ገጾቹና እድሎቹ

በኢትዮጵያውያን እምነት እንዲሁም ብሂል ልጅ ፀጋ/ ስጦታ ነው። ጧሪ ቀባሪም ስለሆነ ሀብት ነው ይባላል። ስለዚህም አቅም እስከ ፈቀደ ድረስ የኑሮ ሁኔታን ታሳቢ ባላደረገ መልኩ ልጆችን የመውለድ ባህል በብዛት ይታያል። ይህ በተጨማሪም ከወሊድ መቆጣጠሪያ ተደራሽነት አልፎም ካለው የማኅበረሰብ ግንዛቤ ጋር የተያያዘ ሆኖም ቆይቷል። ይህም ኢትዮጵያን ደሃ አገር ብትሆንም የልጅና የሰው ሀብታም አድርጓታል። ይህ ሲሆን ልጅ ‹‹ጥርስና ሆድ ብቻ ሳይሆን እጅም ይዞ ነው የሚወለደው›› በሚለው ሐሳብ የሚስማሙ አይጠፉም። በአንጻሩ የሕዝብ ብዛት አስፈሪና አስጊ ሆኖ የሚታያቸው ወገኖችም አሉ። በእርግጥ አንዲት አገር ካላት ሀብትና አቅም አንጻር ተመጣጣኝ ያልሆነ ሕዝብ ካስተናገደች በጠቅላላው ድህነት ውስጥ ስቦ የሚጨምራት ክብደት ነው የሚሆንባት።

በቅርቡ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አዘጋጅቶ በድረ ገጹ ይፋ ያደረገው ‹‹የኢትዮጵያ ሥነ ሕዝባዊ ትሩፋት›› የሚል ርዕስ ያለው ገለጻ፤ ስለ ሕዝባዊ ትሩፋት ያብራራል። ሥነ ሕዝባዊ ትሩፋት ማለትም በአንድ አገር የሕዝብ እድሜ አወቃቀር ለውጥ አማካኝነት ሊገኝ የሚችል ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት መሆኑን ይጠቅሳል። ብዙዎች በሚረዱት መልኩ ሲቀመጥ፣ ሥነ ሕዝባዊ ትሩፋት በእስያ ያሉ አገራት ላሳዩት ልማት አስተዋጽኦ ማበርከት የቻለ ነው።

ኢትዮጵያ እስከ 1970ዎቹ መጨረሻ ድረስ ፈጣን የሕዝብ ቁጥር እድገት ከማስመዝገቧ በተጓዳኝ፣ ከፍተኛ ወሊድና ሞት የተመዘገበባት አገር እንደሆነች ገለጻው ጨምሮ ያነሳው ነጥብ ነው። በዛ ጊዜ፣ አንዲት ሴት በአማካይ የምትወልዳቸው ልጆች ብዛት 7 ሲሆን፤ ከሚወለዱት 1000 ሕፃናት ደግሞ 213 ያህሉ 5 ዓመት ሳይሞላቸው ይሞቱ ነበር። የሕዝብ ቁጥርም ወደ 43.5 ሚሊዮን አካባቢ ነበር።

ከሠላሳ ስምንት ዓመት በኋላ ማለትም በ2008 አንዲት ሴት በአማካይ የምትወልዳቸው ልጆች ብዛት ወደ 5 ሲወርድ፤ በሕይወት ከሚወለዱት 1000 ሕፃናት ውስጥ 5 ዓመት ሳይሞላቸው የሚሞቱት ቁጥር ወደ 67 ዝቅ ብሏል። ይህ ሁኔታ የአገሪቱን ዕድሜ አወቃቀር ቀስ በቀስ እየቀየረ የመጣ ነው። ይልቁንም ከ0- 14 ዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች ቁጥር እያነሰና የሠራተኛ ኃይል ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ፣ ‹‹ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥነ ሕዝባዊ ትሩፋትን ልታሳካ የምትችልበት የዕድል መስኮት እየተከፈተላት መኾኑን ያመለክታል።›› ሲል ገለጻው ያትታል።

ከ2020 ጀምሮ እስከ 2050 ባሉ ዓመታት፣ የኢትዮጵያ የዕድሜ ጥገኝነት ምጥጥን (በሌላ አገላለጽ ከ0-14 ዓመት እና ከ65 ዓመት በላይ ያለው የሕዝብ ቁጥር) ከ15 – 64 ዕድሜ ክልል ውስጥ ካለው የሕዝብ ቁጥር ጋር ሲነጻጸር 32 በመቶ እንደሚሆን ሳይንስ አካዳሚ ጨምሮ ይጠቅሳል። ቀጥሎም ሲያብራራ ‹‹ይህ ማለት፣ የሠራተኛ ዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ በየአንድ መቶ ሰዎች ልክ፣ በአማካይ 32፣ ዕድሜያቸው ከ15 በታችና ከ64 በላይ የሆኑ ሰዎች ይኖራሉ። ይህ ቁጥር ከመቼውም ጊዜ ያነሰ ነው።››

ይህ መሆኑ ታድያ ሠራተኛው ኃይል ከጥገኛው ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ድርሻ እንዲኖረው በማድረግ ኢትዮጵያ ሥነሕዝባዊ ትሩፋት እንድታሳካ እድል የሚከፍት ነው፤ እንደ ገለጻው ከሆነ። ይህ ማለት የሕዝብ ቁጥር መጨመር ለኢትዮጵያ ስጋት ሆኖ እንዳይሰማት፤ አብዛኛው ሠርቶ ማደር የሚችል ዜጋ በመሆኑ በዚህ ትሩፋት ተጠቃሚ ትሆናለች የሚል ነው።

ይህ ጥሩ እድል ሊባል የሚችል ሆኖ፤ የሕዝብ እድገት ስደትን ያስከትላል ሲሉ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት የሥነ ሕዝብ እና የኑሮ አስተዳደር ፕሮግራሞች አስተባባሪ አሕመድ መሐመድ ይናገራሉ። ‹‹በገጠር ያሉ ልጆች አሁን ለአቅመ አዳም ደርሰዋል፤ ግን መሬት የላቸውም። ስለዚህ ያላቸው አማራጭ ወይ ከተማ ይመጣሉ ወይም ስደት ይወጣሉ፤ ባህር አቋርጠው። ለእነርሱ የሚሆን ሥራ የለም።›› ሲሉ ያነሳሉ። ለሚታየው አስከፊ ስደትም የሕዝብ ቁጥር መጨመርን ምክንያት አድርገው ይጠቅሳሉ።

ከዚህ ባለፈ ወሳኝ የሚባሉ መሠረተ ልማቶችን ለማሟላትም የሕዝብ ብዛት ፈታኝ የሚሆንበት አጋጣሚ አለ። ይልቁንም ወደ ከተማ በሚኖር ፍልሰት የተነሳ፣ ለምሳሌ ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ በተለያየ ጊዜ ችግሮች ከዚህ ጋር ተያይዘው ተነስተዋል። ‹‹የውሃ አቅርቦት ችግር የገጠመው ካለው የሕዝብ ብዛት አንጻርና ቀድሞ የተገመተ ስላልነበር ነው›› የሚል መግለጫም በተለያየ ጊዜ ተሰምቷል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ‹‹መደመር›› በተሰኘና ባለፈው ዓመት 2011 ባሳተሙት መጽሐፍ ይህን ጉዳይ በአንድ ንዑስ ምዕራፍ ቃኝተውታል። በዛም ‹‹የወጣት ኅብረተሰብ ክፍል ቁጥር ሲጨምር የአገራችን የኢኮኖሚና ማኅበራዊ እድሎች በተለይም የተፈጥሮ ሀብት እጅጉን እየተመናመነ መጥቷል። የእርሻ መሬት ከመጣበቡ ጋር በተያያዘ የሚታረስ መሬት ያጣ ወጣት ወደ ከተሞች እየፈለሰ ነው።›› ሲሉ የሕዝብ ብዛት በነባራዊ ሁኔታ ያስከተላቸውን ችግሮች ጠቅሰዋል። ይህን መፍታት የሚቻለውም አስተማማኝ የሥራ እድል እና የሠራተኛ ክህሎት የሚያሳድግ ፈጣን የኢንዱስትሪ ልማትን ማምጣት ሲቻል ነው ሲሉ አክለዋል።

በመጽሐፋቸው በሕዝብ ብዛት ጥቅምና ጉዳት ላይ ኹለት ዐበይት ነጥቦች ይነሳሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አንደኛው የሕዝብ ቁጥር በፍጥነት ማደግ የኑሮ ደረጃ እንዲያሽቆለቁል ማድረጉ ነው። ሌላው ባለ ብዙ ሕዝብ መሆን ለሥራ የሚሆን ብዛት ያለው አምራች ኃይል ባለቤት እንደመሆን ነውና ትሩፋት አለው ሲሉ ጠቅሰዋል። ጨምረው ‹‹የሕዝብ ብዛት እድገት ከኢኮኖሚ እድገት አንጻር የተመጣጠነ እስከሆነ ድረሰ የእድገት ሞተር ነው። የተመጣጣኝነት ልኩን ካለፈ ግን ኢኮኖሚያዊ እድገት ጎታች ይሆናል።›› ሲሉ ጥቅምና ጉዳቱን በአንድ ገልጸዋል።

ሀብት ወይስ ስጋት?

ይህ የሕዝብ ብዛት ወይም የሰው ኃይል ሀብት እንጂ ስጋት እንዳይሆን፣ ‹‹የማይተካ ሚና አላቸው›› በተባሉ ቁልፍ ዘርፎች ላይ ማለትም ጤና፣ ትምህርት፣ የሥራ ዕድል እና መልካም አስተዳደር ላይ አተኩሮ ከወዲሁ መሥራት ያስፈልጋል ተብሏል፤ በሳይንስ አካዳሚ አጠር ያለ ገለጻ ላይ።

በታኅሳስ ወር መጀመሪያ ‹‹ኢትዮጵያ በ2050 – ግዙፍ ተግዳሮቶች እና እድሎች›› የተሰኘ ዓለም ዐቀፍ ጉባኤ በስካይ ላይት ሆቴል ተካሂዶ ነበር። ኢትዮጵያ ከሠላሳ ዓመታት በኋላ ሕዝቧ 200 ሚሊዮን ይደርሳል የሚል ቅድመ ትንበያ መቀመጡን ተከትሎ፣ ከወዲሁ ምን መሠራት አለበት በሚለው ላይ ሐሳባቸውን ለማካፈልም ኢትዮጵያውያን የዘርፉ ባለሙያዎች እና ተመራማሪዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በመድረኩ ላይ ተሳትፎ አድርገዋል።

ደብረወርቅ ዘውዴ (ዶክተር) በጉባኤው ላይ ከተሳተፉ መካከል ናቸው። እርሳቸው ታድያ ምንም እንኳ የአምራች ኃይል መብዛት በድምሩም የሕዝብ ብዛትን ለለውጥ መጠቀም ይቻላል በሚለው ቢያምኑም፤ የኢትዮጵያ ሁኔታ እንደሚያሰጋቸው ግን ሳይጠቅሱ አልቀሩም። ‹‹አሁን ላለውም ብዙ አገልግሎት ማቅረብ አልቻልንም፤ የመብራትና የኤሌክትሪክ፣ የውሃ፣ የጤና፣ ትምህርት ቤቶች ኢንተርኔት አቅርቦት ዝቅተኛ ነው።›› ሲሉ ይገልጻሉ።

ለደብረወርቅ የሥነ ሕዝብ ትሩፋት ስጋት እንዳይሆን ከወዲሁ ቀደም ብሎ ያንን በማሰብ መሥራት ወሳኝ ነው። አሁን ላይ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሁሉ በቅርብ ርቀት ሊመጣ ያለውን ሕዝብም ታሳቢ ያደረጉ ሊሆኑ ይገባል ባይ ናቸው።

‹‹መነሻችንን ማወቅ አለብን። ዛሬ የምናመጣው ወደፊትም የሚያገለግል ቴክኖሎጂ ውጤት ይህን ማገናዘብ አለበት። የሕዝብ ብዛት ሲጨምር ከ15-64 ያለው ካልተማረ ጤና ካልሆነ ደሃ ሆኖ ነው የሚቀረው።›› ሲሉ አስረግጠው ይገልጻሉ።

‹‹የገጠር ኢትዮጵያ የልማት ሁኔታና ተስፋ›› በሚል ርዕስ በዛው ዓመታዊ ጉባኤ የዳሰሳ ጥናት ያቀረቡት የስታቲስቲክስ ባለሙያው አየነው እጅጉ በበኩላቸው፣ ነገሩን ከኑሮ ውድነት ጋር አገናኝተው ያብራሩታል። ለውጥ ለማምጣትና የበዛውን የሰው ኃይል በሚገባ ለማስተናገድም ለከተማ የሚሰጠውን ያህል ትኩረት ለገጠር ሊሰጥ ይገባል ሲሉ ይሞግታሉ፤ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በገጠር የሚኖር በመሆኑ።

በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል ታታሪ ሕዝብ መኖሩን ያነሱት አየነው፤ በዚህ መጠቀም ለመቻል ትኩረትን ወዳዛ ማዞር ያስፈልጋል። ግብርና አካባቢ ያለው እንቅስቃሴም ያለውን የኑሮ ውድነት ሳይቀር ሊፈታ እንዲችል ማድረግ ይቻላል የሚል ሐሳብ አቀብለዋል።

ይህን ነጥብ አተኩሮ ለተመለከተ እርግጥም ትኩረቱ ገጠር አካባቢ ሊሆን እንደሚገባ አይጠራጠርም። ይልቁንም ከትንበያው አንጻር በ2050 የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት 200 ሚሊዮን ሲደርስ፣ በከተማ የሚገኘው 70.5 ሚሊዮን ወይም 37 በመቶው ብቻ ነው የሚሆነው። የቀረው በገጠር የሚገኝ ሲሆን፣ አዲስ አበባ አስር ሚሊዮን ላይ እንደምትቆይ ያመላክታል።

ታድያ የሕዝብ ብዛት ስጋት ሊሆን የሚችለው እንደሚታወቀው ከኢኮኖሚ እድገት ጋር አለመመጣጠን ሲኖር ነው። እናም የሕዝብ ቁጥር መጨመር በዚህ ሁኔታ ድህነትን የሚያባብስ እንጂ በምንም ተዓምር በረከት ተደርጎ ሊቆጠር የሚችል አይደለም። አየነው በዚህ ላይ ሲያክሉ፤ አትውለዱ ማለት እንደማይቻልና ነገር ግን ማስተማርን ዘዴ አድርጎ መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ ያነሳሉ።

የሥነ ሕዝብ እና የኑሮ አስተዳደር ፕሮግራሞች አስተባባሪ አሕመድ፣ በአየነው ሐሳብ ይስማማሉ። በከተማና በገጠር ያለውን ልዩነት መስበር ያስፈልጋል ሲሉም ይሞግታሉ። በዚህ ብቻ ሳይሆን የግብርና መር ኢንዱስትሪን ማስፋፋትን መንግሥት ሲያሞካሸው የኖረ ጉዳይ ቢሆንም፣ የገበሬውን ኑሮ ግን ለውጧል ወይ ሲሉ ይጠይቃሉ።

‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዛኛው ገጠር ስለሚገኝ፤ ያንን ካልለወጥን ዋጋ የለውም።›› ሲሉም ሥነ ሕዝብን የተመለከተ ልማት ከገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍሎች መጀመር እንዳለበት አጥብቀው ያነሳሉ።

‹‹አንድ እናት መውለድ በምትችልበት ዘመኗ የምትወልዳቸው ልጆች በገጠርና በከተማ ከኹለት እስከ ሦስት ልጆች ልዩነት አለ። ገጠር አምስት ልጆች ስትወልድ እዚህ ኹለት ትወልዳለች። ገጠር ያለች ልጅ በጊዜ ታጭታ ትዳራለችና በየኹለት ዓመቱ ብትወልድ እንኳ እስከ ሰባት ልጅ ልትወልድ ትችላለች።›› ሲሉ ነገሩን ያብራራሉ። እዚህ ላይ የሳይንስ አካዳሚ ገለጻም ያግዛቸዋል፤ በገጠር የምትኖር አንዲት ሴት በመውለጃ ዕድሜዋ የምትወልዳቸው ልጆች ቁጥርም በከተማ ከምትኖር አቻዋ በ3 ልጆች ይበልጣል ይላል።

መሐመድ በበኩላቸው ታድያ አሁን ባለው የኢትዮጵያ አካሄድ የሕዝብ ብዛት ‹‹ሀብት ነው ወይስ ስጋት?›› ለሚለው ኹለቱንም የሚል መልስ ለአዲስ ማለዳ ሰጥተዋል፤ እንደ አያያዙ ይወሰናል ብለው። ‹‹ትክክለኛ ፖሊሲና አካሄድ ተጠቅመን ሕዝብን ካበቃነው ሀብት ነው። ካልሆነ እንዳለፉት 27 እና ከዛ በላይ ዓመታት የምንቀጥል ከሆነ ስጋት ነው።›› ይላሉ።

የቀደሙት ዓመታት ሥራን ሲቃኙም፤ ብሔራዊ ሕዝብ ፖሊሲ ከወጣ 25 ዓመት በላይ ማስቆጠሩን በማንሳት አፈጻጸሙ ላይ ክትትል ያልነበረው፣ ለባለሞያ ጩኸትም ጆሮ ያልሰጠ አካሄድ እንደተሄደ ያነሳሉ። አብዛኞቹ ችግሮችም በትክክል ፖሊሲው ያለመተግበሩ ያመጣቸው መሆናቸውን ጭምር በመጥቀስ።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በዚህ ነጥብ ላይ በገለጻው ተከታዩን ሐሳብ አካትቷል፤ ‹‹የኢትዮጵያ የሥነ ሕዝባዊ ትሩፋት ስኬት የዕድሜ አወቃቀር ለውጥን ለማፋጠን፣ የዜጎችን ጤናና ክህሎት ለማዳበር፣ እንዲሁም በየጊዜው እየጨመረ ለሚሄደው አምራች ኃይል የሥራ ዕድል ለማቅረብና ለማመቻቸት ባለው የኢኮኖሚ አቅም ይወሰናል። ዜጎች ክህሎቶቻቸውንና ብቃታቸውን ተጠቅመው ገቢ የሚያገኙበትና ለኢኮኖሚው አስተዋፅዖ የሚያደርጉበት ዕድል በሌለበት ሁኔታ የአምራች ኃይል መብዛት ሥነ ሕዝባዊ ትሩፋትን ከማሳካት ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል።››

በፖሊሲ ልጓም የተሄደበት ርቀት

የሕዝብ ብዛት ጠቀሜታና የሚፈጥረው ስጋት፣ ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር ሲታይ ከፋም ለማ የሕዝብ ቁጥር እድገት ፍጥነቱን በተወሰነ ደረጃ መግራትና መቀነስ እንደሚያሻ ባለሞያዎች ይናገራሉ። መሐመድ በዚህ ላይ ሐሳብ ሲሰጡ፣ ‹‹ማስቆም አንችልም።›› ይላሉ። ማስቆም አይደለም በተወሰነ ደረጃ ፍጥነቱን ለማብረድ መሞከር ማለት በፍጥነት ይሄድ የነበረን ተሽከርካሪ በድንገት ፍሬን ይዞ ለማቆም እንደ መሞከር ነው ይላሉ፤ ይንሸራተታል።

ብዙዎች ምሳሌ አድርገው የሚያነሷትን ቻይናን አሕመድም በምሳሌነት ጠቅሰዋታል። ቻይና በፖሊሲ ለውጥ ሕዝብ ብዛትን መቆጣጠርና ለውጥ ማምጣት፣ በ40 እና 50 ዓመታት ውስጥም በዚህ ለውጥ ዓለምን ማስደመም ችላለች። ‹‹በእርግጥ በሰዉ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ አይሁን እንጂ [ፖሊሲው] ቻይናን ጠቅሟታል። አሁን ያለውን እድገትና ሕዝብ የሚይዙበት መንገድ ያ ፖሊሲ ባይኖር ኖሮ ከባድ ይሆን ነበር።›› ሲሉ ያክላሉ።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛቱ እየጨመረ መሆኑ ስጋት እንዳይፈጥርበት አልያም ተስፋ ሰጥቶ ለማበርታት ይሁን ባልታወቀ ሰበብ፤ መንግሥት ቻይናን ብዙ ጊዜ በምሳሌነት ይጠቅሳል። ቻይና አሁን ላለችበት የደረሰችውም በሕዝብ ብዛቷ ነው ይላሉ። ‹‹ፖለቲከኞች የቻይናን ማደግ እንጂ በምን መንገድ እዚህ እንደ ደረሰች ሊያነሱ አይፈልጉም።›› ሲሉ መሐመድ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ሥነ ሕዝብ ፖሊሲ እንደ ቻይና ‹‹ይህን ያህል ብቻ ውለዱ›› ባይልም የራሷ ሥነ ሕዝብ ፖሊሲ አላት። የዚህ ሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ዐቢይ ጉዳይ የሕዝብ ዕድገት ምጣኔ ከኢኮኖሚ ዕድገት ጋር በማጣጣም ከረጅም ጊዜ አኳያ የዜጎች የኑሮ ደረጃና አጠቃላይ ደኅንነት እንዲሻሻል ማድረግ ነው ሲል፤ ኹለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በሥነ ሕዝብ ዙሪያ ባብራራበት ክፍል ያትታል። በዚህ ዙሪያ የሚመዘገቡ ውጤቶችም በአንድ የዕቅድ ዘመን በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የሚገደቡ ሳይሆኑ ድምር ውጤቶች ናቸው በማለትም ያክላል።

በዛው ላይም ፖሊሲው ተግባራዊ ከሆነበት ከ1985 ጀምሮ በፖሊሲው ከተቀመጡት ዓላማዎች አኳያ ሲታይ በሕዝብ ብዛት ዕድገት፣ በዘመናዊ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎች አጠቃቀም፣ አጠቃላይ የውልደት ምጣኔ፣ የጨቅላ ሕጻናት ሞት፣ የእናቶች ሞት ምጣኔ እና በሕይወት የመኖር አማካይ ዕድሜ ረገድ መሻሻሎች ታይተዋል። ለእነዚህ ውጤቶች መገኘትም የሥነ ሕዝብ ፕሮግራሞችና መርሐ ግብሮች አስተዋጽኦ አድርገዋል ይላል።

አቶ አበባው እሸቴ በኢትዮጵያ ፕላን ኮሚሽን የሥነ ሕዝብ ልማት ዳይሬክተር ናቸው። ፕላን ኮሚሽን ሥነ ሕዝብን በተመለከተ የፖሊሲ አፈጻጸም መከታተልና ማስተባበር ላይ እንደሚሠራ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ‹‹ፖሊሲው ከወጣ ከ25 ዓመት በላይ ሆኖታል። አሁን አዳዲስ መካተት ያለባቸው ነገሮች መጥተዋል። በቅርቡ በተሠራ የዳሰሳ ጥናት እንደ ምክረ ሐሳብ የወጣው ነጥብም ፖሊሲው መከለስ አለበት የሚል ነው›› ሲሉ ተናግረዋል።

ፖሊሲው ምንም እንኳ ውጤታማ የሆነበት ጉዳዮች ቢኖሩም፣ እንዲከለስ ያስገደዱ ነጥቦች ጥቂት አይደሉም። አበባው ከጠቀሱት መካከል እንኳ፣ አዳዲስና ጊዜ ያመጣቸው ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው፣ እስከ 2015 ተብለው የታቀዱን ጊዜ ያለፈባቸው አካሄዶች አሉ። ለምሳሌም የእናቶችና ሕጻናት ሞት እንዲሁም የቤተሰብ እቅድ አጠቃቀም ላይ ያሉ ግቦች የጊዜ ገደባቸው እስከ 2015 ሲሆን መከለስና መታየት ነበረባቸው።

ከዛ ባሻገር ታድያ የኢትዮጵያ ሥነ ሕዝብ ፖሊሲ እንደተባለው የልጅ ብዛትን አይወስንም። ‹‹ይሁንና በተዘዋዋሪ መንገድ ሴቶችን በማስተማር፣ ሴቶች ወሊድ መቆጣጠሪያ ሲፈልጉ እንዲጠቀሙ ተደራሽ ማድረግ ላይ ነው እየተሠራ ያለው። ነገር ግን አሁን ላይ የወጣቱ ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑ አንጻር የወሊድ መጠን በአጭር ጊዜ ይቀንሳል ተብሎ አይታሰብም።›› አበባው ያሉት ነው።

ፖሊሲን በተመለከተ የክትትልና የአፈጻጸም ችግር መኖሩን የሚያነሱት መሐመድ በበኩላቸው፤ እንደውም ይህን ውለድ ያንን አድርግ የሚል ፖሊሲ ማውጣትም አያስፈልገንም ይላሉ። ይልቁንም በከተማ ማስፋፋትና በትምህርት ተደራሽነት፣ ሴቶችን በማስተማርና የማኅብረሰብን ግንዛቤ በመለወጥ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ይላሉ። ‹‹ሰብአዊ መብት የሚነካ ፖሊሲ መጠቀም የለብንም። ቤተሰብና ሴቶችን ማስተማር ይሠራል። ምክንያቱም የተማሩ ሴቶችና ትምህርት ውስጥ የቆዩ የልጆቻቸው ብዛት ውስን ነው። ስለዚህ ትምህርት ማስፋት ነው ዋናው ቁምነገር›› ብለዋል።

ነገረ ሥነ ተዋልዶ

በቅርቡ የጤና እና ሥነ ሕዝብ ዳሰሳ ቅድመ ውጤት በጤና ሚኒስቴር ይፋ በተደረገበት ወቅት እንደተገለጸው፣ ዘመናዊ የወሊድ መቆጣጠሪያ ተጠቃሚዎች ቁጥር በ2016 ከነበረው 35 በመቶ በ2019 ወደ 41 በመቶ ከፍ ብሏል። ይህም ከሰባት ሚሊዮን በላይ ያገቡ ሴቶች ዘመናዊ የወሊድ መቆጣጠሪያ በመጠቀም ላይ እንደሚገኙ ማሳያ ነው ተብሏል።

ከዚህም የተነሳ ከ2.7 ሚሊዮን በላይ ያልተጠበቁ እርግዝናዎች፣ ከ600 ሺሕ በላይ ደኅንነቱ ያልተጠበቀ ውርጃ እና ከ 7 ሺሕ በላይ ከወሊድ ጋር የተያያዘ የእናቶችን ሞትን ማስቀረት ተችሏል።

የፕላን ኮሚሽኑ አበባው ሥነ ተዋልዶን በተመለከተ በዋናነት ጤና ጥበቃ በኩል ነው የሚሠራው ብለዋል። ኮሚሽኑም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ላይ አተኩሮ እንደሚሠራ ጠቅሰዋል። የሴቶችን ተሳትፎም አያይዘው ያነሱት አበባው፤ ‹‹በተለያየ ዘርፍ ለውጦች አሉ። ከፖሊሲው በኋላ አስቀድሞ ከነበሩ ተሻሽለው የታዩ ጉዳዮች አሉ። የሴቶች ተሳትፎም ተረጋግጧል ባይባልም ብዙ ለውጦች አሉ።›› ሲሉ አክለው ጠቅሰዋል።

የተለያዩ ዘገባዎችን ለመመልከት የሞከረችው አዲስ ማለዳ ባገኘችው የቁጥር መረጃ መሠረት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ 35 በመቶ ወይም አንድ ሦስተኛ የሚሆኑ ያገቡ ሴቶች የመጀመርያ ልጅ ከወለዱ በኋላ ቀጣዩ የመውለጃ ጊዜያቸው ቢያንስ በኹለት ዓመት እንዲራዘምላቸው ይፈልጋሉ። 24 በመቶ ያህሉ ያገቡ ሴቶች ደግሞ ተጨማሪ ልጅ መውለድ አይፈልጉም። የማእከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንደሚያሳየውም፣ በአጠቃላይ 58 በመቶ የሚሆኑ የቤተሰብ እቅድ መጠቀም ይፈልጋሉ።

መሐመድም ይህን አሃዝ ያነሳሉ። ይልቁንም ዕድሜያቸው በ20ዎቹ መጀመሪያ ያሉ በገጠር የሚኖሩ ሴቶች ትምህርት በሚገባ እንደማያገኙ ይገልጻሉ። ለዚህም አምስት ሴቶች መካከል አንዷ ብቻ የስምንተኛን፣ ከዐስሩ ሴቶች ደግሞ አንዷ የዐሥረኛን ክፍል ትምህርት ታጠናቅቃለች። ይህ የባለሥልጣኑ መረጃ ታድያ ብዙ ሴቶች አሁንም ትምህርት እንዳልደረሳቸው የሚያሳይ ነው።

ዘርፈ ብዙ ድክመቶች

በ2011 ይካሄዳል የተባለው የሕዝብና ቤት ቆጠራ ሲራዘም ቆይቶ በኋላ ጭራሽ ድምጹን አጥፍቶ ጠፍቷል። ይህም ከዚህም በኋላ ሥራዎች በግምት እንዲሁም በሙያዊ ትንበያዎች እንዲቀጥሉ ያስገድዳል። በዚህ መሠረት ስንቀጥል፤ አበባው እሸቴ የፖሊሲ ክለሳው በፖሊሲው ላይ የታዩ ክፍተቶችን እንዲሁም የተስተዋሉ የአፈጻጸም ግድፈትና ቸልታዎችን ያርማል ሲሉ ጠቅሰዋል። ሆኖም አሁንም ችግሮች እንዳሉ ነው ያነሱት።

‹‹ጉዳዩ ብዙ መሥሪያ ቤቶችን የሚመለከት በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ነው። ከዛ አንጻር ቅንጅት ለመፍጠር እንዲቻል ሥነ ሕዝብ ምክር ቤት ማቋቋም ያስፈልጋል። ያ የተባለ ቢሆንም እስከ አሁን ግን አልተቋቋመም›› ሲሉ ይጠቅሳሉ።

ታድያ ከዚህ በተጨማሪ በተለያየ ጊዜ የሚነሱ ችግሮች አሉ። ለምሳሌ በሥነ ሕዝብና ልማት ዙሪያ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ በቂ ችግር ፈች የጥናትና ምርምር ሥራዎች አልተከናወኑም፣ የሥነ ሕዝብ አስተባባሪ አካላትም የአደረጃት ወጥነት የላቸውም። እንዲሁም አበባው እንዳሉት ጉዳዩ ዘርፈ ብዙና ጥቂት ያልሆኑ ተቋማትን የሚመለከት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ በተቋማቱ መካከል ያለው ግንኙነት ደካማ መሆን እንደ ችግር የሚታይ ነው።

ሥነ ሕዝብ እና ሥነ ተዋልዶ በኢትዮጵያ አንጻር ዋና ዋና ግቦቹን የሚያስፈጽምባቸው ተቋማት በተለይ በትምህርትና ጤና ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ናቸው።

እነዚህ ሁሉ በተቋማትና በባለድርሻ አካላት ላይ ያሉ ችግሮች ሆነው፤ የኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ ሥነ ሕዝብ ትሩፋትን በተመለከተ ባቀረበው ዘገባ፣ በሕዝብ በኩል ያሉ ችግሮችን ይጠቅሳል። በሌላ አነጋገር ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት ሥነ ተዋልዶና ሥነ ሕዝብን በሚመለከት አስፈላጊውን ሁሉ ተደራሽ ቢያደርጉ ተብሎ ቢወሰድ፣ ሌሎች ችግሮችም አሉ ነው።

እነዚህንም ሲዘረዝር፤ ‹‹የቤተሰብ እቅድ አገልግሎቶችን ጥቅም እና አማራጮችን በአግባቡ አለመገንዘብ፣ የሴቶች በቤተሰብ ውስጥ ውሳኔ ሰጪነት ዝቅተኛ መሆን፤ የትዳር አጋር ተቃውሞ፣ የቤተሰብ ዕቅድን ከመጠቀም ጋር የተያያዙ ማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ተለምዶዎችና እምነቶች፣ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት የሚሰጥበት ስፍራ ሩቅ መሆን፣ በቋሚነት ለማቅረብ የሚያስችል ዘላቂ የሆነ የገንዘብ ድጋፍ አለመኖር፣ የሥነ ተዋልዶ ጤና እና የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ተግዳሮቶች ናቸው።›› በማለት ቃል በቃል አስቀምጧል።

ቁጥሮች ደግሞ ተከታዩን ይሉናል። እድሜያቸው በ15 እና 49 መካከል ካሉ ሴቶች ውስጥ ሥራ ያላቸው በ2003 38 በመቶ ነበሩ። ይህ ግን በ2008 ብሶበት ወደ 33 በመቶ ዝቅ ብሏል። በአንጻሩ የወንዶቹ ሲታይ፣ ቀድሞ ከነበረው መሻሻል ያሳየ ሲሆን፣ ይህም ከ85 በመቶ ወደ 88 በመቶ ማደግ ችሏል። ይህም በተለይ ከሴቶች አንጻር ሲታይ አልፎም ከጠቅላላው ሕዝብ 61 በመቶ በላይ የሚሸፍን የእድሜ ክልል እንደመሆኑም፤ ቁጥሮቹ ምን ያህል ዋጋ እንዳላቸው መገመት አይከብድም።

ምን በጀን?

በሳይንስ አካዳሚ ሐተታ መሠረት፤ ሥነ ተዋልዷዊና በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተደራሽነትን ማረጋገጥ ወሳኝ እንቅስቃሴ መሆን አለበት። እንዲሁም የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት በትምህርት ሲታገዝ የሴቶችን የመጀመሪያ ልጅ የመውለጃ ዕድሜ ከፍ ለማድረግ ይረዳልና በዛም ላይ ትኩረት ያስፈልጋል።

የሥነ ተዋልዶ ጤና እና የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት በመጠበቅ፣ እናቶች ጤናማ እርግዝና እንዲኖራቸው በማስቻልና በመንከባከብ፣ ታዳጊዎችም ጤናማ ሆነው ወደ ምርታማ ወጣትነት እንዲሸጋገሩ በማድረግ ሥነ ሕዝባዊ ትሩፋትን ለማሳካት ይረዳል፤ ሳይንስ አካዳሚ እንዳኖረው ገለጻ።

ደብረወርቅ ሕዝብን ማስተማር ከተቻለ ትልቅ ሀብት ነው ባይ ናቸው። ‹‹ማተኮር ያለብን ትምህርት ላይ ነው። ለዚህም አሁን ጀምሮ ማስተማር አለብን። ሥራ ፈትቶ ያለ ወጣት ብዙ ነው። የትምህርት ቤቶች ብዛት ላይ ብቻ ሳይሆን ጥራትም ሊታሰብበት ይገባል።›› ብለዋል።

በ2050 ጥሩ ቦታ ላይ ለመድረስ ሥራው የሚጀመረው አሁን ነው ያሉት ደብረወርቅ፣ 2020 ጀምሮ ይህ የሕዝብ ጭማሬ በጉልህ መስተዋሉ አይቀርምና እርምጃዎች በሚቀጥለው 10 ዓመት መውሰድ ወሳኝ ነው ብለዋል። ‹‹አሁን ነው ሥራ መስጠትና ማስተማር መጀመር ያለብን። የተማረ ከሆነ ብዛቱ ቢጨምርም መብላት ካለበት ወይም አምራች ካልሆነው ማኅበረሰብ ስለሚበልጥ ስጋት አይሆንም። ይህ የፊታችን 10 ዓመት ወሳኝ ነው። አለበለዚያ አሁን ባለንበት ነው የምንቀጥለው።›› በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አየነው በበኩላቸው ደግሞ ኢኮኖሚውም በፍጥነት በማያድግበት ሁኔታ የሕዝብ ብዛት በከፍተኛ ፍጥነት መጨመር ችግር ፈጣሪ እድገት ነው ያሉ ሲሆን፣ ከገጠሩ ጋር አብሮ ማደግ ከተቻለ ግን ይህ ስጋት አይኖርም ብለዋል። ‹‹ግን በግንባርህ ኑር ዓይነት፤ ከተማውን እያሳመሩ ገጠሩ ከተረሳ መባላት መምጣቱ አይቀርም። እና እዛ ሳንደርስ እንጠንቀቅ። አሁን አፋፉ ላይ ነው ያለነው።

ሁላችን የምንችለውን ካዋጣን ማሳካት እንችላለን። ካልሆነ እስከ መጨረሻው አዘቅት ውስጥ እንገባለን።›› ሲሉም አሳስበዋል። መሐመድ አሕመድ በተመሳሳይ መፍትሔ ያሉትን አስተያየት ሲሰጡ፤ ከኢኮኖሚና ከገቢ አንጻር ቃኝተውታል። ‹‹በእያንዳንዱ ቤተሰብ የሚጠራቀሙ ሳንቲሞች ናቸው አገር የሚለውጡት። በዚህ ደግሞ ኢንቬስትመንት ይመጣል።›› ይላሉ።

ይህም ከሥራ እድል ፈጠራ ጀምሮ ያሉት ፋይዳዎች ብዙ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ ኹለቱን በአንድ ማስኬድ ያሻል ሲሉ ይመክራሉ። እነሱም ሕዝብን በአግባቡ መምራት የሚቻልበትን መንገድ መፍጠር እና ከፍተኛ የሆነ የአገር ውስጥ ቁጠባን ማሳደግ ነው። ከውጪ አገራት የሚደረገውን ልገሳና ድጋፍ የሚያነሱት ባለሞያው፣ ‹‹እድገት በውጪ አገር በሚገኝ ነገር መመሥረት የለበትም።

ቁጠባ መኖር አለበት። በተለይ የአገር ውስጥ ቁጠባ ስርዓት።›› ሲሉ አሳስበዋል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ‹‹መደመር›› በተሰኘ መጽሐፋቸው፣ በ1999 የሕዝብ ቆጠራ ውጤት መሠረት፣ ወጣቱ የሥራ ኃይል 28 በመቶ ነበር ሲሉ ያወሳሉ። በዚህ ላይ እድሜያቸው ከሠላሳ በላይ የሆኑ ወጣቶች 61 በመቶ እንደሚሸፍኑም ይጠቅሳሉ።

ይህም በድምሩ የኢትዮጵያ አምራች ሕዝብ በከፍተኛ እድገት ላይ መሆኑን ያመላክታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህን ለመጠቀም የኢኮኖሚ ስልት መቀየስ አስፈላጊ ነው። በየዓመቱ የሚጨምረውን የሕዝብ ቁጥር ለመመገብ ዓመታዊ ግብርና ምርት እጅግ በጣም መጨመር አለበት። በሥራ እድል ረገድም የተመጣጠነ እድገት መኖር አለበት።

እስከ አሁን የተሞከሩ የተለያዩ የሥራ ፈጠራ ፕሮግራሞች የተወሰነ ውጤት ያስገኙ ቢሆንም፤ ቀጣይነት ያለው የሥራ እድል ለማስፋት ተስፋ የሚጣልባቸው አይደሉም። እናም የሥራ እድል ቅድሚያ ትኩረት ይፈልጋል ብለዋል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 64 ጥር 16 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here