ከ19 የፖለቲካ ፓርቲዎች አገራዊ ጥምረት ሊፈፅሙ ነው

0
798

ከ19 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያቀፈ ‹‹ትብብር ለህብረ ብሔር ፌደራሊዝም›› የሚል ስያሜ የሚሰባሰብ ቅንጅት በመመስረት ላይ መሆኑ ተገለፀ፡፡ የአራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ትብብር ለህብረ ብሔር ፌደራሊዝም የሚል ስያሜ የተሰጠው ጥምረት ለመመስረት የጥምረት ጥያቄያቸውን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስፈላጊ ሰነዶችን በሟሟለት ማቅረባቸውን ለአዲስ ማለዳ ስታወቁ ሲሆን በዚህ ጥምረት ስርም 15 ፓርቲዎች በመጪው ሁለት ሳምንት ውስጥ እንደሚካተቱ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

ለምርጫ ቦርድ በቀረበው የጥምረት ጥያቄ ያቀረቡት አባላት የአገው ብሔራዊ ሸንጎ፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር ፣ የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባርና ሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን ሌሎች በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረቱን ለመቀላቀል ፍላጎት ማሳየታቸው ተገልጿል፡፡ ኀዳር 26/2012 10 የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረሙ ሲሆን ከ 10 ቀናት በኋላ በሚጀመረው የመዋቅር ጥናት መሠረት ቢያንስ ትብብር እንደሚሆን እና ከተቻለ ግን ወደ ግንባር ወይም ወደ ውህደት ሊመጣ እንደሚችል ማስታወቃቸው ይታወሳል። በኢሊሊ ሆቴል ለትብብሩ ቅድመ ሁኔታ ወይም የፍላጎት መግለጫ ይሆን ዘንድ በተፈረመው ሰነድ ላይ በመመርኮዝ ሦስት ኮሚቴዎች ከሁሉም ፓርቲዎች ተመርጠው ሶስት ኮመቴዎች ተዋቅረው ነበር የኮሚቴ የትብብሩን መዋቅር የሚያጠና፣ የህዝብ ግኑኙነት ጉዳዮችን የሚከታታል እና ስለ መጪው ምርጫ የሚያጠና አንደነበሩም ለአዲስ ማለዳ ገልጸው ነበር፡፡

ከኦነግ በተጨማሪም የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ)፣ የአፋር ሕዝቦች ነፃነት ፓርቲ፣ የሲዳማ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ፣ የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ፣ የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የአገው አገር አቀፍ ሸንጎ፣ የሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የካፋ አረንጓዴ ፓርቲ ትብብሩን መሥረተዋል። ይህንንም መሰረት በማድረግ በፌዳራሊዝም ስርሃት የሚያምኑ፣ ኢትዮጵያ በሰላም እና ዲሞክራሲዊ መንገድ እንድትመራ የሚፈልጉ እንዲሁም ምርጫው ፍትሃዊ እና ግልፅ እንዲሆን የሚፈልጉ ፓርቲዎች ጥምረቱን መቀላቀል እንደሚችሉ የኦብነግ የውጪ ግኑኙነት ሃላፊ እና የትብብሩ ስራ አስፈፃሚ አባል ሀሰን ሙሃሚን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ጊዜያችንን በአግባቡ ለመጠቀም አራት ፓርቲዎች የመግባቢያ ስምምነቱን አልፈን ቅንጅት ለመመስረት ተስማምተን ጥያቄአችንን ለምርጫ ቦርድ አስገብተናል›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

ከ 19 የሚደርሱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ቅንጅቱን በመቀላቀል እንድ ትልቅ በሔራዊ ጥምረት በመመስረት በቀጣይ ኹለት ሳምንታት ውስጥም ይፋ እንደሚሆን ሃሰን ተናግረዋል፡፡ ጥምረቱ በመርህ ደረጃ ተመሳሳይነት ያላቸውን ፓርቲዎች ያቀፈ መሆኑን የገለፁት ቀጂላ መርዳሳ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የህዝብ ግኑኙነት ሀላፊ ናቸው፡፡ ፓርቲዎቹ በቀጣዩ አካባቢያዊ እና አገራዊ ምርጫ ላይ በጋራ ለመሳተፍ፣ ሀብትን እና የሰው ኃይልን በጋራ ለመጠቀም፣ ምርጫ ቅስቀሳን ባገራ እና ለማድረግ በምርጫውም መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ድምፅ ከተገኘ በጋራ መንግስት መመስረት የሚሉ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ላይ በመስማማት ቅንጅት ለመፈፀም በሂደት ላይ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም ጥምረቱን ወደ ግንባር እና ውህደት ለማሳደግ የሚያስችል ስምምነት ላይ ሊደረስ እንደሚችል ገልፀው ሌሎች በርካታ ፓርቲዎች የጥምረቱ አባል ለመሆን እንቅስቀሴዎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ከነዚህ ውስጥም የአፋር ሕዝብ ነፃነት ፓርቲ ፣የካፋ አረንጓዴ ፓርቲ፣ የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እንደሚገኙበት ተናግረዋል፡፡ የፓርቲዎች ተቀራርቦ መስራት በድምጽ ላይ የሚያመጣው ለውጥ ይኖራል ያሉት ቀጂላ በጋራ ተፅህኖ ለመፍጠር ይረዳል፤ ፓርቲዎች አንድ መሆን በመካከላቸው ያለ ጥላቻን ለማስወገድ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶችን ለማስቀረት ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ አስራ ሁለት አባላት ያሉት የስራ አስፈፃሚ አባላትን የመረጠው ቅንጅቱ ከኦነግ ዳውድ ኢብሳ ሊቀ መንበር፣ ከኦብነግ አብዱረህማን መህዲ ምክትል ሊቀ መንበር እንዲሁም አላምረው ይርዳው ከአገው ብሔራዊ ሸንጎ ጸሀፊ ሆነው መመረጣቸውን አስታውቀዋል፡፡ ከምርጫው በተጨማሪም በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ፓርቲዎች የጋራ መግባባት በመፍጠር አብሮ ለመስራት እና በመካካለቸው ያሉ ልዩነቶችንም ለማጥብብ ቅንጅቱ ይጠቅማል ያሉ ሲሆን ከ 11 በላይ የሚሆኑ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅንጅቱን ለመቀላቀል ጥያቄ አቅርበዋል ብለዋል፡፡

ቅንጅቱን በሚመለከት በተደረገው ጉባኤ ላይ የአራቱ ፓርቲዎች አመራሮች ብቻ መገኘታቸው የተገለፀ ሲሆን አሁን ለምርጫ ቦርድ ከቀረበ በኋላ የሚመጡ ደብዳቤዎችን በሌላ መንገድ ለምርጫ ቦርድ የማቅረብ ሀሳብ መኖሩን አብራርተዋል፡፡ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳውንም በሚመለከት ገና ያለፀደቀ ነው እኛ የሚጠበቅብንን መስፈርቶች እና ሰነዶች አሟልተን አቅርበናል ሌለው ስራ ምርጫ ቦርዱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ታኅሣሥ 24/2012 በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ብሔራዊ ፓርቲ (ኦብፓ) ከፈረሙት የጥምረት ስምምነት ጋር ልዩነት የለውም በኹለት ሳመንታት ውስጥም መድረክን ጨምሮ 19 የሚጠጉ ሌሎች ፓርቲዎች ጋር በመሆን መግለጫ ለመስጠት በዝግጅት ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ቀጂላ መርዳሳ በበኩላቸው ሶስቱ ፓርቲዎች በኦሮሚያ ክልል ውስጥ አብረው ለመስራት ነው ከስምምነት የደረሱት ወደ አንድ ጥምረት ሊመጡ የሚችሉበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል ያንን ግን አሁን ላይ ለመግለፅ ጊዜው አይደለም ስልጣኑም የለኝም ሲሉ ገልፀዋል፡፡ የኦፌኮ ሊቀ መንበር እና መድረክ የተሰነው ቅንጅት መሪ ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና በበኩላቸው ‹‹መድረክ እንደመድረክ እራሱን ችሎ ይቀጥላል ሆኖም ግን ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ በሚያስማሙን ጉዳዮች ላይ የማንሰራበት ምክኒያት›› የለም ሲሉ ይናገራሉ፡፡ በ ምርጫ 97 ወቅትም እንዚህ አይነት ጥምረቶች ነበሩ ለመበታታናቸው ምክኒያት ግን በወቅቱ መንግስት በፓርቲዎቹ ላይ ዘመቻ ማካሄዱ ነው በወቅቱም አብዛኛዎቹ የፓርቲ አመራሮች መታሰር ለቅንጅታቸው መፍረስ ምክኒያት እንደነበር መረራ አውስተዋል፡፡

የዓለማቀፍ የሕገ መንግሥት የምርምር ኢንስቲቱት (አይዲኢኤ) አርታኢ የሆኑት አደም ካሴ (ዶ/ር) እንደሚሉት የፓርቲዎች መጣመር በተተበታታነ መልኩ ከሚቀርቡ ይልቅ በጋራ መቅረባቸው ድምፅ እንዳይበታተን ለማድረግ እንደሚራዳቸው ያብራራሉ፡፡ ህዝቡ በፓርቲዎቹ የምርጫ ምልክት እንዳይደናገር ያደርጋል የሚሉት አደም አክለውም ጥቅሙ ለተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ብቻ ሳይሆን ምርጫውንም ለሚመራው አካል ነው የምርጫ ወረቀቶችን ማዘጋጀትንን በሚመለከት እንዲሁም ተወዳዳሪዎችን ከመመዝገብ አንፃር ያለውን ጫና ለመቀነስ ያግዘዋል ሲሉ የፖርቲዎች መጣመር ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ገልፀዋል፡፡

የፓርቲዎች በኹለት መሰረታዊ ምክኒያቶች ሊጣመሩ ይችላሉ የሚሉት አደም አንደኛው ፕሮግራም መመሳሰል ነው ኹለተኛው ደግሞ የገዢውን ፓርቲ ጥንካሬ በመመልከት የሚፈፀም እንደሆነ ያብራራሉ ሆኖም ፖለቲካ፣ በታሪክ፣ እንዲሁም በግለሰቦች አመለካከት እንደሚመራ ጠቅሰዋል፡፡ አክለውም ጥምረት መመስረት በተለይም በአንድ አይነት አካባቢ ላይ ለሚወዳደሩ ፓርቲዎች የተሻለ ጥቅም ይሰጣል ተቃዋሚ ፓርቲዎች እርስ በእርስ ከመጣመር በተጨማሪ በተለይም በብሔራዊ ነን የሚሉ ፓርቲዎች ከገዢው ፓርቲ ጋር የሚሠሩበት አጋጣሚ ካለ አብረው ቢሰሩ ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ ይላሉ፡ ፡

‹‹በስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ አቅም ስላለው የምርጫ ቅስቀሳዎችንም ሆነ ሌሎች ጉዳዮችን በቀላሉ ሊፈፅም ይችላል›› የሚሉት አደም ተቃዋሚ ፓርቲዎችም መጣመራቸው ያላቸውን ሀብት በጋራ እንዲጠቀሙ እንደሚያደርግም አንስተዋል በምክር ቤትም ተሸለ የመቀመጫ ቁጥር ለማግኘት ይረዳቸዋል ብለዋል፡፡ ‹‹የፓርቲዎችን በተለያዩ ጥምረቶች ውስጥ መግባታቸው እንደዚህ አይነት የምርጫ ፉክክሮች በኢትዮጵያ አዲስ መሆናቸውን የሚያመላክት ነው፤ ፓርቲዎቹም ከማን ጋር እንሰራለን በሚለው ላይ ለመወሰን የሚያደረጉትን ጥረት የሚያመላክት ነው›› ሲሉ አደም አብራርተዋል፡፡ ሆኖም ግን ከምርጫ በኋላ ለሚነሱ የንብረት እና ሌሎች መሰል ጥያቄዎች ምክኒያት ሊሆን ይችላል የሚሉት አደም የምርጫ ህጉ ግን አንድ ፓርቲ ከአንድ በላይ ጥምረት ውስጥ መገኘትን እንደማይከለክልም ተናግረዋል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 64 ጥር 16 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here