ዳሰሳ ዘ ማለዳ (ጥር 19፤ 2012)

0
782

የህዳሴው ግድብ ውርስ አገኘ

ኃይሉ ታደሰ የተባሉ ግለሰብ ህይወታቸው ከማለፉ በፊት ካላቸው ሃብት አስር በመቶው ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንዲሰጥ ተናዘው ማረፋቸውን ተከትሎ ግድቡ ውርስ አገኘ።  በዚህም መሰረት ያላቸው ንብረት ተሽጦ 124 ሺህ ብር ለሕዳሴ ግድብ ገቢ መደረጉን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ  ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ሃይሉ አብርሃም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። (አዲስ ማለዳ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ የተፈጸመውን እገታ የሚያወግዙ ሰላዊ ሰልፎች ተካሄዱ። በደንቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲ ሲማሩ የነበሩና የታገቱ ተማሪዎችን በተመለከተ የተደረገው ሰለማዊ ሰልፍ  መንግስት ግልፅ መረጃ እንዲሰጥ፣ በአጋቾች ላይም እርምጃ በመውሰድ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የሚጠይቁ ሲሆኑ ሰልፉም  በባህርዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ወልዲያ፣ በደብረ ብርሃንና በሌሎች የክልሉ ከተሞች ተካሂደዋል። (የአማራ ብዙሃ መገናኛ ድርጅት)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል በሚል የተጠረጠሩ አራት ሰዎች በቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ምርመራ ከተደረገላቸው በኋላ ነፃ ሆነው መገኘታቸውን እና የደም ናሙናቸውም ወደ ደቡብ አፍሪካ ለተጨማሪ ምርመራ መላኩን የጤና ጥበቃ ሚንስትር ዲኤታ ሊያ ታደሰ(ዶ/ር) በቲውተር ገጻቸው ላይ አስታወቁ ። ቫይረሱ በተከሰተበት የቻይና ዉሃን ግዛት ተማሪ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ከተጠረጠሩት መሃል መሆናቸውንም ሊያ ገልጸዋል። በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የመንገደኞች የኮሮና ቫይረስ ለመለየት የሰውነት ሙቀት መለካት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን 22ሺህ ሰዎች ሙቀት መለካቱም ተነግሯል። (ቢቢሲ አማርኛ)

 

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

ከደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ለደህንነታቸው በመስጋት ወደ ቤተሰቦቻቸው እየተመለሱ ሳሉ ማንነታቸው ባልታወቀ ሰዎች የታገቱ ተማሪዎችን ለማስለቀቅ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ብርሃኑ ፀጋዬ ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቁ። የተቋቋመዉ ኮሚቴ ከክልሉና ከፌደራል አካላትን ያካተተ እንደሆነ እና የታገቱትን ተማሪዎች ከማስመለስ ባሻገር ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ እንደሚሰራም ተናግረዋል። (አዲሰ ማለዳ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት  ከጉዲና ኩምሳ ፋንዴሽን ጋር በመተባበር በሰሜን ሸዋ ዞን ውጫሌ ወረዳ ልዩ ስሙ ጃቲ በሚባል አካባቢ ያስገነባውን የኢፋ ሰላሌ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በዛሬው እለት አስመረቀ። ትምህርት ቤቱ  14 ሚሊዮን ብር ገደማ ወጪ የተደረገበት ሲሆን  በጽህፈት ቤቱ ተሰርተው ከተመረቁ አምስት ትምህርት ቤቶች  መካከል አንዱ ነው። በምርቃቱ ወቅት ቀዳማዊት እመቤት ዝነሽ ታያቸው ለፋውንዴሽኑ እንዲሁም በግንባታው ሥራ ድርሻ ለነበራቸው የምሥክር ወረቀት የሰጡ ሲሆን ‹‹እንደራሳችሁ ንብረት እድትይዙ አደራ እላለሁ፤ በመንግስት ሳይሆን በራሳችሁ ብር የተሠራ ነው›› ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። ትምህርት ቤቱን ለመገንባት በቀዳማዊት  እመቤት  የመሰረት ድንጋይ ሚያዚያ 3/2011 መጣሉ ይታወሳል (አዲስ ማለዳ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

በጉራጌ ዞን በእነሞርና ኤኅር እንዲሁም  በአንዳንድ ቀበሌዎች ላይ የአንበጣ መንጋ ተከስቷል።  የአንበጣ መንጋው  በፍጥነት እየተዛመተ በመሆኑም  ህብረተሰቡ መንጋው በሚገኝበት አካባቢ ጭስ በማስጨስ፣ከፍተኛ ድምፅ ያላቸውን እንደ ባሕላዊ የትንፋሽ መሳሪያዎችን በማስጮህ እና ሌሎች ባህላዊ መንገዶችን በመከተል እዲከላከል ከዞኑ የአደጋ መከላከል ዝግጅት  ጥሪ ቀርቦለታል። (ኢትዮ ኤፍ ኤም)

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here