ወደ ደንቢ ዶሎ የተጓዘው ልዑክ ከእገታ የተለቀቁትን ተማሪዎች በአካል ማግኘት አልቻለም

0
621

ከደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ በጋምቤላ ክልል አድርገው ወደ ቤተሰቦቻቸው በመመለስ ላይ ሳሉ ታግተው ከነበሩ እና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ንጉሡ ጥላሁን ጥር ኹለት ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተለቀዋል ካሏቸው ተማሪዎች መካከል፣ ባለፉት ኹለት ቀናት ወደ ዩኒቨርሲቲው በተደረገው ጉዞ በአካል ማግኘት እንዳልተቻለ ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።

በተያዘው የትምህርት ዓመት በደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተመድበው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የነበሩ 800 የአማራ ክልል ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ግቢውን ለቀው በመውጣታቸው ምክንያት፣ በመከላከያ ሠራዊት ከአጋቾች እጅ ወጥተው ወደ ዩኒቨርሲቲው ተመልሰው የነበሩ ተማሪዎችን ለማግኘት እንዳልተቻለ አረጋግጠዋል።

‹‹እስከ አሁን ድረስ ልጆቻችን ጠፍተዋል ብለው ያመለከቱ እና በርግጥም ተማሪዎቹ በደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተመድበው የነበሩ መሆናቸውን ያረጋገጥነው ስምንት ብቻ ናቸው። ለዚህም የፈተናዎች ድርጅትን እና የዩኒቨርሲቲውን የመረጃ ቋት ተጠቅመን 12ቱ በደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሆናቸውን አረጋግጠናል›› ሲሉም በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

አክለውም በማኅበራዊ ሚዲያ ሥማቸው ሲዘዋወር ከነበሩ 17 ተማሪዎች መካከል አምስቱን በዩኒቨርሲቲውም ሆነ በፈተናዎች ኤጀንሲ የመረጃ ቋት ውስጥ ማግኘት ያለመቻሉን እና ይህም ማጣራት ወደኋላ ያሉ ዓመታትን ጭምር ያካተተ እንደነበርም ተናግረዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ሪፖርት በተመለከተም ከአዲስ ማለዳ ጥያቄ የቀረበላቸው የሥራ ኃላፊዎች አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበው ‹‹በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች መንግሥት በወሰደው እርምጃ እፎይታ እንደተሰማቸው በአካባቢው ተገኝተን አረጋግጠናል›› ሲሉ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰዓት የዩኒቨርሲቲው ተማሪ ናቸው የተባሉ እና በማኅበራዊ ሚዲያ ሥማቸው ሲዘዋወር ከነበሩ ተማሪዎች መካከል 12ቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ መሆናቸው፣ ኹለቱ በቤተሰብ ማመልከቻ ብቻ የተፈለጉ ተማሪዎችና አምስቱ በዩኒቨርሰቲው ተማሪ ያለመሆናቸው የተረጋገጠውን ጨምሮ የ 19 ተማሪዎች ፍለጋ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ለማወቅ ተችሏል።

ከእገታው አምልጣ የነበረቸው የዩኒቨርሲቲው ተማሪ አስመራ ሹምዬ ለሚዲያ ሆነ ለፀጥታ ኃይሎች ስትሰጥ የነበረው መረጃ የተለያዩ መፋለሶች የነበረበት ነው ሲሉም የትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በመግለጫው ላይ ተናግረዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here