ገንዘብ በማተም የተፈረደባቸው ግለሰብ ቅጣት ተቀነሰላቸው

0
536

ሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን፣ ቼኮችን፣ የክልል እና የፌዴራል መንግሥት ሰነዶችን፣ የተለያዩ የትምህርት ማስረጃዎን እና የመንጃ ፈቃዶችን በማዘጋጀት ተከሰው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ15 ዓመት ፅኑ እስራት እና 3000 ብር የገንዘብ መቀጮ የወሰነባቸውን ስንታየሁ ጌታነህን፣ የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በይግባኝ ወደ ስምንት ዓመት ፅኑ እስራት እና 2000 ብር የገንዘብ መቀጮ አቀለላለቸው።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 እና የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ የተለያዩ ክፍሎችን በመተላለፍ ሐሰተኛ የብር ኖቶችን፣ ቼኮችን፣ የክልል እና የፌዴራል መንግሥት ሰነዶችን፣ የተለያዩ የትምህርት ማስረጃዎን እና የመንጃ ፈቃዶችን በማዘጋጀት በአራት ክሶች የካቲት 15 እና 19 ቀን 2010 የቅጣት ውሳኔ የሰጠባቸው አንደኛ ተከሳሽ ሳምሶን ስማቸውን እና ሁለተኛ ተከሳሽ ስንታየሁ ጌትነትን ነበር።
ሁለተኛ ተከሳሽ ስንታየሁ ጌትነት የ15 አመት ፅኑ እስራት እና 3000 ብር የገንዘብ መቀጮ የተወሰነባቸው ሲሆን በዚ ቅር በመሰኘት አንደኛ ተከሳሽ ላደረጉት ድርጊት ሁሉ እኔ ተጠያቂ ልሆን አይገባኝም ሲሉ ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠይቀዋል።
ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የውሳኔ መዝገብ ለመረዳት እንደሚቻለው ስንታየሁ ጌታነህ ለአንደኛ ተከሳሽ የቀለም ኅትመት መሣሪያ መግዛታቸው እና የተለያዩ የውጪ አገራት የገንዘብ ኖቶችም እንደተገኙባቸው ምስክሮች አስረድተዋል። የአማራ ክልል የሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ አግባብነት ያለው በመሆኑ ሊፀና ይገባል ሲል ተከራክሯል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም በሥር ፍርድ ቤት የቀረቡ ምስክሮችን እና የሰነድ ማስረጃዎችን ከመረመረ በኋላ ስንታየሁ ጌታነህ ላይ የቀረቡት ማስረጃዎች ግለሰቡ አንደኛ ተከሳሽን በወንጀል ድርጊት መርዳቱን እንጂ የወንጀል አድራጊነቱን አያሳዩም በሚል የጥፋተኝነት ውሳኔው ከዋና ወንጀል አድራጊነት ወደ አባሪነት እንዲሻሻል ወስኗል።
የቅጣት ውሳኔዎቹም በዚህ መሠረት መስተካከል እንደሚገባቸው የገለጸው ፍርድ ቤቱ ኅዳር 19 ቀን 2011 በዋለው ችሎት ስንታየሁ ጌታነህ ላይ የስምንት ዓመት ፅኑ እስራት እና 2000 ብር የገንዘብ መቀጮ ወስኖባቸዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 4 ኅዳር 29 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here