መርስክ የኢትዮጵያን የባሕር አገልግሎት ድርሻ ለመግዛት አቅዷል

0
583

‹ኤፒ ሞለር መርስክ› በመባል የሚታወቀው መቀመጫውን ዴንማርክ ያደረገ ኩባንያ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅትን ድርሻ ለመግዛት አቅዷል። በኢትዮጵያ የመርስክ ወኪል የፍሬተርስ ኢንተርናሽናል ኃ/የተ/የግ/ማ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑ ዳንኤል ዘሚካኤል እንደገለጹት ከሆነ ኤፒ ሞለር ካፒታል በሎጂስቲክስ ዘርፉ ላይ ለመሠማራት በቂ ገንዘብ፣ ዕውቀትና ልምድ ስላለው በዘርፉ ለመሠማራት ያለውን ፍላጎት ለኢትዮጵያ ኢንቬስትመንት ኮሚሽነር ፍፁም አረጋ ገልጿል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ፍፁም አረጋ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው “ኢትዮጵያ የማምረቻ ኢንዱስትሪ ማዕከል ለመሆን ወስና እየሠራች ትገኛለች። ሆኖም ውድና ቀልጣፋ ያልሆነ የትራንስፖርት እና የሎጂስቲክስ ዘርፍ ስላለን በዓለም ገበያ መወዳደር እየቻልን አለመሆናችንን በማየት በቅርቡ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት የሎጂስቲክስ ዘርፉ በከፊል ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት እንዲሆን ተወስኗል። ይህንን በማየት ‹ኤፒ ሞለር መርስክ› የተባሉ ኩባንያዎች በአገራችን ተገኝተው ጥናት ማድረግ ጀምረዋል። በሎጂስቲክስ ዘርፉ የተሠማሩ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የሚመጡትን የዘመነና ተወዳዳሪ ሊሆን የሚችል ዕድል በብቃት በመጠቀም አብረው እንዲያድጉ እንመክራለን’’ በማለት ገልጸው እንደነበር ይታወሳል።
ዳንኤል ኤፒ ሞለር መርስክ አንድ ቢሊዮን ዶላር (303 ቢሊዮን ብር) ገንዘብ በአፍሪካ ለተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ለማዋል ማዘጋጀቱን ገልጸው፣ ኩባንያው ይህ ገንዘብ ወደ ኢዮጵያ በኢንቬስትመንት መልክ እንዲገባ ፍላጎት አለው ብለዋል። በመሆኑም ድርጅቱ የደረቅ ወደብ ልማትና የጭነት ጣቢያዎች ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ ይሠራል። እነዚህ ግንባታዎች ከአምስት እስከ ዐሥር ዓመት የሚፈጁ ሲሆን የግምጃ ቤት ግንባታን ጨምሮ የደረቅ ወደብ አገልግሎትን ለማቀላጠፍ የሚረዱ ማሽኖችን ግንባታ ይጨምራል። ዳንኤል እንደሚሉት ከሆነ ኤፒ ሞለር የደረቅ ወደብ ግንባታውን ካጠናቀቀ በኋላ ለመንግሥት ወይንም ለሌላ ተገቢ አካል በሕግ አግባብ ወደቡን የመሸጥ ዕቅድ ነው ያለው። በአሁኑ ወቅት በጥናት ላይ ያለው ኩባንያው ጥናቱ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቆ ወደ መዋዕለ ንዋይ ፍሰት የሚገባ ከሆነ የደረቅ ወደቡንም ሆነ የጭነት ጣቢያው ግንባታ ሲጠናቀቅ ለተለያዩ አምራች ድርጅቶች ዕቃን የማሸግ፣ የመጋዘን አገልግሎት የመስጠት፣ የተለያዩ አምራች ድርጅቶችን ተመሳሳይ ምርት በአንድ ላይ አሽጎ (consolidation) ወደ ውጪ መላክና የመሳሰሉትን አገልግሎቶች ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያዊያን በባለቤትነት በሚመራ አንድ የሎጂስቲክስ ድርጅት ውስጥ በማርኬቲን ዳይሬክተርነት የሚሠሩ ግለሰብ እንደገለጹልን የውጪ ባለሀብቶች በሎጂስቲክስ ዘርፍ እንዲሳተፉ መንግሥት መፍቀዱ ኢትዮጵያዊ ባለሀብቶችን ይጎዳል ይላሉ። ምንም እንኳን የሎጂስቲክስ ዘርፉን ለማቀላጠፍ በቂ ዕውቀት ቢኖረንም ከውጪ ኩባንያዎች ጋር ለመወዳደር የሚያበቃ የገንዘብ አቅም ስለሌለን መንግሥት ይህን ዘርፍ ለውጪ አገር ባለሀብቶች ክፍት በማድረጉ አልስማማም ብለዋል።
ዳንኤል በዚህ ሐሳብ አይስማሙም። በመሆኑም የኢትዮጵያ የንግድ እንቅስቃሴ በግለሰብ ድርጅቶች ጥቅም ላይ ሳይሆን በአገር ደረጃ በሚሰጠው ጥቅም ላይ መሠረት ማድረግ አለበት። አሁን ያሉት የሎጂስቲክን ድርጅቶች ዕውቀት ቢኖራቸውም የተሻለ አገልግሎት የሚሰጡበት የገንዘብ አቅም ስለሌላቸው ተገቢውን አገልግሎት አየሰጡ አይደለም። ስለዚህ እንደ ‹ኤፒ ሞለር› ዓይነት የገንዘብ አቅም፣ እውቀት፣ ልምድና ቴክኖሎጂ ያላቸው የሎጂስቲክስ ተቋማት ወደዘርፉ መግባት ለኢትዮጵያ ዕድገት የራሱን በጎ አስተዋጾ ያበረክታል ብለዋል።
‹ኤፒ ሞለር› መቀመጫውን በዴንማርክ ያደረገ ኩባንያ ሲሆን በሥሩ ባሉና እራሳቸውን ችለው በሚቀሳቀሱ ድርጅቶች አማካኝነት በሎጂስቲክስ፣ ትራንስፖርትና ኢነርጂ ዘርፍ ላይ ተሠማርቶ ይገኛል። ኩባንያው በ130 አገራት ቢሮ ከፍቶ የሚንቀሳቀስ ሲሆን ከ88,000 በላይ ሠራተኞች አሉት። ዓመታዊ ገቢውም 6.7 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ይገመታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 4 ኅዳር 29 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here