በስንታየሁ አባተ
ባለፉት ቀናት በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች የተካሔዱት ሰልፎች ዓላማ ሞትና መፈናቀል እንዲቆም እና በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሰቀቃሱ የፖለቲካ ኃይሎች ለሕዝብ ደኅንነት በጋራ እንዲሠሩ የሚጠየቁ ቢሆኑም፥ ሰልፉን በመንግሥት ላይ የተቀሰቀሰ አመፅ ለማስመሰል የሞከሩ ወገኖች አልተሳካላቸውም ተባለ።
ኅዳር 18 በኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዋሳኝ በሆነው የምሥራቅ ወለጋ ዞን ሊሙ ወረዳ ልዩ ሥሙ አርቁምቤ አካባቢ በደረሰ ጥቃት የኦሮሚያ ክልል ፖሊሶችን ጨምሮ በርካታ ንፁኃን ዜጎች ሕይወት ስለመጥፋቱ መገለጹ ይታወሳል። የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ባወጣው መረጃ በርካታ ሰዎች መሞታቸውን ጠቅሶ ቁጥሩ በቅርቡ ይገለጻል ይበል እንጂ እስካሁን ይፋ አልተደረገም። ይሁንና የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረንስ (ኦፌኮ) ባወጣው መግለጫ “በኦሮሞና በቤነሻንጉል ጉሙዝ ድንበሮች አከባቢ በተጫረው ግጭት ሰበብ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሞተዋል” ብሏል።
የክልሉ መንግሥት መግለጫ በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ ያጋጠመው የፀጥታ ችግር እንዲቆም የኦሮሚያ ክልል ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ጋር እየሠራ ቢሆንም የፀጥታ ችግር እየፈጠሩ ያሉ አካላት በተቀናጀ መንገድ በሥልጠና እና በተለያየ ጦር መሣሪያ በመደገፍ በሕዝቡ ላይ ጦርነት የከፈቱ በመሆኑ ችግሩ በአጭር አልቆመም ብሏል።
በተለያዩ አካባቢዎች ከሚያጋጥሙ የፀጥታ ችግር ጀርባ ያሉት “ለዓመታት ሕዝቡን ሲያሰቃዩ የነበሩና አሁን በአገሪቱ በተጀመረው ለውጥ መንገድ የተዘጋባቸው እንደሆኑ” ያሚያምነው ክልሉ “ወደ ሥልጣን ተመልሰው ሕዝቡን ሊያሰቃዩ እየተጣጣሩ ያሉ ጠላቶች እጅ አለበት” ይላል።
በተያያዘም የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ካቢኔ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በመከረበት የኅዳር 25 ስብሰባ በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ባጋጠመው የፀጥታ ችግር ላይ መክሯል ተብሏል። እየተፈፀሙ ያሉ ግድያዎች እንዲቆሙና ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሰዎቸ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ለመሥራት ቃል መግባቱንም ባወጣው መግለጫ ማመልክቱ ይታወሳል። በዚህም ሕዝብን ለማረጋጋት ለሚሠሩ የፀጥታ ኃይሎች ድጋፍ እንደሚደረግ መግለጹ በመግለጫው ተጠቅሷል።
ሰሞኑን ለስብሰባ የተቀመጠው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (ቤጉሕዴፓ) ከስብሰባው በፊት በሰጠው መግለጫ በክልሉ ፀጥታና መረጋጋት እንዲርቅ በማድረግ እጃቸው ያለበትን የሥራ ኃላፊዎች ለሕግ እንደሚያቀርብ አሳውቆ ነበር።
ያጋጠመውን የፀጥታ ችግር መቅረፍ እንዲቻል በሁለቱ ክልሎች ሥምምነት መሠረት፣ የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት በኅዳር 21/2011 ውሎው የፌደራል የፀጥታ አካላት ችግር ባጋጠማቸው አካባቢዎች ጣልቃ እንዲገባ መወሰኑ ይታወሳል።
ይህ ተከትሎ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር እየወሉ ነው የተባለ ሲሆን፣ የኦሮሚያ ኮሙዩኒኬሽን ተጠርጣሪዎችን መያዙ እንደሚቀጥል በመጥቀስ እስካሁን ከ200 በላይ ተጠርጣዎቸ ስለመያዛቸው መግለጫ አውጥቷል። የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ ኅዳር 26/2011 እንዳሳወቀው ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኩል የተጠረጠሩ አምስት ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ተይዘዋል። ከተጠርጣዎቹ መካከልም የክልሉ አስተዳደርና ፀጥታ ጉዳይ ምክትል ኃላፊና የቀድሞው የአሶሳ ከተማ ከንቲባ እንደሚገኙበት ተነግሯል።
ሰሞነኛውን ግጭትና የሕይወት ሕልፈት ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል አዳማ፣ አምቦ፣ ጊምቢ፣ ሆለታ፣ ቡራዩ፣ ባኮ፣ መቱና ሌሎቸም ከተሞች ሠላማዊ ሰልፎች ተደርገዋል። የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አዲሱ አረጋ በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ሰልፎቹ “በለውጡ ተቃራኒ ኃይሎች አቀናባሪነት እየተፈፀመ ያለውን የዜጎቻችንን ግድያ፣ መፈናቀል እና ሰብኣዊ ቀውስ በአስቸኳይ እንዲቆም፣ መንግሥት የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ የዜጎችን ደህንነት ለማስከበር ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ፣ ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ የዜጎችን ሰብኣዊ መብት ሲጥሱ የነበሩ አካላት በሕግ ቁጥጥር ሥር የማዋል ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል መንግሥት ላይ ጫና ለመፍጠር፣ ለውጡን በማፋጠን የሕዝባችንን የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ እና ማኅበራዊ ተጠቃሚነት በተሟላ መልኩ እንዲረጋገጥ መንግሥት የጀመራችውን የለውጥ እንቅስቃሴዎች እንዲያፋጥን የሚጠይቁ መፈክሮችን ያነገቡ ናቸው” ብለዋል።
ይሁንና “የለውጡ ተቃራኒ ኃይሎች እና የእነዚህ ኃይሎች ተቀላቢ አክቲቪስቶች” የኦሮሞ ሕዝብ የለውጥ እንቅስቃሴውን ብሎም የዐቢይን መንግሥት እንዲሁም የክልሉን አስተዳደር በመቃወም ኦሮሚያ በተቃውሞ ሰልፍ የተናጠች በማስመሰል “አጀንዳውን ፍሬም” ለማድረግ ሞክረዋል ሲሉ ወቅሰዋል።
እንደ አዲሱ ገለጻ ከሆነ “ፀረ ለውጥ ኃይሎቹ” ሰልፎቹ ተጠናክረው በመቀጠል ወደ ሁከትና ብጥብጥ እንዲሻገሩ ለማድረግ “ቅጥረኞች እና ገንዘብ መድበው እየተንቀሳቀሱ ነው”።
አክቲቪስት ጃዋር በበኩሉ ሰልፉ በመንግሥት ላይ የተነሳ አመፅ ሳይሆን በለውጡ የተገቡ ቃሎች ትኩረት እንዲሰጣቸውና ገቢራዊ አንዲሆኑ የሚጠይቁ ናቸው ብሏል። የዐቢይን ወይም የለማን አስተዳደር ያለመቀበል እንዳልሆነም ጠቅሷል። ይልቁንም ‹‹መንግሥት የዜጎችን ሕይወት እንዲጠብቅ፣ ተቃዋሚዎችም እንዲደራጁና አቅማቸውን እንዲያሳድጉ የሚያስጠነቅቁ ናቸው›› ያለው ጃዋር በሰልፉ ለተነሱ ጥያቄዎች ፈጥኖ የተግባር ምላሽ አለመስጠት በሽግግር ሒደቱ ላይ “አደገኛ ውጤት” የሚያስከትል መሆኑንም አክሏል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በበኩሉ ባወጣው መግለጫ በሠላማዊ ሰልፉ የኦሮሚያ የፀጥታ አባላትም መሳተፋቸውን በመጥቀስ መንግሥት ግድያና ማፈናቀልን በማስቆም ኃላፊነቱን እንዲወጣ በሰልፉ ላይ ጥያቄ መቅረቡን ጠቅሷል።
ይሁን እንጂ በነቀምት በነበረው ሰልፍ “ሁለት የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በመንግሥት ወታደሮች ተግድለዋል 12 ተማሪዎችም ቆስለዋል” ያለው የኦነግ መግለጫ ግድያውን የፈጸሙት የመከላከያ ሠራዊትን የደንብ ልብስ የለበሱ የኦሮሚያ ፖሊሶች እንደሆኑ ማወቁንም አመልክቷል።
ይህም “በእሳት ላይ ቤንዚል ማርከፍከፍ” እንደሆነ በመጥቀስ ያለውን ሁኔታ የሚያባብስና ተጠያቂነትና የዘነጋ በመሆኑ መንግሥትና የሚመለከታቸው ሁሉ ተጠያቂነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስቧል።
“መንግሥት ሕዝባችንን ከጥቃት፣ ክልላችንን ከመደፈር እንዲታደግ እንጠይቃለን” በሚል ርዕሰ መግለጫን ያወጣው ኦፌኮ “ትግሉ እየተፋፋመ ባለበት ወቅት እና አብዛኛው ሕዝባችን የዕለት ጉርሱን የዓመት ልብሱን አጥቶ ልጆቹን ለማብላትም ሆነ ለማስተማር ደፋ ቀና በሚልበት ወቅት ላይ ሥልጣን ከእጃቸው ያመለጠው ኃይል ወንድም ወንድሙን እንዲገድል በገንዘብ በመግዛት ሕዝብ በማጋጨት አገር እስከ ማፍረስ ሊሔዱ እንደሚችሉ ፓርቲያችን በየጊዜው በሚያወጣቸው መግለጫዎችም ሆነ ማሳሰቢያ ሲያስጠነቅቅ መቆየቱ ይታወሳል” ብሏል።
የኮንግረሱ አቋም ግጭቶች በሠላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈቱና በዜጎች ሁሉ ተሳትፎ ለሁሉም የምትሆን ኢትዮጵያ እንድትገነባ መሆኑን በመጥቀስም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ግጭቶች ተከስተው ሠላማዊ ዜጎች መገደላቸውንና ከቤት ንብረት መፈናቀላቸውን አውግዟል።
ባሳለፍነው ሐሙስ ኅዳር 27 በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ 14 የፖለቲካ ማኅበራትን ያሳተፈ የምክክር መድረክ ተካሒዷል። “በአንድነት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሽግግር” በሚል መሪ ሐሳብ የተካሔደው ውይይቱ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ማኅበራት በኦሮሞ ሕዝብ ዙሪያ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ተነግሯል። ‹የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ከየት ወዴት እንዲሁም አሁን ያለበት ደረጃና ወደፊት መሆን ስላበት ጉዳይ› ለውይይቱ የመነሻ ጽሑፍን አዲሱ አረጋ አቅርበው ምክከር ተደርጎበታል። በምክክሩ ማብቂያ የጋራ ፎረም ለመመስረት ተስማምተዋል።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ለማ መገርሳ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተባበረና በጋራ መንፈስ እንዲሠሩ ጠይቀዋል።
“ጠላት በየዕለቱ በሚሰጠን አጀንዳ ላይ እየተባላን ውለን እንድናድር እያደረገ ነው” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የፖለቲካ ማኅበራቱ በመረዳዳትና በዘመናዊ የፖለቲካ አካሔድ የሽግግር ወቅት አለመረጋጋቶችን እንዲያልፉም መክረዋል። ይሁንና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ማኅበራት ለችግሮች መላ ከመዘየድ ይልቅ ችግሩን የሚያባብሱ ተግባራትን ሲፈፅሙ እንደሚስተዋልም አንስተው ወቅሰዋል።
የኦፌኮ ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ዶ/ር) በበኩላቸው ፓርቲዎች ከመጠላፍ ወጥተው በጋራ እንዲሰሩና አንድነትን እንዲያጠናክሩ መክረዋል። የኦነግ ሊቀ መንበር ዳውድ ኢብሳም፥ አንድነትን ከማጠናከር ባሻገር መዋሃድ የሚችሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲዋሐዱ፤ መዋሐድ የማችሉትም የሕዝቡን ጥቅም ለማስጠበቅ በጋራ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 4 ኅዳር 29 ቀን 2011