ፊልሞችና ተመልካች የጎደለባቸው የሲኒማ አዳራሾች

0
1021

ኢየሩሳሌም ጋሹ አማርኛ ፊልም አብዝተው ከሚከታተሉ ሰዎች መካከል መሆኗን ራሷ ትናገራለች። አንዳንዴ በሥራ ቀን ብዙ ጊዜ ደግሞ በእረፍት ቀናት ሲኒማ ቤቶች በር ላይ ትገኛለች። አሁን አሁን ግን ያ ልማዷን ቀንሳለች። ‹‹የአማርኛ ፊልሞች ጥራት ጭራሽ እየቀነሰ ነው የሄደው። ተዋንያኑ ልምድ እያገኙ ቢሆንም፣ ተመሳሳይ መልክ ያለው ገጸ ባህሪን ይተውናሉ። በአማርኛ ፊልሞች ላይ ያለው የፈጠራ ሐሳብ በጣም ጥቂት ነው።›› ብላለች።

ኢየሩሳሌም አንዲት ተመልካች ትሁን እንጂ ሌሎች በርካታ የፊልም ተመልካቾችን ወክላ ልትታይ ትችላለች። በሥራ ቀን ማምሻውን፣ በእረፍት ቀናት ደግሞ ግማሹን ቀን የሲኒማ ቤቶች በሮቻቸው ላይ ረጃጅም ሰልፍ ያስተናግዳሉ። አማርኛ ፊልሞች ከመቼውም ጊዜ በላይ ተመልካች ያገኙበት፣ ለዚህም ፊልሞቹን ለማየት ሰዎች እየተጋፋ የሚገቡበት አንዳንዴም ወንበር ሞልቶ የሚመለሱበት ትዕይንት ጥቂት አልነበረም፤ እንደ ኢየሩሳሌም ያሉ ወጣቶችን ጨምሮ።

ይህንንም ተከትሎ ጥቂት የማይባሉ ባለሀብቶችና የንግድ ሥራ ሰዎች ዘርፉን ተቀላቅለው ለፊልም ማሳያ የሚሆኑ አዳራሾችን ማዘጋጀቱን ሥራዬ ብለው ተያያዙት። የተመልካች መኖር አንድም ከፊልም ሥራው እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው። ሆኖም እንደጠበቁት የሆነ አይመስልም።

የዴንቨር ሲኒማ ቤት ሥራ አስኪያጅ አሉላ አባይ በዚህ ላይ አስተያየት ሰጥተዋል። እርሳቸው በዋና ሥራ አስኪያጅነት እየመሩት ያለው ዴንቨር ሲኒማ ከሰባት ዓመት በፊት ሲከፈት ብዙ ተመልካች በሥራ ቀን እንዲሁም በእረፍት ቀና የሚሰለፍበት እንደነበር ያስታውሳሉ። ባሉት ኹለት የሲኒማ ማሳያ አዳራሾች ያሉት ሲሆን በእያንዳንዱ 90 ሰዎችን የማስተናገድ አቅም አለው። በየቀኑም እስከ 6 ፊልሞችን ሲያሳይ፣ ቢያንስ 150 ሰዎች ይታደማሉ።

ቀስ በቀስ ግን የተመልካች ቁጥር መቀነስ ጀመረ። ይህንንም ተከትሎ ሲኒማ ቤቱም የሚያሳያቸውን ፊልሞችና የፊልም ማሳያ ሰዓት መርሃ ግብሩን ከስድስት ወደ ኹለት አወረደ። አሉላ ቀጥለው ይህን አሉ፤ ‹‹እንደውም ከኹለቱ የሲኒማ አዳራሾች መካከል አንዱን ልንዘጋው ነው። በሕንጻው ላለው ሆቴል ተጨማሪ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ አስበናል።›› ሲሉ አሁን ያለውን ሁኔታ ጠቅሰዋል።
ነገሩን በአሃዝ ያብራሩት አሉላ፤ ቀድሞ ከነበረው ተመልካች አንጻር አሁን ምን ያህል እንደቀነሰ አንስተዋል። በዚህም መሠረት አሁን ላይ በሳምንት እስከ 30 ተመልካች ሲታደም በእረፍት ቀናት ደግሞ በቀን 100 ሰዎች ፊልም ሊያዩ ዴንቨር ሲኒማ ይገኛሉ። ሲኒማ ቤቱ በዚህ አያያዝ ወጪውን ለመሸፈን ስለተሳነው በጥቂት ተመልካቹ ላይ የመግቢያ ዋጋን ጨመር ለማድረግ ተገዷል። በዚህም መሠረት በመደበኛ 40 ብር የነበረውን 50 ብር፣ እንዲሁም በእረፍት ቀናት 50 ብር የነበረውን 60 ብር አድርጓል።

ይህ የፊልም የተመልካች ቁጥር መቀነስ በአዲስ አበባ በሚገኙ ሲኒማ ቤቶች ብቻ ሳይሆን ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ ከተሞችም ተስተውሏል። ለዚህም ጥሩ ማሳያ አዳማ ከተማ ናት።
በአዳማ ከተማ የሚገኘው ኦልያድ ሲኒማ ምንም እንኳ አንድ ሺሕ ሰው እንዲይዝ ተደርጎ የተገነባ ቢሆንም፣ አንድ ተመልካች እንኳ ሳይገኝ የፊልም መርሃ ግብሮች የሚያልፉበት ቀን ጥቂት አይደለም። ‹‹በእሁድ ቀን እስከ 150 ሰዎች ይመጣሉ፣ በሥራ ቀን ግን በአማካይ በቀን 10 ሰዎች፣ አንዳንዴም ምንም ሰው አይገኝም›› ሲሉ አስተያየት የሰጡት በሲኒማ ቤቱ ሠራተኛ የሆኑት ኪያ ብርሃኑ ናቸው።
‹‹አዳራሹን ለሲኒማ ቤት በወር 50 ሺሕ ብር ነው የተከራየነው። የመግቢያ ዋጋውም ለአንድ ሰው አርባ ብር ነው። እናም አሁን ምንም ዓይነት ትርፍ እያገኘን አይደለም›› ብለዋል።

ለምን ተመልካች ቀነሰ?
ይህ ጥያቄ ብዙ ምርምርና ዳሰሳ የሚሻ ይሆናል። የተለያዩ የፊልም ባለሞያዎች ግን ግምታቸውን ገልጸዋል። በአገር ፍቅር ቴአትር የመድረክ አስተባባሪና ተዋናይ ዮሐንስ አፈወርቅ በቴአትር እንዲሁም በፊልም ሥራ ከ15 ዓመት በላይ ልምድ አለው። ዮሐንስ እንደሚለው ከሆነ እንደ ኢየሩሳሌም ያሉ ተመልካቾች እንዲቀሩ ምክንያት የሆነው አንድም የፊልሞች ጥራት መቀነስ ጉዳይ ነው። ይህም ከፊልም ቀረጻና ከግብዓት ችግር አይደለም። ይልቁንም ተመሳሳይነት ያላቸው፣ ፈጠራና አዲስነት የተለያቸው ከመሆናቸው ጋር የተያያዘ ነው።

‹‹ተመሳሳይ ታሪኮች በተለያዩ ተዋንያን በተለያዩ ፊልሞች ሲሠሩ ማየት ለተመልካች አሰልቺ ነው›› ያለው ዮሐንስ፤ ታሪኮችን ከአሜሪካና ከአውሮፓ እንዲሁም ከተለያዩ የዓለም አገራት ፊልሞች ላይ መቅዳትም የተለመደ እየሆነ መምጣቱን ያነሳል።

ከዚህ ባለፈ ተመልካቾች የተሻሉ አማራጮችን ለማየት ችለዋል። ይልቁንም በየቤታቸው በሚገኙ ሳተላይት ዲሾች አማካኝነት የውጪ አገራት ፊልሞችን ያያሉ። ይህም የአገር ውስጥ የፊልም ባለሞያውን ትግል ያበረታዋል። በዚህ መንገድ የቀረበው አማራጭም ተመልካቹ የሚያየውን እንዲመርጥ ግድ ብሎታል።

ዮሐንስ እዚህ ላይ አስተያየት ሲሰጥ የኢትዮጵያ ፊልም ባለሞያዎች ብዙ ተወዳዳሪ እንዳላቸው ማሰብና ማወቅ እንደሚጠበቅባቸው ያነሳል። ሰዎች ሁሌም አዲስ ነገር ይፈልጋሉና ነው። ኢትዮጵያም ብዙ ታሪክና ቅርስ ያላት አገር ብትሆንም በፊልሙ ግን ያንን መጠቀም አልተቻለም። ‹‹ተዋንያን በብቃታቸው ከመመረጥ ይልቅ፣ አዳዲስ ተዋንያን በሰውነት አቋማቸውና በሚታይ ገጽታቸው ነው የሚመረጡት። ይህ ደግሞ ችግሩን አብሶታል›› ዮሐንስ አክሏል።

ለተመልካች ቁጥር መቀነስ የፊልም ጥራት እንደምክንያት ከተነሳ፣ የፊልሙ ‹ኢንደስትሪ› እርምጃ የተስተካከለ እንዳልሆነ ይነግረናል። ለዚህም የፊልም ፕሮድዩሰሮች ምክንያት ሲሰጡ ጣቶቻቸውን የሚቀስሩት አነስተኛ ወደሆነ የሲኒማ ቤት ጥራት፣ በሲኒማ ቤቶች አስተዳደር ወዳለው ቢሮክራሲ እንዲሁም የመንግሥት ትኩረት አነስተኛ መሆን ላይ ነው።

‹‹መንግሥት ፊልም መሥራት ከፍተኛ ትርፍ እንደሚገኝበት ቢዝነስ እንደሆነ ነው የሚያስበው፤ ይህም የተመልካችን ቁጥር በመቀነስ ለዘርፉ ወደኋላ መራመድ አስተዋጽኦ አለው። መንግሥት ፊልም ሥራን ቢዝነስ ከመሥራት በላይ አሻግሮ ማየት ያለበት ጊዜ አሁን ነው። አሉታዊ የሆነ የባህል ተጽእኖን የምንታገልበት፣ አገራችንን የምናስተዋውቅበት፣ ቱሪስት የምንስብበት እና የሥራ እድል የሚፈጠርበት ስፍራ ነው።›› ያለው ከዐስር በላይ ፊልሞችን ፕሮድዩስ ያደረገው የፊልም ባለሞያ ዳዊት ተስፋዬ ነው።

የአማርኛ ፊልሞች ጥራት መቀነስ በተመለከተ የፊልም ደራሲትና አዘጋጅ መዓዛ ወርቁ ስትናገር፤ ብዙ ፊልሞች በባለሙያ ታይተው ሽልማቶችን እንዳገኙ ትገልጻለች። ነገር ግን እነዚህ ፊልሞች ተመልካችን መሳብ አልቻሉም። ታድያ የጥራት ጉዳይ ቢሆን ኖሮ እነዚህ ፊልሞች ብዙ ተመልካች ባገኙ ነገር ስትል ትሞግታለች። የፊልም ተመልካች መቀነስ ምክንያቱ የፊልም ጥራት መቀነስ የሚለው ላይ ይህ በአንጻሩ የሚቀመጥ ነጥብ ነው።

የኢትዮጵያ ፊልም ፕሮድዩሰሮች ማኅበር ሊቀመንበር አርሴማ ወርቁ በመዓዛ ሐሳብ ትስማማለች። ለአርሴማ ደግሞ ጥናቶች አለመደረጋቸው ትልቁ ክፍተት ነው። እንደምትለው ከሆነ የኢትዮጵያ ፊልም ተመልካቾች በደንብ በተከናወነ ጥናት ምልከታ አልተደረገባቸውም። የፊልም ጥራት ማነስ እና የታሪክ ተመሳሳይነት ቢነሳም፣ እንደ ጤዛ፣ ቁራኛዬ እና መሰል ጥራት ያላቸው ፊልሞች ለእይታ ወጥተዋል። በአንጻሩ ግን የተሻለ ገቢ ያገኙት ከእነዚህ ፊልሞች አንጻር በጥራት የሚቀንሱት ናቸው ብላለች።

ቀጥላም ስትገልጽ፣ ‹‹ዘርፉን ከማበረታታት እና ገንቢ አስተያየት ከመስጠት ይልቅ ሚድያው የአማርኛ ፊልሞችን ያብጠለጥላል። በአንድ ጎን ቢያንስ ለአንድ ደቂቃ ማስታወቂያ እስከ 30 ሺሕ ብር ድረስ ይጠይቃሉ። በሌላ በኩል ለጣቢያቸው ፊልሞችን 10 ሺሕ ብር ነው የሚገዙት። ይህ ለአንድ ፕሮድዩሰር ትልቅ ኪሳራ ነው›› አርሴማ እንዳለችው ነው።
እንዲህ ያለው ሁኔታ ፕሮድዩሰሮች ወጪያቸውን እንዲቀንሱ ሲያደርግ ጥራትን በዛው ልክ ይቀንሳል። አርሴማ ይህ ብቻ ሳይሆን የፊልም ሠሪዎችን ማኅበርም አንዱ የፊልም ዘርፍን ያዘገየ ብላ የምትቆጥረው ችግር ነው።

ችግሩ የተፈጠረው ገና ከመሠረቱ መሆኑን የሚያወሳው ደግሞ ተዋናይ ዳንኤል ተገኝ ነው። በጊዜ ሂደት ትኩረት የሳቡ የፍቅርና አስቂኝ ዘውግ ያላቸው ፊልሞች መሆናቸውን የሚያነሳው ዳንኤል፣ በእርሱ እምነት ይህን የሳበው አንድም የወንዶች ጉዳይ የተሰኘው ፊልም ነው። ይህን ፊልም ተከትሎም ፊልም ሠሪዎች የተመልካች ስበት ያለው ወደዛ እንደሆነ በማሰብ ዘውጉን እንዲያዘወትሩ ሆነዋል። አልፎም የተመልካቹ ፍላጎት ያ እንደሆነም ይታሰባል።

የኮሜዲ ዘውግ ያላቸው ፊልሞች ይዘት ደግሞ ጠንካራ አይደለም፤ እንደ ዳንኤል ገለጻ። ‹‹ሰዎችን ሊያስቅ ይችላል ያሉትን ሁሉ ያካትታሉ/አይመርጡም። ይህም ልምድ ያላቸውን የፊልም ሠሪ ባለሞያዎች ከገበያው ገፍቶ ያስወጣል›› ይላል። በዚህም ምክንያት ጥቂት የማይባሉ ተዋንያን ራሱ ዳንኤልን ጨምሮ ወደ ቴአትር እንዲያተኩሩ ምክንያት ሆኗቸዋል።
ነገሩ ለተዋናይት ትዕግስት ግርማም እውነት ነው። ትዕግስት የውጪውን የፊልም አሠራር መከተል ወይም ከዛ መቅዳት ለፊልም አፍቃርያን እርካታ ማጣት ምክንያት ነው ባይ ናት። ይህን ለመቀየርም ፊልሞችን ኢትዮጵያዊ ማድረግና ከባህልና እሴት ጋር የተዛመዱ ታሪኮችን መፍጠር መፍትሔ ይሆናል ትላለች።

እንደ ትዕግስት ገለጻ፤ የፊልም ተመልካች ቁጥር መቀነስ፣ ፕሮድዩሰሮች ጥቂት ፊልሞችን ብቻ እንዲሠሩ በማድረጉ ትወናም የሚያኖር የሥራ መስክ እንዳይሆን እያደረገ ነው። ‹‹ገቢ የምናገኘው ከፕሮድዩሰሮች ጋር በምንገባው ውል መሠረት ነው። እናም ፕሮድዩሰሮች በቂ ገቢ ካላገኙ ለእኛ በአግባቡ ሊከፍሉን አይችሉም። ይህ በእኛ ላይ ትልቅ ተጽእኖ አለው። በሚቀንሰው ገቢ ፊት ኑሮ እየተወደደ ነው የሄደው›› ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች፤ ትዕግስት።

ይህም በመሆኑ ተዋንያን ተጨማሪ ሌላ ሥራ ያስፈልጋቸዋል ብላ ትሞግታለች። ይህም ማንኛውንም ፊልም ጥራቱ ዝቅተኛ የሆነም ቢሆን ለመሥራትና ትርፍ ለማግኘት የእድላቸውን ለመሞከር መገደድ ቀሪ አማራጭ ሆኖ እንዲቀመጥ ያደርጋል።

ሲኒማ ቤቶችስ?
በዳዊት አስተያየት መሠረት ሲታይ የኢትዮጵያን ሲኒማ ወደኋላ ያስቀረው አንዱም የሲኒማ ቤቶች ቢሮክራሲያዊ አሠራር እንደሆነ የሚናገሩ ጥቂቶች አይደሉም። ሲኒማ አዳራሾች ሊያገኙ የሚችሉትን ገንዘብ በመገመት የሚያሳይዋቸውን ፊልሞች ዓይነት ይመርጣሉ። አንዱን በመጣልና ሌላውን በምርጫቸው በማንሳትም ቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ፊልም ሠሪዎች መሥራት ያለባቸው ምን ዓይነት ዘውግ ያለው ፊልም እንደሆነ ይነግራሉ/ይመራሉ። በጥቅሉ ፊልሞችን በአዳራሾቻቸው ለማሳየት የሚፈቅዱትም ሆነ የሚከለክሉት በራሳቸው ባስቀመጡት መስፈርት ነው።

ይህም በተለያየ ዓላማ ፊልሞችን ያመርቱ የነበሩ ፕሮድዩሰሮች ከገበያ እንዲወጡ ያስገድዳቸዋል። ‹‹ብዙዎቹ የሲኒማ ቤት ባለቤቶች በፊውዳል ስርዓት እንደነበሩት ባላባቶች ናቸው። ለሲኒማ እድገት ምንም አስተዋጽኦ አያደርጉም። ከመግቢያ ከሚገኘው ገንዘብ እኩሌታውን የሚወስዱ ቢሆንም እንኳ ተመልካችን ለመጥራት ማስታወቂያ እንኳ አይሠሩም። ሸክሙ ሁሉ ያለው ፕሮድዩሰሩ ጋር ነው›› ስትል አስተያየት የሰጠችው መዓዛ ወርቁ ናት።

መዓዛ እንደምትለው፤ ከፍተኛ የማስታወቂያ እና የፕሮዳክሽን ሥራ፣ ለተዋናይ የሚከፈል ከፍተኛ ክፍያ፣ ግብር እንዲሁም በሲኒማ ቤት አስተዳዳሪዎች ያለው ሙስና ተዳምሮ ልምድ ያላቸውን ፕሮድዩሰርች ከገበያ ገፍቶ ያስወጣቸዋል/አስወጥቷቸዋልም። ይህም ገበያውን በአዳዲስ ገቢና ልምድ የሌላቸው የፊልም ባለሞያዎች እንዲሞላ አድርጓል።
‹‹በአማርኛ ፊልም ተመልካቾች ቁጥር መቀነስ አልተደነቅኩም። እንደውም የሚደንቀኝ ዘርፉ አሁንም ድረስ ችሎ መዝለቁ ነው›› ስትልም አስተያየቷን ሰጥታለች።
የሲኒማ ኢትዮጵያ አስተዳዳሪ ኤልያስ መንግሥቴ በበኩላቸው፣ እድገቱን ያቀጨጨው እውቀትን ቸል ማለትና ዘርፉን በገንዘብ ለመምራት መሞከር ነው ባይ ናቸው። ‹‹የተመልካች ቁጥር የመቀነሱ ምክንያት በደንብ ባልተማሩ ሰዎች የሚመራ ዘርፍ በመሆኑ ነው።›› ብለዋል። በእርሳቸው እይታ፣ ሲኒማ ኢትዮጵያም ከአዲስ ቴክኖሎጂ ጋር አብሮ ያለመዘመኑ ተመልካቹን ገፍቶታል።
‹‹ደንበኞቻችንን ድጋሚ ለማግኘት ሲኒማ ኢትዮጵያ ታሪካዊነቱን ሳይቀንስ መታደስ አለበት›› ሲሉ የጠቆሙ ሲሆን፣ ይህን ለማከናወንም ጥናቶች መከናወናቸውንና መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል። ለዚህ እድሳትም 37 ሚሊዮን ብር ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ሌላው ኤልያስ ችግር ብለው የጠቀሱት የማበረታቻ አለመኖርን ነው። ለምሳሌ የብዙ ዓመት ልምድ ያላቸው ቢሆኑም፤ የሲኒማ ኢትዮጵያ ሠራተኞች አሁን ላይ የሚያገኙት ደሞዝ ኹለት ሺሕ ብር ነው። ሰዎች አዳዲስ ሐሳብ እንዲያፈልቁ፣ ደንበኛን በደንብ እንዲያስተናግዱና ቢዝነሱን እንዲያስኬዱ በደንብ መከፈል ወይም መሸለም አለባቸው›› ኤልያስ ያነሱት ሐሳብ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሲኒማ ቤቶች አስተዳደር የተለያዩ ሥልጣኖችን ሰጥቷል። ከእነዚህም ውስጥ ፊልሞችን ማሳየት፤ ሲኒማ ቤቶችም ማስተባበር፣ ማስተዋወቅ፣ መመሥረት፤ ለእይታ የሚቀርቡ ፊልሞችን ማውጣትና ማሰራጨት እንዲሁም ለሚሰጠው አገልግሎት ገቢ እንዲሰበስብ የሚሉ ይገኙበታል።

ኤልያስ እንደሚሉት ታድያ የሚመለከታቸው ይህን መመሪያ መፈጸምና ማስፈጸም ይጠበቅባቸዋል። ይሁንና የግንዛቤ ማነስ፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የዋጋ መጨመር ወዘተ ለተመልካቹ ቁጥር መቀነስ ተጨማሪ ምክንያት እንደሆኑ ይጠቅሳሉ።

ፊልም ቅንጦት ነው?
የአገር ፍቅሩ የፊልምና የቴአትር ባለሞያ ዮሐንስ እንደሚለው፣ በፊልም የተለያዩ አገራት ባህልና ማንነት ይታያል። ፊልሞች እነዚህን አጉልቶ የማሳየት አቅም አላቸው። ብዙዎች ትኩረት ያልሰጡትን ጉዳይ እንዲያጤኑትም ያግዛሉ፤ ፊልሞች። ታሪክ፣ ባህልና ማኅበራዊ ጭብጦችን በመያዝም ስላለፈውና ስለ አሁኑ ሁኔታ በማስረዳት የተሻለ ማኅበራዊ ትስስር የመፍጠር ኃይል አላቸው።
ከዛም ባለፈ ፊልሞች የሥራ እድልን ይፈጥራሉ። ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች እንደ ጸሐፊ፣ ተዋናይ፣ ዳይሬክተር፣ የገጽ ቅብ ባለሞያ፣ ተዋናይ መራጭ፣ የመብራት ባለሞያ፣ አጃቢ ተዋናይ፣ ሲኒማቶግራፈርና ወዘተ ሆነው መሥራት ይችላሉ።

ፊልም እነዚህን አስተዋጽኦዎች እንዲያደርግ ታድያ ተመልካቾችን ይፈልጋል። ባለሞያዎቹ እንደሚናገሩትም በርከት ያሉ ተመልካቾችን መሳብ አለበት። ለዛ ነው የፊልም ባለሞያዎች ፊልም ቅንጦት እንዳይደለና አስፈላጊ እንደሆነ ደጋግመው ሲናገሩ የሚሰማው።

ዮሐንስ አክሎ እንደጠቀሰው፣ ለፊልም ግብዓት የሚሆኑ ቁሳቁሶች ላይ ያለው ከፍተኛ ቀረጥ ይወርዳል ተብሎ ቢጠበቅም ከፍተኛ ሆኖ ቆይቷል። በዚህ ላይ የማበረታቻዎች እጥረት ለፊልም ፕሮዳክሽን መቀነስ ትልቅ ድርሻ አላቸው።

በተጨማሪም ተመሳሳይ ተዋንያንን በተደጋጋሚ መምረጥ ለአዳዲስ ችሎታዎች በሩን ዝግ አድርጓልና አዲስ ነገር የሚፈልጉ ተመልካቾችን መሳብ አልተቻለም።
‹‹የቅጂ መብትን በተመለከተ በፊልም ስርጭት ወቅት ያለው ሂደትና አካሄድም ፕሮድዩሰሮች በዘርፉ ገንዘባቸውን ፈሰስ እንዳያደርጉ ያደርጋል፤ አዳዲሶቹንም ገና ከውጪ ይገፋል›› ዮሐንስ ያለው ነው።

ኤልያስ በበኩላቸው ዘርፉ ቅድሚያ እንዲሰጠው ማድረግ ያስፈልጋል ባይ ናቸው። እንደ አገር ፍቅር ቴአትር ያሉ ቴአትር ቤቶች ተቋማዊ መዋቅር ያላቸውና በጀት የሚመደብላቸው ሆነው ሳለ፤ የሕዝብ የሆኑ ሲኒማ ቤቶች ግን ያንን እድል አላገኙም ወይም በራሳቸው ተትተዋልና ያ መቀየር አለበት።
በተጨማሪም የጥናትና ምርምር ተቋም አስፈላጊ ነው ይላሉ። ተከተታይት ያለው ሥልጠና በመስጠትም ዘርፉ እውቀት ባላቸው ሰዎች እንዲመራ ማድረግ ተመልካችን በድጋሚ ሊመልስ ይችላል የሚል እምነት አላቸው።

በአዲስ አበባ ባህል ጥበብና ቱሪዝም ቡሮ የክውን ጥበባት ፕሮዳክሽን ዳይሬክተር ሰለሞን ደኑ እንደሚሉት፣ ተገቢ ማበረታቻ ለፊልሙ ዘርፍ አልተሰጠም፤ በተለይ በመንግሥት በኩል። ‹‹ፊልም እንደ ቅንጦት የሚታይ ቢሆንም፣ የአንድ አገር ምስል በመገንባትና ለቱሪዝም በማስተዋወቅ ረገድ ያለው ሚና ቅንጦት እንዳይደለ ይነግረናል።›› ይላሉ ሰለሞን በፊልም መሣሪያዎች ላይ የሚጣለውን ኤክሳይስ ታክስም ሆነ ፊልም ቅንጦት ነው የሚለውን ሐሳብ አይደግፉም። ቢሮውም ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመሆን ፊልም እንደ መሠረታዊ ጉዳይ እንዲቆጠር ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል። በቢሮው ያሉት እንቅስቃሴዎችም ተስፋ ሰጪ በመሆናቸው የመንግሥት ትኩረትና ድጋፍ ሞቶ ተቀብሯል ለማለት የማያስችል ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ከአዲስ ማለዳ ጋዜጣ እህት መጽሔት ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው መጽሔት የተወሰደ፣ በኪያ አሊ ተዘጋጅቶ በሊድያ ተስፋዬ የተተረጎመ፤

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here