ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ የ14 ሚሊዮን ዶላር ማስፋፊያ አደረገ

0
941

ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ በኦሮሚያ ክልል ሰበታ በሚገኘው ፋብሪካው ላይ የ 14 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ የማስፋፊያ ሥራ ማከናወኑን አስታወቀ።
ማስፋፊያዉ ፋብሪካው በሰዓት 32 ሺሕ የማልታ ጊነስ መጠጦችን እንዲያመርት የሚያስችል እንደሆነ ፋብሪካው አስታውቋል። በሌላ በኩል የዲያጆ ኩባንያ አካል የሆነው ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ፣ ጥር 21/2012 አዲሱን የ330 ሚሊ ምርቱን በአዲስ የፕላስቲክ ማሸግያ ለገበያ በይፋ አስተዋውቋል።

ኩባንያው ከሌሎች በዘርፉ ከተሰማሩ ኩባንያዎች ጋር በመሆን የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን ለማከናወን ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል። በዚህም የደቡብ አፍሪካውን ፔትኮ ኩባንያ በመቅጠር የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን በሚመለከት የማማከር ሥራዎችን ያከናውናል። ፕላስቲኮች ተመልሰው አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ለማድረግም ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ተገልጿል።
ከፕላስቲክ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ስለሚመጣው ጉዳትና መልካም አጋጣሚዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን ኩባንያው እንዲሰጥ አብሮ እየሠራ መሆኑንም ፋብሪካው ገልጿል። ማልታ ጊነስ ከነሐሴ 2007 አንስቶ በኢትዮጵያ የማልታ አልኮል አልባ መጠጥ እያመረተ ይገኛል።

ሜታ አቦ ቢራ ፋበሪካ በ 1967 በሰበታ ከተማ ውስጥ የተመሠረተ እና በቢራው ኢንዱስትሪ በርካታ ዓመታትን የቆየ ሲሆን፣ ዲያጂዮ ከተባለ ዓለማቀፍ የአልኮል መጠጥ አምራች ባለቤትነት ስር ይገኛል። ድርጅቱ ፋብሪካውን ለመግዛት 225 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርጓል። እስከ አሁንም ከ123 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማስፋፊያ ሥራ ወጪ ተደርጓል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here