የገናሌ ዳዋ ሦስት ኃይል ማመንጫ ግድብ ጥር 26/2012 ኃይል የማምረት ሥራውን እንደሚጀምር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
ግድቡ 2 ነጥብ 57 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን፣ 254 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ነው። የፕሮጀክቱን የሲቪል እና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎችን የሠራው ሲጂጂሲ (CGGC) የተሰኘ የቻይና ኩባንያ ሲሆን፣ የማማከር ተግባሩን ደግሞ የአሜሪካው ኤም. ደብሊው. ኤች (MWH) ከአገር በቀሎቹ አኪዩትና ኢንቲግሬትድ ጋር በጥምረት እንዳከናወኑት ተገልጿል።
በ2003 ግንባታው የተጀመረው ኃይል ማመንጫው፣ ፕሮጀክቱ አጠቃላይ የፋይናንስ ወጪው 451 ሚሊዮን ዶላር ነው። ከዚህ ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነው ከቻይናው ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ (Exim Bank) በብድር የተገኘ ሲሆን፣ ቀሪው 40 በመቶ ደግሞ በኢትዮጵያ መንግሥት ተሸፍኗል።
ግድቡ ከአዲስ አበባ በ630 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በጉጂ እና ባሌ ዞኖች በሚገኙት የመዳ ወላቡና ጎሮዶላ ወረዳዎች አዋሳኝ ቦታ ላይ ይገኛል። የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ በቴክኒክና ሙያ ለተመረቁ በአካባቢው ለሚኖሩ ወጣቶች እና መጠነኛ ሙያ ላላቸው ሰዎች የተለያዩ ሥራዎችን ለመስጠት ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ውይይት መደረጉም ተገልጿል። በፕሮጀክቱ ግንባታ ወቅትም ለ390 ኢትዮጵያውያን ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር ችሎ ነበር።



