የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫ ቦርድ ወገንተኛ ነው ሲሉ ወቀሱ

0
627

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አድልኦ ያደርገብናል፣ ሕጋዊ እርምጃዎችን አይወስድም እና ከምርጫው በፊት የሚደረጉ ውይይቶችንም ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነም ሲሉ ወቀሱ።

ምክር ቤቱ ከ107 አባል ፓርቲዎቹ ውስጥ ከግማሽ በላዩ የተስማማባቸውን አቋሞች አርብ 22/2012 በራስ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይፋ አድርጓል። ‹‹እንደ አዲስ የተዋቀረው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከወገንተኝነት አልፀዳም። ለብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ ወገንተኝነት ይታይበታል። ገዢው ፓርቲ ሕግ ሲጥስ እየታየ ያለ ቅጣት ታልፏል›› ሲሉ የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ ግርማ በቀለ ተናግረዋል።

‹‹ምርጫ ቦርድ የተሰጠውን ሥልጣን ተጠቅሞ በገለልተኝነት መሥራት የሚገባውን ሥራ መሥራት አልቻለም›› ሲሉም ወቀሳቸውን ሰንዝረዋል። የቦርዱ የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ እንዳሉት፣ ለማንኛውም ውንጀላ ማስረጃ ሊመጣ ይገባል። ብልፅግናም ይህንን አድርጓል ካሉ ማስረጃ ይዘው ካልመጡ ይህ ለምርጫ ቦርድ ብዙም አዲስ ያልሆነ የተለመደ ውንጀላ ነው ሲሉ ገልፀዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ የሚያደርጉበት ጊዜ ይፋ ከመደረጉ በፊት የተወሰኑ ፓርቲዎች ከሕግ አግባብ ውጪ በሆነ መንገድ ቅስቀሳቸውን በተለያዩ አካባቢዎች እያደረጉ ቢሆንም፣ የምርጫ ቦርድ እርምጃ አልወሰደም። ቦርዱ ሕጉን ለጣሱ የፖለቲካ ፖርቲዎች ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ መስጠት ሲገባው ይሄንን በቸልተኝነት ማለፉ ‹‹አንዱን አስሮ አንዱን ደሞ ሜዳ ሰጥቶ፣ አሠልጥኖ አንድ ላይ ማወዳደር እንደማለት ነው የዘንድሮ ምርጫ የሚሆነው›› ሲሉ የኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር እና የምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ ግርማ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ‹‹የተወሰኑ የታዘብናቸው ነገሮች ስላሉ እየመረመርን ነው። አይተን አስፈላጊውን እርምጃ እንወስዳለን›› ያሉት ሶሊያና፣ ‹‹ይህ ግን ፓርቲዎችን ለማሳጣት ተብሎ ሳይሆን እንዲማሩ እና እንዲያስተካክሉ የሚያደርግ ስለሆነ፣ የግድ በአደባባይ የምናደርገው አይደለም›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ምርጫ ቦርድ ከምርጫው በፊት እንድንነጋገርበት የተቀመጡትን አጀንዳዎች አለማስፀደቁ እና ካለመወያየቱ ጭምር በተደጋጋሚ በፓርቲዎቹ ቢጠየቅም፣ ሊያመቻች ፈቃደኛ አይደለም ሲሉም ወቀሳ አቅራቢዎች ጠቅሰዋል።

‹‹ምርጫ ቦርድ የጋራ ምክር ቤቱን በስሩ ለመምራት መፈለጉና ምክር ቤቱ እንደ ተቋም ለመቆም እና ተጠሪነቱ ለፓርቲዎች ሆኖ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማስቻል በሚያደርገው ሂደት፣ ጣልቃ በመግባት ጭምር እንቅስቃሴውን አዳክሟዋል›› ሲሉ ገልጸዋል። ይህንንም ወቀሳ የማይቀበሉት ሶሊያና፣ ምክር ቤቱ ራሱ ኹለት ስብሰባዎችን መበተኑን እና ቦርዱም እንዲህ ዓይነት የምክክር መድረኮችን የመጥራት ሥልጣን እንደሌለው እና ምክር ቤቱ በጠራው መድረክ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

መንግሥት የሕግ የበላይነት የማስከበር እና አገራዊ ሰላም ብሎም መረጋጋት፣ የዜጎች ደኅንነትን ማስከበር በተመለከተም አቅሙ አሽቆልቁሏል ሲሉ ፓርቲዎቹ ወቅሰዋል። በተጨማሪም ቦርዱ ከፓርቲዎች ጋር በጋራ በመሆን ግርታ በፈጠሩ ጉዳዮች ላይ ለማጥራት የጋራ ስብሰባ ይደረግ የሚለውን ውሳኔ እንዲፈፀም አለመደረጉ ክፍተቱን እንዲባባስ ብሎም አንዱን የበታች አንዱን የበላይ እንዲሆን እድል ያመቻቸ ነው ብለዋል። ‹‹አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ ነው።

እንደ ኅብር ኢትዮጵያ ምርጫው ባይደረግ መልካም ነው›› ብለዋል። ‹‹አሁን ባለው የፀጥታ ሁኔታ ምርጫን ሊያስደርግ የሚችል የተስተካከለ ሰላም እና እኩል እድል የለም›› ብለዋል። ከዛ ይልቅ አንድ ላይ በመሆን ለፖለቲካዊ ችግሮቻችን መፍትሄ ማግኘት እና መወያየት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባም ምክር ቤቱ አሳስቧል። በእኩል ሜዳ ላይ መከራከር፣ ሰላም ከማምጣቱ በተጨማሪ በፓርቲዎች መካከል መቀራረብን እና መተማመንን እንደሚያመጣም ምክር ቤቱ ገልጿል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here