ኢዜማ ሰላማዊ እንቅስቃሴዬን አብን አውኮብኛል አለ

0
590

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ባሳለፍነው ሳምንት ጥር 18/2012 በጎንደር ከተማ ሊያካሂድ የነበረውን የሕዝበ ስብሰባ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አባላቶቹን በመላክ ስብሰባዎችን እንዳልከውን አድርጎኛል አለ። የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አንዱአለም አራጌ፣ አብን የኢዜማን እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ መሞከሩን ለፖሊስ ቢያሳዉቁም ፖሊስ ችግሩን ለማስቆም ፈቃደኛ አንዳልነበረ በፓርቲው ጽሕፈት ቤት በሰጡት መግለጫ ገልፀዋል።

“ጎንደር ላይ ሕግና መንግሥት አለመኖሩን አረጋግጠናል። ሰዉ ሕገ መንግሥታዊ መብቱን ተጠቅሞ የመሰብሰብ መብቱ ካልተከበረለት የሚወራዉ ሁሉ ወሸት ይሆናል። መንግሥት ፀጥታን ከማስከበር ይልቅ እራሱ ከጀርባ ሆኖ መምጣት ይታይበታል” ሲሉ ምክትል ሊቀመንበሩ ተናግረዋል። መንግሥት በማን አለብኝነት የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ አፋጣኝ እርምጃ መዉሰድ እንዳለበትና በሕግ አግባብ እንዲመሩ በማድረግ ሕግን እንዲያስከብርም ጠይቀዋል።

ጉዳዩን ለምርጫ ቦርድ ማሳወቃቸዉንም ምክትል ሊቀመንበሩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ፓርቲዉ ጥር 24/2012 በአርባ ምንጭ ከተማ ሕዝባዊ ዉይይት ለማድረግ ጥር 22/2012 ቅስቀሳ በሚደረግበት ጊዜ በአስተዳደር አካላት እንደተከለከለ ምክትል ሊቀመንበሩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በሸዋ ሮቢት ከተማም ተመሳሳይ ችግር ገጥሟቸዉ እንደነበር አንዱአለም ጠቁመዋል። የኢዜማ ሊቀመንበር የሽዋስ አሰፋ በበኩላቸዉ፣ ኢዜማ በአሁኑ ጊዜ በዜጎች ላይ የሚደረጉ የመብት ገደቦችን እንደሚቃወም ተናግረዋል።

“ፓርቲያችን ቅስቀሳ እንዳያደርግ ተገቢ ባልሆነ አካሄድ ሥልጣናቸዉን ማራዘም በሚፈልጉ የወረዳ ካድሬዎች በየወረዳዉ ያሉ አባሎቻችን እንቅስቃሴያቸዉ እየታገደብን ነዉ” ሲሉም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ገልፀዋል። ፓርቲው በአጠቃላይም “ከመንግሥት አካላትና ከስርአት አልበኞች ችግር አየገጠመኝ ነዉ” ብሏል። ኢዜማ ከአብን ጋር ስላለዉ ግንኙነት ለተጠየቀዉ ጥያቄ ከአብን አመራሮች ጋር ጥሩ ወንድማዊ ግንኙነት እንዳላቸው እና የተለየ ግጭት እንደሌላቸው ተናግረዋል። ኢዜማ በሠለጠነ መንገድ በመመራት ፍቃደኛ ከሆኑ ፓርቲዎች ጋር ለመወያየት ዝግጁ መሆኑንና ፓርቲዎች ከሕግ ዉጭ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ግን ማቆም እንዳለባቸዉ አንዱአለም አክለዉ ገልፀዋል።

ፓርቲው የምርጫ ጊዜ ሰሌዳዉ ለተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም እንደሚፈልግ አንዱአለም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ለዚህም ኢትዮጵያ ያለችበት ውቅታዊ ሁኔታ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጁ ስለማያደርጋትና የምርጫ ጊዜዉ ክረምት ላይ በመሆኑ የተመቸ ሁኔታ ስለማይኖር መራዘም አንዳለበት ተናግረዋል። ኢዜማ በሰጠዉ መግለጫ፣ በአገር ደረጃ የሚከሰቱ ክስተቶች የአንድ ክልል ጉዳይ እየሆኑ መታየታቸዉን ገልፆ፤ በተለይም የተማሪዎች እገታ የአንድ ክልልና ፓርቲ መሆን እንደሌለበትና ሁሉም አገራዊ ጉዳይ አድረጎ መረባረብ እንዳለበት አመላክቷል። “የታገቱ ልጆች አገር ናቸዉ። የአንድ ክልል ናቸዉ ብሎ ዝም ማለት ኢ ሰብዓዊ ነዉ” ያሉት የኢዜማ የሴቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ቅድስት ግርማ፣ ለተማሪዎቹ ከእገታ መዉጣት ሁሉም መጮህ እንዳለበት አስገንዝበዋል። በታገቱ ተማሪዎች ላይ የሚደረጉ ሰልፎች በሁሉም ክልሎች እንጂ በአንድ ክልል ብቻ ሊሆን የማይገባ መሆኑንም ቅድስት ገልፀዋል። የአብን ሊቀመንበር ደሳለኝ ጫኔ (ደ/ር) ኢዜማ ባቀረበዉ ቅሬታ ላይ አስተያየት እንደማይሰጡ ገልፀዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here