ተመልካች ያጣው የድሃ ደሃው ጥያቄ ውሎ አይደር!

0
624

በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ በተለይም በሪፖርቶች ላይ ቁጥሩ እየቀነሰ የመጠው የድሃ ደሃ ቁጥር በመሬት ላይ ግን ከእለት ወደ እለት ከፍ እያለ መምጣቱን የኢኮኖሚ ጠበብት ይናገራሉ። በዓለም ባንክ መለኪያ አንድ ሰው በወር ከ 1 ሺሕ 237 ብር በታች የሚያገኝ ከሆነ ከድህነት ወለል በታች የሚገኝ በሚል ይመደባል። እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሻቀብ ላይ ይገኛል። በቅርቡ የሕዝብ ቆጠራ አይካሄድ እንጂ፣ አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥሩ አሁን ላይ 112 ሚሊዮን መድረሱ ይገመታል። በዚህ ደረጃ በማደግ ላይ የሚገኝ ሕዝብ ደግሞ የትምህርት፣ የጤና፣ ንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የምግብ ዋስትና፣ የሥራ እድል እና ሌሎች በርካታ ለኑሮ መሠረታዊ የሆኑ ጉዳዮች ጥያቄም አብሮ እንደሚያድግ የሚያጠራጥር አይደለም። እነዚህ የኅብረተሰብ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ የማያገኙ ከሆነ፣ በማኅበረሰቡ ላይ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና በአገር ላይ ደግሞ ፖለቲካዊ ቀውስን የሚያስከትል መሆኑ እርግጥ ነው።

መንግሥት ባለፉት 20 እና 30 ዓመታት በኢትዮጵያ ድህነትን ለመቀነስ በርካታ ሥራዎችን ሲያከናወን መቆየቱን በመግለፅ፣ ከየትኛውም ጊዜ በተሻለ መልኩ ባለፉት ዓመታት ድህነትን ስለመቀነሱ በስፋት ይገልፃል። በተያያዘም ኢኮኖሚው ያለማቋረጥ እድገት ማሳየቱ እንዲሁም በመንግሥት ኢንቨስትመንት የሚገነቡ ፕሮጀክቶች ቁጥር መጨመር በትምህርት እና ጤና ዘርፎች የታዩ ለውጦች የምጣኔ ሀብት እድገቱ ውጤቶች ተደርገው ይነሳሉ። ሆኖም ዜጎች ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ምጣኔ ሀብታዊ እድገት እኩል ተቋዳሽ ነበሩ ወይ የሚለውን መንግሥት በትኩረት ሊመለከተው እና ሊፈትሸው የሚገባ ጉዳይ ነው።

ምንም እንኳን የአገር ውስጥም ሆነ የውጪ ሪፖርቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ከድህነት ወለል በታች ያለው ነዋሪ 28 በመቶ ብቻ ነው ቢሉም፣ አንዳንድ የኢኮኖሚ ተመራማሪዎች ግን ይህን ቁጥር እስከ 70 በመቶ ያደርሱታል። ከዚህ ቀደምም በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ከድህነት ወለል በታች የሚኖረው ሕዝብ ቁጥር ከ 23 በመቶ አይዘልም የሚለው አሃዛዊ መረጃ የኢትጵያውያንን የኑሮ ሁኔታ የሚገልፅ ስለመሆኑ በርካታ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ጥያቄ ያነሱበታል። ለዚህም መንግሥት የሚያቀርበው ከ70 በመቶ በላዩ ሕዝብ ከድህነት ወለል በላይ ይገኛል። ይህ መረጃ ግምትም ይሁን ሂሳባዊ ስሌት በመሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ያገናዘበ አይደለም የሚል ነው። የእነዚህን የኢኮኖሚ ባለሞያዎች ሙግትና ክርክር ወደ ጎን ብንል እንኳ፣ በየወሩ አሳሳቢ በሚባል መልኩ እየጨመረ ያለው የኑሮ ውድነት በየቀኑ ሚሊዮኖች ከድህነት ወለል በታች መወርወሩ አይቀሬ ነው።

በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ የሚያደርገው የድህነትን ጉዳይ ሕዝቡም ሆነ ፖለቲከኛው ነገሩን አይቶ እንዳለየ ማለፉ ነው። እየተባባሰ ካለው የኑሮ መወደድና ድህነት በላይ የሚያሳስብ፣ ለብዙ ችግሮች መንስኤ የሆነ ጉዳይ ባይኖርም፣ በመከራከሪያና በመሟገቻ ጠረጴዛ ዙሪያ የሚነሳው ጉዳይ ግን ከዚህ የራቀ ነው። በቀጣይ ዓመታት የሚደረጉ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች እና ሌሎች መርሃ ግብሮችን ሲያከናውን የድሃ ድሃውን የማኅበረሰብ ክፍል ያገናዘበ፣ ኢትዮጵያ ያፈራችው ሀብት በፍትሐዊነት ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ የሚሆንበት መንገድ ሊመቻች ይገባል። የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ 77.8 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ወጣት ኑሮውን የሚገፋው በቀን ከኹለት ዶላር ባነሰ የገንዘብ መጠን ነው። በየዓመቱም ከኹለት ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ወደ ሥራ ፈላጊው የእድሜ ክልል ይቀላቀላሉ። በቀጣዮቹ ዐስር ዓመታትም አጠቃላይ የሥራ ፈላጊዎች ቁጥር ከ 90 ሚሊዮን በላይ እንደሚደርስ ይገመታል።

ከአርባ በላይ ከሚሆኑ ዩኒቨርሲቲዎችም በየዓመቱ ከ150 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ይመረቃሉ። እነዚህ ሁሉ አገሪቷ ተጨማሪ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር እንዳለባት የሚያሳዩ ናቸው። ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ግን ድህነት ሊባባስ እንደሚችል ባለሙያዎች ያነሳሉ። እነዚህም መንግሥት ወጣቶችን የሚያሳትፍ ውጤታማ የሥራ ዕድል የመፍጠር ከባድ የቤት ሥራ እንደሚጠበቀው ማሳያ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም። ታዲያ ከኢትዮጵያ የሕዘብ ቁጥር ብሔር፣ ሃይማኖት እና ፆታ ሳይለይ ከግማሽ በላዩን ሕዝብ በጋራ የሚደቁሰው እና እንደ ሰው የመኖር ህልውናውን የፈተነውን ከድህነት በታች ያለውን ሕዝብ ትኩረት መንፈግ ለቀሪውም ቢሆን አደጋ ነው። የገቢ ያለመመጣጠኑ ከእለት ወደ እለት እየሰፋ ሠራተኞች በቀን ለዓአታት ተሰልፈው ትራንሰፖርት በመጠበቅ የሥራ ሰዓታቸውን በሚያባክኑባት አዲስ አበባ፣ ሚሊዮኖች የሚያወጡ መኪኖች ፋሽን በመከተል መቀያየርም እንግዳ አይደለም። የአብዛኛው ከተሜ የምግብ ፍጆታ የሆነው ጤፍ 4500 ብር ተሻግሮ ከድህነት ወለል በላይ ያለውንም ከወር ወር ሰርቶ የሚያድረውንም ዜጋ ተስፋ የሚያሳጣ ነው።

መንግሥት የሚያወጣቸው ፖሊሲዎች የልሂቁን እና ሲያስነጥስ ሳይቀር ድምጹ ሰማይ ድረስ የሚጮኽለትን ብቻ ሳይሆን የብዙኀኑን ጥያቄ የሚመልስ መሆን አለበት። ለዚህም በተለይ የግብርናውን ዘርፍ ማሻሻል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ከመሬት በላይ ያሉ ሃብቶቿ ተቆጥረው የማያልቁት ኢትዮጵያን ከሙሰኞች እና በድሃው ላብ እና እንባ ከሚንደላቀቁ ባለሥልጣኖቿ የሚያላቅቃት የሕግ መዋቅር ካላገኘች እርምጃው እዛው መሆኑ አይቀርም። በሞጣ የሙስሊም ወንድሞቻችን የንግድ ቤቶች በግፍ ተቃጥለው ለዘመናት ለፍተው ያፈሩት ንብረታቸው መውደሙ አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ያስቆጣ የሚወገዝ ድርጊት ሆነ አልፏል። በዚህ ጥቃት ላይም የጫማ ቤቶች በመግባት አዲስ ጫማ በመውሰድ አሮጌ ጫማዎቻቸውን ትተው የወጡ ሰዎችን በማኅበራዊ ሚዲው መሳለቂያ ሆኖ እንደነበርም ይታወሳል። ይህ ድርጊት ግን በግልጽ ድህነት ከሁሉም ችግሮቻችን ጀርባ መኖሩን እና አሁንም ከውጪው ከውስጥም ጠላቶቻችን ይልቅ ድህነት ትልቁ ጠላታችን ሆኖ መቀጠሉን ያሳያል። ስለዚህም ዜጎች፣ መንግሥት፣ የፖለቲካ ኃይሎች እና የሃይማኖት ሰዎች ተባብረው መጪው ትውልድ ይህንን ጠላት ድባቅ መምታቱ አማራጭ የሉለው ጉዳይ ነው። ቀደም ባለው ጊዜ ‹የጋራ ጠላት› እየተባለ የሚነሳው ድህነት መፍትሔ ማስገኘት የሚችል ትኩረት እንዲሰጠው አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 65 ጥር 23 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here