የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የመዋቅር ማሻሻያ ሊደረግባቸው ነው

0
588

አዲስ በተሾሙት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘደንት መአዛ አሸናፊ በቀረበ ጥያቄ መሠረት ቀደም ሲል በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሥር በተዋቀረው የሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ ሥር የተደራጀው የዳኝነት ጉዳዮች ማሻሻያ ቡድን በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሥር ተደራጀ።
ኅዳር 25 የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን የአሠራር ስርዓት እና መዋቅር ለማሻሻል በተዘጋጀ ረቂቅ ጥናት ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን የመዋቅር ማሻሻያ ጥናቱ የጉዳዮች ፍሰት፣ አመራርና አስተዳደርን፣ የወንጀል ቅጣት አወሳሰን ስርዓትን፣ የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ማዕከልን፣ እንደ አዲስ መደራጀት ያለባቸውና የሚዋሐዱ የሥራ ክፍሎችን፣ የተከላካይ ጠበቆችን፣ የፍርድ አፈፃፀም መዋቅርን እስከታች ማደራጀት የሚቻልበት አሠራርን ከግምት ውስጥ ባስገባ ሁኔታ የተዘጋጀ መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድቤት የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት አስታውቋል።
በዚህ ውይይት ላይ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንቷ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በመዋቅር ጥናት እና ረቂቅ ዝግጅት ኮሚቴ የተዘጋጀው የመዋቅር ማሻሻያ ጥናት በአገር ዐቀፍ ደረጃ በተቋቋመው የሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ ሥር ባለው የዳኝት ጉዳዮች ቡድን ፊት ቀርቦ ከተገመገመና ማስተካከያ ከተደረገበት በኋላ ሥራ ላይ ይውላል ብለው ነበር። ከዚህም ባለፈም በጉባዔው ሥር ከሚገኙ 8 ቡድኖች መካከል በዳኝነት ጉዳዮች እንዲሠራ የተደራጀው ቡድን በጠቅላይ ፍርድ ቤት ሥር በአዲስ መልክ ተደራጅቶ እንዲሠራ በፕሬዚደንቷ ሐሳብ ቀርቧል። ፕሬዝዳንቷ የፍርድ ቤቶች ነፃነትን ለማስጠበቅ ሲባል የዳኝት አካሉን የተመለከቱ የማሻሻያ ሥራዎች መከናወን ያለባቸው በፍርድ ቤቱ መሪነት መሆን አለበት ማለታቸውን የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬቱ ገልፆአል።
በዚህም መሠረት የዳኝነት ጉዳዮች ማሻሻያ ቡድኑ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሥር ካለው አማካሪ ጉባዔ ወጥቶ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሥር በአዲስ መልክ በመደራጀት ኅዳር 27 የመጀመሪያ ስብሰባውን አድርጓል። ቡድኑ የሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ ሰብሳቢ የሆኑትን ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመን ጨምሮ በዳኝት፣ በጥብቅና፣ በሕግ መምህርነትና አማካሪነት የካበተ ልምድ ያላቸው 22 አባላትን ያቀፈ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 4 ኅዳር 29 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here