የሴቶች ጥቃት የዕለት ልማድ መሆኑ ቢበቃስ? (ክፍል ሁለት)

0
768

በክፍል አንድ የሴቶች ጥቃት ምንነት፣ የጥቃት አድራሾቹ ማንነት እና መንስዔዎቹን ያስነበበችን ቤተልሔም ነጋሽ በቀጣዩ እና የመጨረሻው ክፍል መጣጥፏ፥ ማኅበራዊ ስንክሳሮችን እና የመፍትሔ ሐሳቦችን ትጠቁማለች።

 

 

የሴቶች ጥቃት የሚፈፀመው ድርጊቱ ከፍተኛ የማዋረድና የማሰቃየት፣ ከባድ ሥነ ልቡናዊ ጫና የሚያሳድር መሆኑ እየታወቀ ነው። ወሲባዊ እርካታን ብቻ ፈልጎ የሚከናወን ሳይሆን ደፋሪዎቹ ራሳቸው በበታችነት ስሜት የሚማቅቁ፣ እልኸኛና በቀለኛ የሆኑ የሥነ ልቡና ጉዳት ያለባቸው፣ ሌላውን በማስጨነቅና በመጉዳት እርካታ የሚያገኙም ጭምር እንደሆኑ የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ።
የጥቃት አድራሹ ሥነ ልቡናዊ ችግርና የበታችነት ስሜት አልያም ሌላ ያልታየ ጉድለት ከመሆኑ ባሻገር ሴትን እንደ እቃ መቁጠር፣ ማንአለብኝነት ወይንም ደግሞ ሴት የሚል የንቀት አለመካከት የወለደውም ሊሆን ይችላል።
ለምሳሌ ፕሮፌሰር ግርማ ብርሃኑ ሚያዚያ 24፣ 2010 ‹ትንሳኤ ኢትዮጵያ› በተሰኘ ድረገጽ ያወጡትና በመካሔድ ላይ የነበረ ጥናት ቅንጭብ ጽሑፍ አስገድዶ መድፈር እና የዘር ማመንጫና ተጓዳኝ አካላትን መጉዳት፣ የኅሊና እስረኞች፣ ታዋቂ ጋዜጠኞች እና ሰብኣዊ መብቶች ተሟጓቾች በኢትዮጵያ እስር ቤቶች የማሰቃያ ዘዴ መሆኑን ይጠቅሳል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ሴት የሰብኣዊ መብቶች ተሟጋቾች፣ የኅሊና እስረኞች እና ታዋቂ ጋዜጠኞች በእስር ላይ እያሉ በአስገድዶ መድፈር የማሰቃያ ዘዴ ጉዳት እየደረሰባቸው ነው።
በእስር ቤት ውስጥ አስነዋሪና ጭካኔ የተመላባቸው ማሰቃያዎች ተግባር ተርታ አስገድዶ መድፈር መጀመሩን የፕሮፌሰሩ ቅንጭብ ጽሑፍ ሲጠቅስ አብሮ እንዳስቀመጠው ይህ ድርጊት የሚፈፀመው ሰለባዎቹን ለማዋረድና ሌሎችንም ለማስፈራራት ነው።
ከሕጉ የማይጣጣም ቅጣት
በኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አስገድዶ መድፈር የሚያስጠይቅና የሚያስቀጣ ወንጀል መሆኑ በግልጽ ተደንግጓል። የሕግ ባለሙያዎችና በሴቶች መብቶች ላይ የሚሠሩ ተቋማት ሠራተኞች ካልሆኑ በስተቀር ሕጉ ለአስገድዶ መድፈር የሚያስቀምጣቸውን ቅጣቶች በሚመለከት ትክክለኛው መረጃ የለውም ለማለት ያስደፍራል። በደፈናው ሕጉ የላላ ነው ወይንም አስገድዶ ከደፈረ ይልቅ ሌባን ይቀጣል ወዘተ ሲባል ይሰማል። በደፈናው ወንጀሉ የበዛው የሕጉ መላላት ስለበዛ ነው ሲባል የሚሰማውም ለዚሁ ነው። ይሔ የሚያስኬድ አይደለም። ያለው ሕግ፣ በአግባቡ ከተተገበረ የሚያንስ አይደለም። ምናልባት ከወንጀሉ ማስረጃ ለማቅረብ አስቸጋሪ መሆንና በአገራችን ከወሲብ ጋር በተያያዘ ያለው ድብቅነት በወቅቱ ወደ ሕክምና ለመሔድ እንቅፋት መሆኑ በቂ ማስረጃ በሌለበት ደግሞ ውሳኔ ለማሳለፍ ለዐቃቤ ሕግ አስቸጋሪ በመሆኑ ነው። ሌላው ዳኞች ራሳቸው (ሴት ዳኞችም ጭምር ሊሆኑ ይችላሉ) በማኅበረሰቡ ወግና ልማድ እንዲሁም እምነት የተቃኙ መሆናቸው፣ ባላቸው የአመለካከት መዛባት ፍርድ የሚያዛቡ የመሆናቸው ጉዳይ ነው።
ለምሳሌ ያህል የኢትዮጵያ ሕግ ባለሙያ ማኅበር እጁን ያስገባበትና ከፍ ወዳለው ፍርድ ቤት ደርሶ ዳኛውን በዲሲፕሊን ጉድለት ከሥራ ያስባረረ ጉዳይ ማንሳት ይቻላል። ባጭሩ አንዲት ለአቅመ ሔዋን ያልደረሰች ታዳጊ በአባቷ በተደጋጋሚ ተደፍራ እናት ባለመኖርዋ የምታማክረው አጥታ ቆይታ በኋላ ታማ ሐኪም ቤት ለወሰደቻት አክስቷ ስትናገር ክስ ተመሥርቶ ጉዳዩ ዳኛው ጋር ሲደርስ ዳኛው ‹ምነው መጀመሪያ ሳያማት ሰውነቷ ለምዶ ሳለ በኋላ አመማት? በእርስዋ ዕድሜ ያሉ ሴት ልጆች እሳት በጉያቸው ይዘው የሚዞሩ ናቸው፤› በማለት በጽሑፍ ሳይቀር አስቀምጠው፣ ተጎጂን ተጠያቂ አድርገው የጎዳዩን ልክ ያጣ ነውረኝነት ሳያዩ በማለፋቸው ተከሰው ከሥራ ገበታቸው እንዲነሱ ተደርገዋል። ይሔ በአመለካከት ችግርና ሴትን ልጅ እንደ ሰው ካለመቁጠር ከጥቃት የመጠበቅ መብትን ከመካድ ውጭ ምን ሊባል ይችላል።
ጥቃትን ለመቀነስ ምን ይደረግ?
በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች የሴቶች ችግር ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የኅብረተሰቡ፣ የጤና ማኅበራዊና ከዚያም አልፎ የደኅንነት ችግር መሆኑ ዓለም ዐቀፍ ደረጃ እየታመነበት መጥቷል።
ይህንን ለመከላከልበአ፣ በአንድ በኩል የፈፀሙትን ድርጊት መለስ ብለው እንዲቃኙና ወደ ጤናማ ሕይወት እንዲመለሱ የትምህርት ፕሮግራሞችን ለጥቃት አድራሾች መዘርጋት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከችግራቸው እንዲያገግሙ ሥነ ባሕርያዊ እንክብካቤና የሙያ እገዛ የጥቃቱ ሰለባ ለሆኑት መስጠት፤ ብሎም በመንግሥት ደረጃ ይህን ማድረግ የአቅም ክፍተት ሲኖር፣ የሴቶች ማረፊያና ልማት ማኅበር ዓይነት ድርጅቶች እንዲበዙና እንዲጠናከሩ አስፈላጊው ድጋፍ ማድረግ ይገባል።
በማንኛውም መስክ ፆታዊ ጥቃት ሲደርስባቸው በሕግ ላይ እምነት ኖሯቸው ተጠቂዎች ወደ ሕግ እንዲሔዱ በየደረጃው የሚገኙ የሕግ አስከባሪ አካላት ለሰለባዎቹ የሚያሳዩት አቀባበልና መስተንግዶ እንዲሻሻል፣ በወሲብ ጥቃት ዙሪያ ተከታታይ ትምህርት መስጠትና የሕጉን ተፈፃሚነት ማገዝ፣ እንዲሁም በግጭትና በመፈናቀል ጊዜ ለሴቶችና ለሕፃናት ልዩ ጥበቃ የሚደረግበትን መንገድ መፍጠር ይጠቀሳሉ።
የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ መሥራት
ጥቃትን ሪፖርት አለማድረግ ወንጀል ነው። ጥቃትን ሪፖርት ማድረግ፣ በኔ ይቁም ማለት መከራው እንዲያበቃ የግል ድርሻን መወጣት ነው። ወንጀለኛን ማቀፍ ይበልጥ ተጎጂን ማሳመም መሆኑን መረዳት ይገባል።
እናቶች በኋላ የሚመጣውን መገለል እና በልጆቹ ሥነ ልቡና ላይ የሚመጣውን ጉዳት ለመቀነስ፣ መዋረድን በመፍራት፣ ደፋሪው የቤተሰብ አባል በሚሆንበት ጊዜም የቤተሰብን ገመና ለመደበቅ በሚል፣ ጉዳዩ ወደ ፍድር ቢሔድ በቤተሰብ መካከል ሊፈጠር የሚችለውን ችግር በመፍራት ጉዳዩን ከማውጣት ይቆጠባሉ። በልጆች ላይ የሚፈፀመውን ከባድ ጉዳት አንዴ ሆኗል ምን ይደረጋል በሚል ፍርዱን በራሳቸው ይወስናሉ። ሴት ለመከራ የተፈጠረች ነች ትቻለው በሚልም ሊሆን ይችላል።
የአመለካከት ለውጥ እናምጣ ሲባልም ራሳቸው ሴቶቹንም የሚያካትት ሊሆን ይገባል። ስለሆነም በመደፈርና በሴቶች ጥቃት ላይ የሚያተኩር ሰፊና ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ለኅብረተሰቡ በማቅረብ በማናቸውም መልክ የሚፈፀም የወሲብ ጥቃት ወንጀል መሆኑን ሁሉም እንዲያውቅ ማድረግ፤ ጥቃት የደረሰባቸው ልጃገረዶችና ታዳጊዎች እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው ወንጀሉ እንደተፈፀመ ወዲያውኑ ለሕግ አካላት ሪፖርት ማድረግ እንዲችሉ ተከታታይ ትምህርቶችን መስጠት ይገባል።
ከዘህ ጋር ተያይዞ የመገናኛ ብዙኃን ሚና ኅብረተሰቡን በማንቃትና መረጃ በመስጠት በኩል ከፍተኛ በመሆኑ ይህንን ድርሻ እንዲወጡ መቀስቀስ ይገባል።
የብዙኃን መገናኛ ሚና
እንደኛ ባለ መገናኛ ብዙኃንን የመረጃ ምንጭ አድርጎ የሚያይ በርካታ ማኅበረሰብ ባለበት የኅብረተሰቡን አመለካከት ለመቀየርና ለውጥ ለማምጣት የብዙኃን መገናኛዎች ሚና እጅግ ወሳኝ ነው። ብዙኃን መገናኛዎች የመረጃ ምንጭ ሆኖ ከማገልገል ባለፈ ኅብረተሰቡ የሚወያይባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በማቀበል፣ መደረግ ያለባቸውና የሌለባቸው ድርጊቶችን በመጠቆም፣ በተለይ ሴቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ ሊኖራቸው ስለሚገባው ሥፍራና መብቶቻቸው መከበራቸው ለማኅበረሰቡም ጭምር ጠቃሚና ግድ መሆኑን በማስገንዘብ ረገድ አዎንታዊ ሚና መጫወት ይችላሉ።
ነገር ግን በተለያዩ ጊዜያት የሚደረጉ ዳሰሳ ጥናቶችና ለጋዜጠኞች የሚሰጡ ሥልጠናዎች ላይ የሚቀርቡ ምክረ ሐሳቦች የሚያሳዩት፣ የሴቶችን ጥቃት በሚመለከት ሚዲያው ወንጀል ሲፈፀም ሪፖርት ከማድረግና የፍርድ ቤት ጉዳዮችና ተያያዥ ሁነቶችን ለዜና ፍጆታ ከማዋል ባለፈ የሚጠበቅበትን ሚና ተወጥቷል ማለት አዳጋች ነው። ከዚህም ሌላ በሴቶች ጉዳዮች ላይ አተኩረው ከሚሠሩ ጥቂት ፕሮግራሞች በስተቀር በሚዲያ ደረጃ ጉዳዩን እንደ ተለያየ ጊዜ የሚፈፀሙ ቁንፅል ድርጊቶች እንጂ ተያያዥነት እንዳላቸው፣ ምንጫቸው ተመሳሳይ እንደሆነ ማኅበራዊ ችግሮች ያለማየት አዝማሚያ ይታያል። ይህም ጉዳዩ ባልተፈፀመም ጊዜ እንደ ርዕሰ ጉዳይ ተቆጥሮ ተከታታይ ዘገባዎች እንዳይሠሩ፣ ምክንያቱ ምንድነው የሚለው ላይ እንዳይሠራ ምክንያት ሆኗል።
ከዚህም የከፋው አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ላይ የተለያዩ ትዕይንቶችና የመዝናኛ ፕሮግራም ላይ የሚሠሩ ባለሙያዎች የመፍትሔ አካል ከመሆን ይልቅ የችግሩ አባባሽ ሲሆኑ ይታያሉ። በሴቶች ላይ ያሉና ማኅበረሰቡ ልማድ አድርጎ የያዛቸው አባባሎችና የተዛቡ አመለካከቶችን በማንፀባረቅና መልሶ በማስተጋባት አመለካከቶቹ ሊለወጡ እንደሚገባቸው ሳይሆን እንዲቀጥሉ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲፈጥሩ ይታያሉ። ይህ ምናልባትም ጠንካራ የሲቪል ማኅበራት ሲፈጠሩ (ያሉት እንደ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ያሉት ከባቢው ሲሻሻል የተሻለ መንቀሳቀስ ሲችሉ) ይህን ሥራዬ ብሎ የሚከታተልና የሚዲያ ይዘትን ከሴቶች ወይም ከስርዓተ ፆታ አተያይ አንፃር አይቶ የማሻሻያ ሐሳብ የሚያቀርብ ሲኖር ሊለወጥ የሚችል ይሆናል። ባለን ጥቂት ልምድ እንኳን በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ በቀረቡ ቅሬታዎችና ዘመቻዎች አንዳንድ ማስታወቂያዎች ሲለወጡ አይተናል።
የወንዶችን አጋርነት መጠቀም
አሁን ያለነው የኅብረተሰብ ክፍሎች (ሴቶችን ይጨምራል) የድሮው በሃይማኖት፣ ባልተፈተሸ ወግና ልማዶች የተተበተበው ማኅበረሰብ ውጤትና አካል እንደመሆናችን በስርዓተ ፆታ ጉዳዮችና ሴቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸው ቦታ ምን መሆን አለበት የሚለውን አስመልክቶ ያለን ግንዛቤ በአብዛኛው ጎዶሎ እና ያልተስተካከለ ነው።
በመሆኑም ለዘመናት የመከላከል ሥራና ትኩረታችን ማኅበረሰቡን አጠቃሎ የያዘና ሴቶች ላይ ብቻ ያተኮረ ነበር። ፍርዳችንና የምንጥለው ሸክም በሴቷ ላይ ነው። በጩቤ ተወጋች፣ ተገደለች፣ አሲድ ተደፋባት የሚለውን ስንሰማ ‹እንዴት ሲገረግ› ሳይሆን ‹ምን ብታደርገው ነው› የሚለው አስቀድሞ ይመጣብናል። ይህ ደግሞ የጥቃቱን ስፋት ሊቀንሰው አልቻለም። ስለዚህ ትኩረቱ ጥቃቱን ወደሚያደርሱት አካላት አዙረን እንዲህ ማድረግ ወንድነት አይደለም ልንል ይገባል።
በዚህ ሁሉ ተስፋ አስቆራጭ የሚመስል እውነታ መካከል ምናልባት ተስፋችን አብዛኛው የሃገሪቱ ዜጋ በለጋ ወጣትነት ዕድሜ ላይ የሚገኝ መሆኑ ይሆናል። እነሱ ላይ፣ ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ላይ አተኩረን ከሠራን የስርዓተ ፆታ መስተጋብሩን ልናሻሽለው፣ ሴቶችን በተሻለ መልኩ የሚያከብር፣ ጥቃትን የሚፀየፍ፣ ጥቃት ፈፃሚዎች የእጃቸውን ዋጋ የሚሰጥ ትውልድ ልንገነባ እንችላለን።

ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው bethlehemne@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 4 ኅዳር 29 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here