እውነቱና «እውነት የሚመስለን››

0
361

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

የወር ገቢያችሁን የሚያስረሳ ሰው ወይም ጉዳይ ገጥሟችሁ ያውቃል? በንግድ ተሠማርተው ዳጎስ ያለ ገቢ ከሚያገኙ ወዳጆቼ ጋር ስገናኝ ደሞዜ ይጠፋብኛል። ከወር ወር እንዴት ቆጥቤ እንደማዘግም፣ ስንቱን እቁብ ጥዬ፣ ስንቱን ብድር ከፍዬ እንደምደርስ እዘነጋለሁ። በእነርሱ ዓለም ስገባ የእኔ ዓለምም እንደ እነርሱ ይመስለኛል።
በተመሳሳይ ሠፊና ዘመናዊ መንገድ ሲሠራ፣ ብዙ ሕንጻ ሲገነባ፣ ቴክኖሎጂ በሽበሽ ሲሆን፣ ዘመናዊ መገበያያዎች ሲተከሉ፣ ባለዲግሪ ሲበራከት፣ ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችን አስፋልቱን ሲያጠብቡ ወዘተ አገራችን ያደገች ይመስለናል። ይህ «መሰለኝ»አችን በየጎዳናው ያሉ ሕፃናትን፣ የራባቸው ወገኖችን፣ ሥራ አጥ ወጣቶችንና ጎስቋላ እናቶችን እንዳናይ ይጋርደናል።
ለመጻፍ የተነሳሁት እንኳን ከእኔ ደምወዝም ጋር ሆነ የአገር ምጣኔ ሀብት አይደለም ጋር ግንኙነት የለውም። በሰሞኑን የተወሰኑ ሴቶች ወደ ሥልጣን መጥተው ስናይ የሴቶች የዕኩልነት መብት ከግቡ የደረሰ እየመሰለን መሆኑ ላይ ነው። ወደ ሥልጣን በመጡት ሴቶች «ዓለም» ውስጥ ሆነን እውነታውን እየዘነጋነው ሳይሆን አልቀረም። እንጠይቅ፤ የሴቶች ወደ ሥልጣን መምጣት የሴቶች ጉዳይን አሳሳቢ አጀንዳ ከመሆን ይታደገው ይሆን?
በእርግጥ መሪነቱን የጨበጡት ሴቶች አርዓያ መሆናቸው ሳንዘነጋ ወደፊት የሚሆነውን ግን አናውቅም። ይሁንና የተወሰኑ ሴቶች በአቅምና በችሎታቸው ወደ ሥልጣን መጡ ማለት የሴቶች የእኩልነትና መብት ጥያቄዎች ተመልሷል እንዳልሆነ ይሰመርበት። ሥልጣንን ለሴቶች መስጠት ብቻ የሴቶችን የመብትና እኩልነት ጥያቄ አይመልስም።
ከቀልድ ውስጥ ቅንጣት ቁምነገር አይጠፋምና፤ «አሁንማ ተቆጣጥራችሁት! የወንዶች ጉዳይ ሚኒስትር ልናቋቁም ነው!» ከሚለው ውስጥ ብዙዎች እየመሰላቸው ያለውን ነገር ማየት እንችላለን። ግን ሁሉም እንደነበር በነበረበት ነው። አሁንም የሕክምና ጣብያዎችና ፍርድ ቤቶች ለመስማት የሚዘገንን የሴቶች ጥቃት ጉዳዮችን እያስተናገዱ ናቸው፤ አሁንም አሳዛኝ የጥቃት ዜናዎችን እየሰማን ነው።
ሻገር አድርገን ስንመለከት በዓለማችን ላይ በርካታ የሚባሉ ሴቶች በሥልጣን ላይ የሚገኙባት አፍሪካዊቷ አገር ሩዋንዳ ናት። በሩዋንዳ ፓርላማ ውስጥ 64 በመቶ መቀመጫ በሴቶች ተይዟል። ይህም 19 በመቶ ብቻ ወንበርን ለሴቶች ካስያዘችው ከኃያሏ አሜሪካ ጋር ሲነጻጸር የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት እንዳለ ያሳያል።
ይሁንና የድህነት ቀንበሯን ከተሸከሙ ሕዝቦቿ አብዛኞቹ ሴቶች የሆኑባት ሩዋንዳ ከሴቶች ጥቃትና መብት ጥሰት አልራቀችም። ምንአልባት ዕኩልነት የሰፈነ መስሏቸው ተዘናግተው ይሆን? አላውቅም። ግን «የብዙኃን አገዛዝ የህዳጣን መብት›› በሚባልለት ዴሞከራሲ ከግማሽ በላይ የሆኑ ሴቶች ድምጽም መብትም ተነፍገዋል። ለተማሩትና ቦታውን ለሚመጥኑት ሽመቱ መስጠቱ ተገቢነቱ እንዳለ ሆኖ፤ ገና ብዙ ብዙ መሠራት አለበት።

ሊዲያ ተስፋየ liduabe21@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 4 ኅዳር 29 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here