ከምናብ ወደ እውነት ማን ያስጠጋን?

0
948

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከሐሳባዊነት ሳይላቀቅ የኖረበትን ዘመን እየጠቀሱ የሚያብራሩት ይነገር ጌታቸው፣ ሕዝብ እንዲሁም ፖለቲካ ፓርቲዎች ይመጣል እያሉ የሚጠብቁት ሁሉ በአንጻሩ ሲሆን የታየባቸው የታሪክ አጋጣሚዎች ያወሳሉ። ይህ በሆነበት ሁኔታ አሁን ላይ የሚታዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ‹ብልጽግና ይሸነፋል› የሚል እምነት መያዛቸው ካለፈው ሁኔታ አንጻር መገመት አለመቻል ነው ሲሉ ይሞግታሉ። የ2012 አገራዊ ምርጫንም ብልጽግና ያሸንፋል ሲሉ ከሐሳባዊነትና ምናብ ወጥቶ እውነታውን ወደማየት መሸጋገር ይገባል ብለዋል።

ክርስትያን ታደለ ከመታሰሩ ከቀናት በፊት ስለ ፖለቲካችን በሰፊው ማውራታችንን አስታውሳለሁ። የውይይታችንን መነሻ ብዘነጋውም ሙግቱ ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲ በምርጫው ይሸነፋል አይሸነፍም የሚለው ነበር። ክሪስ ተስፈኛ፤ እኔ ፀለምተኛ ሆነን ያደረግነውን ክርክር ዛሬ ላይ ሳስበው በምናባዊነት እና እውናዊነት መካከል የተደረገ ይመስለኛል።

የአብን ቃል አቀባይ በራሱና በፓርቲው ላይ የጣለውን ተስፋ ሰንቆ ገዥው ፓርቲ መሸነፉ እንደማይቀር ቅንጣት ታኽል ጥርጥር አልነበረውም። የእኔ መንገድ ግን ከዚህ ይለያል። በቀጣዩ አገራዊ ምርጫም ብልፅግናን አሸንፋለሁ ማለት የቁም ቅዠት ይመስለኛል።

ለምን? የሚለውን ጥያቄ ከማንሳቴ በፊት ፖለቲካችን የምናብ እስረኛ ሆኖ መኖሩን ወደኋላ ተመልሼ ጥቂት ላስታውስ። ጄነራል መንግሥቱ ነዋይ የ1953 መፈንቅለ መንግሥት ከመካሄዱ ሰዓታት ቀደም ብለው በቢሯቸው ባካሄዱት ስብሰባ፣ ንጉሡን ለመጣል የተደረገው ቅደመ ዝግጅት ከበቂ በላይ መሆኑን እርግጠኛ ሆነው ተናግረው ነበር። ይሁን እንጂ ውጤቱ የተገላቢጦሽ ሆነ።
ታሪካችን የምኞት ቁራኛ መሆኑ ግን እዚህ ላይ አላቆመም። ከአስራ ሦስት ዓመታት በኋላ የመጡት አብዮተኞች ሕዝባዊ መንግሥት ለመመስረት ከጫፍ ደረሱ። ትግሉ ነው ሕይወቴ ፍፁም ነው እምነቴ! የሚለውን መዝሙር እየዘመሩም ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ሕልው የመሆኗ ዋዜማ ላይ መድረሷን አበሰሩ። ምናብ የተጣባው ፖለቲካችን ግን ልፋታቸውን ሰማይ ላይ ባለ ማማ መሰለው።
ተስፋ ቆርጠን አልቆምንም። ለምን ብለንም አልጠየቅንም። ይልቅ አንድ ቀን በሚል ተስፋ ወደፊት ነጎድን። ሌላ አስራ አራት ዓመት ጠብቀን 1981 መፈንቅለ መንግሥት አካሄድን። ፊልም የሚያስንቅ እውነትን አስታቀፎን ከመሄዱ ውጭ አዲስ ነገር አልተገኘም። ፖለቲካችን ሐሳባዊ እንደሆነ 1997 ባተ። ቅንጅቶች ታሪካችን የጎበጠው ምናባዊ ከመሆናችን ጋር ተዛምዶ እንደሆነ ጠርጥረዋል።

በዚህ የተነሳም የቅደመ ምርጫ ዳሰሳ አድርግን እውነተኛ ውጤታችን ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ያስፈልጋል አሉ። ልደቱ አያሌውና ኃይሉ ሻወል (ኢንጅነር) ቅድመ ጥናት አድርገው የመነሻ ጽሑፍ እንዲያቀርቡ ተመረጡ። ለወራት የተካሄደው የዳሰሳ ውጤት ፍፁም ለየቅል የሚባል ነበር። ኃይሉ ሻወል በእኔ ጥናት ቅንጅት በሰፊ ልዩነት መንግሥት ለመመስረት እንደሚችል አረጋግጫለሁ አሉ።

ቀጥሎ የልደቱ ተደመጠ። የምናገኘው ውጤት መንግሥት ለመመስረት አይደለም 200 ወንበሮች አያስገኝም አለ። ቤቱ ለኹለት ተከፈለ። ማን የነገ እጣ ፋንታችንን በቀረበ መንገድ ተንብዮት ይሆን ብሎ ተጨነቀ። ልዩነቱ የሚጠበቅ ቢሆንም በዚህ ደረጃ መስፋቱ ግን ተገቢ አይደለም ተባለ። አሁንም መሠረታዊውን እውነት መድፈቅ እንጂ መተርጎም የሚችል አልተገኘም።
እንደውም በጊዜ ሂደት ብርሃኑ ነጋን (ፕሮፌሰር) የመሰሉ ፖለቲከኞች ልደቱ አያሌው አስቀድሞም ቢሆን ኢሕአዴግ የሰጠንን ኮታ ያውቅ ነበር የሚል ሽሙጥ ጀመሩ።

ያስደንግጣል! ፖለቲካችንን ከሐሳባዊነት ሊያላቅቅ የሚችለው አጋጣሚ ጨነገፈ። ዛሬ ላይ ሳስበው የልደቱና የኃይሉ የናሙና ውጤት መለያየት መነሻው የትውልድ ዘመናቸው ይመስለኛል። የስላሳዎቹ ትውልድ ማናባዊ ነው። ከኢሕአፓ እስከ ኢጫት፣ ከመኢሶን እስከ ወዝሊግ ብናስስ የምንጨብጠው የረባ ነገር የለም። ግን በዛ መንደር ሰዎች ሽንፈት የሚታሰብ ነገር አልነበረም። እውነቱ ሌላ ቢሆንም በምናብ ፈረስ ከድል ማማ ላይ መውጣት ተለምዷል። እንዲህ ያለው ሀቅ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሰርክ ልማድ ሆኗል።

ዛሬም የምንመለከተው የምናብ ምርኮ መሆንም ከዚህ ይቀዳል። የኦነግ አመራሮች ወደ ሀረር ሄደው ብልፅግናን እንደምናሸንፍ እርግጠኛ ነን ብለዋል። የኦፌኮ ሰዎች ወደ ባሌ አምረተው የራሳችሁ መንግሥት ሊኖራችሁ ወራት ቀሩ የሚል የድል ነጋሪት ጎስመዋል። ጎንደሮች ለብልፅግና ፓርቲ ቀይ ካርድ መዘዋል። የዚህ ድምር የገዥውን ፓርቲ ሽንፈት ይወልዳል የሚል ካለ ግን ወይ ታሪክን ዘንግቷል አልያም የምናብ ፖለቲካን ከዛሬ ዘመን ሊያደርስ አምሮታል። ስድስት ነጥቦችን በመጥቀስ ብልፅግና በቀጣዩ ምርጫ እንደማይሸነፍ ልሟገት።

በኢትዮጵያ 1200 ወረዳዎችና መቶ ዞኖች ይገኛሉ። በእነዚህ የመንግሥት መዋቅሮች በእያንዳንዳቸው ቢያንስ 10 የቀድሞው ኢሕአዴግ የአሁኑ ብልፅግና አባላት ይኖራሉ ብለን እናስብ። ይህ አሃዝ የመንግሥት ካድሬዎች በብዛት የሚገኙባቸውን የቀበሌ መዋቅሮች ሳይጨምር አስራ ሦስት ሺሕ ያህል ዜጎች ሕልውናቸውን ከብልፅግና ጋር ማስተሳሰራቸውን ያረጋግጣል። ለእነዚህ ወገኖች በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ መሸነፍ ሕልወናቸው ላይ የሚቃጣ ጥቃት ነው።

ገዥው ፓርቲ በቀጣይ አገራዊ ምርጫ ሊሸነፍ አይችልም ስንል ገለልተኛ የሆነ ቢሮክራሲ በሌለበት አገር ዴሞክራሲ ቅንጦት ስለሚሆን ብቻ አይደለም። ይልቁኑ ብልፅግና ፓርቲ ዛሬም ገለልተኛ ሊሆን የሚገባውን የፀጥታን የደኅነንት መዋቅር በቁጥጥሩ ስር እንዳዋለው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን በያዙ ማግስት ከፖለቲካ ነፃ የሆነ የፀጥታና የደኅነንት መዋቅር እንደሚገነቡ ቃል ቢገቡም፣ ግብራቸው ግን የዚህ ተቃሪኒ ነው።

የፖሊሲ ኮሚሽነሩ ከአማራ ብልፅግና ፓርቲ፣ የደኅንነት ቢሮ ኃላፊው ከኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ መሆናቸውም ለዚህ አብነት ይመስላል።
ምርጫው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፓርቲ አያሰጋም ስንል ሌላም ማስረጃ ልንጠቅስ እንችላለን። የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ‹ገለልተኛ ነው አይደለም› የሚለው ብዙ ሊያወዛግብ ቢችልም ቢያንስ ግን በአንድ ነገር ላይ እርግጠኛ መሆን ይቻላል። እሱም ቦርዱ አገራዊ ምርጫው ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ ሆኖበታል። በዚህ የተነሳም ትናንት ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እንዳይካሄድ እንቅፋት የሆኑ ሰዎችን በድጋሚ በወረዳና በዞን መዋቅሮቹ ላይ በመቅጠር ላይ ይገኛል።

የአገራችን ፓርቲዎች ከምናብ ባልወረደ ሐሳባዊ መስመር ዴሞክራሲን አምጠን ልንወልድ ነው የሚል እንጉርጉሮ እንዳስደመጡን ከዛሬ ደጃፍ ደርሰዋል። ይሁን እንጂ ቃላቸው ኑፋቄ ነው። ኹለት ነገሮችን እንጥቀስ፤ የመጀመሪያው ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ይተሳሰራል።

የአገራችን ተቃዋሚ ፓርቲዎች መንግሥትን ከመኮነን የዘለለ ግብ የላቸውም። በዚህ ምክንያትም ተፎካካሪ እንጂ ተወዳዳሪ ለመሆን ብዙ ይቀራቸዋል። በነገራችን ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚጠቀሙት ተፎካካሪ ፓርቲ የሚለው ቃል በፖለቲካ ውስጥ ቅይጥ ዴሞክራሲን በሚጠቀሙ ስርዓቶች ውስጥ የሚዘወተር ነው።

ስቴፈን ሌቬቲስኪ ወቅት ጠብቀው ምርጫን ለይስሙላ በሚያካሄዱ መንግሥታት ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች ተቃዋሚ ሳይሆን ተፎካካሪ (competitive party) ተብለው ይጠራሉ ይላል። እንዲህ ያለው ብያኔ ለአገራችን ፖለቲካ በልኩ የተሰፋ ነው። መንግሥት እውነተኛ ዴሞክራሲን ለማስፈን ከፈለገ ቢያንስ ከላይ የተጠቀሱትን ቀላል ቅድመ ሆኔታዎች ሊያሟላ ይገባዋል። የአገራችን ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ከምናብ የዘለለ እውነታን ለመጋፈጥ ከፈለጉ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ነባራዊ ስሪት ታሳቢ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
ማስታወሻ ፦ ለጽሑፉ ማጣቀሻ ‹Six causes of transitional trauma› የሚለውን የመሐመድ አሕመድ ጽሑፍ ተጠቅሜያለሁ ።

ይነገር ጌታቸው ተለያዩ መገናኛ ብዙኀን በማገልገል ላይ የሚገኙ ባለሙያ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው
mar.getachew@gmail.com ሊገኘኙ ይችላሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 66 ጥር 30 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here