የታዬ ደንደአ ኹለት ሚሊዮን ብር

0
677

የኦሮሚያ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ታዬ ደንደአ የራሳቸውንም ይሁን የፓርቲያቸው አቋም ባገኙት አጋጣሚ ይገልጻሉ። በማኅበራዊ ሚዲያዎች ይሁን ወይም በመደበኛ መገናኛ ብዙኀን በኩል፣ ሐሳባቸውን ከመግለፅ ወደ ኋላ ሲሉ አይስተዋሉም።

ባሳለፍነው ሳምንትም በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀን ትኩረትን ከሳቡ ጉዳዮች መካከል አንደኛው የታዬ ደንደአ ኹለት ሚሊዮን ብር መዘረፍ መሆኑን ብዙዎች የተመለከትነው ጉዳይ ነው።

ታዬም ስለ ዘረፋው ከቢቢሲ አማርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ ቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ ‹ቢን ኢንተርናሽናል› በተባለ ሆቴል ምሳ ለመመገብ መኪናቸውን አቁመው በገቡበት ጊዜ “የመኪናቸው በር በማስተር ቁልፍ ተከፍቶ” ኹለት ሚሊዮን ብር እና ሌሎች ንብረቶች እንደተወሰደባቸው ገለጹ።

የብዙዎች ጥያቄ የሆነው ያንን ያህል ገንዘብ ለምን ያዙ የሚል ነው። ይህ በመኪናቸው ይዘውት የነበረው ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በቢሾፍቱ ከተማ ሥልጠና እየተከታተሉ ለነበሩ ሠልጣኞች የሚከፈል አበል እንደነበር በማስታወስ፣ ከገንዘቡ በተጨማሪ ላፕቶፕ ኮምፕዩተር እና ኹለት የሥራ እና የግል ጉዳዮችን የሚጽፉባቸው ማስታወሻ ደብተሮች ጨምረውም መሰረቃቸውን አልሸሸጉም።
ስርቆቱ ከተፈፀመ በኋላ “የታዬ ማስታወሻ ደብተር እጄ ገብቷል” ብሎ የፌስቡክ ገፁ ላይ የጻፈ ግለሰብ መኖሩንና ጉዳዩን ወደ ሕግ መውሰዳቸውንም አስረድተዋል። የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ ስለጉዳዩ ተጠይቆ ምርመራ እየተካሄደ ስለሆነ ተጣርቶ ሲያልቅ ይፋ እንደሚደረግ የከተማው ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ደረጀ ሙለታ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ማስታወሻ ደብተሩን አግኝተዋል የተባሉት ግለሰብ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ሐሳብ በመስጠት የሚታወቀው ደረጀ ቤጊ የተባሉ ሰው ሲሆኑ፣ የታዬ ደንደአ የማስታወሻ ደብተር እጃቸው ላይ መግባቱን ተክትሎ ሲጠየቁ ደረጀም “እንደማንኛውም ጊዜ በፌስቡክ የመልዕክት ሳጥኔ እንደተላከልኝ አስታውቄ ነው ማስታወሻዎቹ መሰረቃቸውን የጻፍኩት” ብለዋል።
“በውስጥ መስመር ነው የተላከልኝ፤ የለጠፍኩትም [ኢንቦክስ] ብዬ ነው። ታዬ መዘረፉንም ሆነ ስለ እርሱ ምንም የማውቅው ነገር የለኝም” ሲሉ ምላሻቸውን ለቢቢስ ሰጥተዋል።

ይህ ነገር ያልተዋጠላቸው ሰዎች ሐሳባቸውን በስፋት ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲያንሸራሽሩት ነበር። ብልፅግና አሁን ቢሆን ኢሕአዴግ ነው፣ እንደፈለገ ብር እና የመንግሥትን ንብረት ይዞ ይንቀሳቀሳል ያሉም አልጠፉም።

‹ታዬ ኹለት ሚሊዮን ብር አልተሰረቁም፣ ይልቁንም ማስታወሻ ደብተራቸውን ለመቀበልና ለማስመለስ ሲሉ ያደረጉት ነው› ያሉም አሉ።
አንዳንዶቹማ አንድ የመንግሥት አመራር ይህን ያህል ብር በቀላሉ እንዴት በመኪና ይዞ ይዞራል? ይህን መቀበል አይከብድም? አሁን ነው ‹‹ብልፅግና›› ሲሉ የአመራሩን ሐሳብ አጣጥለዋል።
አዲሰ ማለዳ ጋዜጣም በጥር 30/2012 እትሟ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች ሥልጠና በመንግሥት ወጪ መደረጉ ቅሬታ ማስነሳቱ መዘገቧም ይታወሳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 67 የካቲት 7 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here