ዛሬ፣ ኅዳር 29፣ 2011 የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው። የኢትዮጵያን ፌዴራላዊ አወቃቀር በሕግ ያፀናው ሕገ መንግሥት የፀደቀበትን ኅዳር 29 ቀን ታክኮ የሚከበረውን ይኼንን የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀንን ታምራት አስታጥቄ ፌዴራሊዝሙ መነሻው ምንድን ነበር? እንከኖቹ ምንድን ናቸው? ስለ ወደፊቱስ ምን ይደረግ በሚል የጥናት ሰነዶችን በማገላበጥ እና ባለሙያዎችን በማነጋገር የሚከተለውን ጽሑፍ ለሐተታ ዘ ማለዳ አዘጋጅቷል።
እንደመነሻ
በተለያዩ የታሪክ መዛግብት እንደሰፈረው በታኅሣሥ 1953 በንዋይ ልጆች ፊታውራሪነት የተካሔደው መፈንቅለ መንግሥት (አንዳንዶች ‹የታኅሣሥ ግርግር› ይሉታል) ገዝፎ ይታይ የነበረውን “ሰማይ አይታረስ፣ ንጉሥ አይከሰስ” ይትባሕል ከሥረ መሠረቱ እንዲናድ በማድረግ ያበረከተው ትዕምርታዊ አስተዋጽኦው በብዙዎች ምሥክርነት ይሰጠዋል።
ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩትንና የሚያስተምሩትን ያካተተውና በተለምዶ “የተማሪዎች እንቅስቃሴ” በመባል የሚታወቀው ንቅናቄ አጀማመሩ ግብታዊ እንደነበር የሚገልጹት ዓለማየሁ አረዳ (ዶ/ር) “ምሁሩ” በተሰኘ በ2010 አሳትመው ባስነበቡት መጽሐፍ ላይ “ምሁራንና ወጣቶች ከትምህርት ተቋማቱ ብዙም ባልራቁ ቦታዎች ተወስነው ‹መሬት ላራሹ ይሰጥ፣ የሕዝብ መንግሥት ይመሥረት፣ የአስገባሪዎች ስርዓት ይፍረስ፣ የብሔሮች መብት ይከበር፣ ወዘተ› የሚሉ የለውጥ ማጠንጠኛ መፈክሮችን ሲያሰሙ የተደራጀና ዘላቂነትን የሚያረጋግጥ ፍኖተ ካርታ አልነበረውም” ብለዋል። “የብሔር ጥያቄ” የሚለው ጉዳይ የተነሳው እና እስከዛሬም የዘለቀው በዚህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ መሐል ነው።
የብሔር ጥያቄ መነሻ
በ1961 በዋለልኝ መኮንን የተጻፈችው ‹On Question of Nationalities in Ethiopia› አጭር መጣጥፍ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ልሳን “ታገል” በምትባል መጽሔት ላይ መሰራጨቷ የብሔር ጥያቄን ፊሽካ በይፋ አስነፍታ ያስጀመረች ለመሆኑ በብዙዎች ይታመናል። ዋለልኝ ጽሑፉን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተሰበሰቡበት ልደት አዳራሽ ውስጥ በንባብ አሰምቶም እንደነበር ዓለማየሁ ራሳቸውን በእማኝነት በመጥቀስ የነበረውን አጠቃላይ ድባብ እንዲህ አስቀምጠውታል። “ያንን ጽሑፍ በዚያ ዕለት ያዳመጠ ተማሪ መንፈሱ በተቀላቀለ ስሜት ውስጥ ሆኖ ከአዳራሹ እንደወጣ እገምታለሁ። እኔም ራሴ እጅግ በተሳከረ ስሜት ውስጥ እንደነበርኩ፣ በውስጤ መጠነኛ ድንጋጤ ተፈጥሮ እንደነበር አስታውሳለሁ።” (ገጽ 75) የሚሉት ዓለማየሁ በርግጥም በተማሪው የትግል ሒደት የጋራ አገራዊ መፈክር ይዞ በአንድነት ይጮህ፣ ይፈክር፣ ይዘምር የነበረው ወጣት ከዚያች ዕለት በኋላ አንዱ የሌላውን ብሔር ማንነት ለማወቅ ወደጎን መተያየት መጀመሩን ጨምረው ገልጸዋል።
የዋለልኝ ጥያቄ ምንድን ነበር?
ዋለልኝ በወቅቱ ገንኖ የነበረውን የግራ ዘመም ፍልስፍና ጽሑፎችን በማንበብ፣ በመጻፍና በመከራከር ከሚታወቁ ተማሪዎች መካከል አንዱ እንደነበረ በእርሱ ላይ የተጻፉ ጽሑፎች ይመሰክራሉ። ሥሙን ከታሪክ መዝገብ ያሰፈረውን ጽሑፉን ያዘጋጀውም በወቅቱ ይካሔድ የነበረውን የተማሪዎች ንቅናቄ ንድፈ ሐሳባዊ ጥራት እንዲኖረው ለማስቻል እንደነበረ በብዙዎች ይታመናል።
የዋለልኝ ጽሑፍ አይነኬ የነበረውን ርዕሰ ጉዳይ በመንካት በወቅቱ በነበረው ዋነኛ የፖለቲካ ጥያቄ ላይ የውይይት አጀንዳ መክፈት ችሏል። የመከራከሪያ ነጥቦቹም በተገቢው ለማስጨበጥ ጥረት አድርጓል። አንኳር የጽሑፉ ጭብጦች በሚከተሉት ነጥቦች ተቀንብበው ሊቀርቡ ይችላሉ።
ሀ) በአጠቃላይ የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ሒደት የውሸት ብሔርተኝነት ላይ የተመሠረተ ነው ማለቱ፣
ለ) ኢትዮጵያ አንድ ዓይነት መልክ ብቻ ያላት አገር አይደለችም፤ በመሆኑም ትክክለኛው የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ሊፈተሸ ይገባዋል የሚል አንድምታ ያለው የኢትዮጵያን ብዝኃነት ያወጀበት እና
ሐ) ኢትዮጵያን የአማራን ገዢ መደብ የበላይነት በማረጋገጥ አንድ ቀለም ያላት እንድትሆን ተደርጓል በማለት የአማራ (እንዲሁም በሁለተኝነት ደረጃ የትግሬ) ባሕል የተጫነባቸው ተሸናፊ ብሔሮች የሚኖሩባት አገር ናት የሚል አንድምታ ያለው መከራከሪያ ሐሳብ ነው።
ዋለልኝ ይህንን ጽሑፍ ካወጣ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያልበረደ ሁለት የተቃርኖ መከራከሪያዎች ይንፀባረቃሉ፡- የድጋፍና የተቃውሞ። ትክክለኛ ጥያቄ አንስቷል የሚሉት ድጋፍ የሚሰጡትን ያክል በአገራችን ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መካከል ለዘመናት ፀንቶ የቆየውን አንድነት አዳክሟል የሚሉት ደግሞ በብርቱ ይወቅሱታል።
በሰኔ 2010 “ዋለልኝ መኮንንና የብሔር ትግል በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ሑሴን አዳል መሐመድ (ዶ/ር) የተባሉ ምሁር በኢትዮ ፓኖራማ ድረገጽ ላይ በሁለት ክፍል ባስነበቡት ረጅም ሐተታ ስለ ዋለልኝ መኮንን አጨቃጫቂነት በድጋፉም በወቀሳውም የሚነሱት ነጥቦች እንዴት መዳኘት እንዳለባቸው አመላክተዋል። ሁሴን “የብሔር ትግል ፖለቲካ በኢትዮጵያ ያሳደረውን አሉታዊና አዎንታዊ ተፅዕኖ በመገምገም፣ ትክክለኛ አቋም መያዝ የሚቻለው፣ በትግሉ መነሻ ወቅት ላይ ስለ ብሔር ትግል ከዋለልኝ መኮንን አንደበት የወጣውን አስተያየት ወይም በብዕሩ ያስነበበውን ሥነ ጽሑፍ ሚዛን ላይ በማስቀመጥ ከመሆን ይልቅ በትግሉ ረዥም ሒደት በተደረገው ተጨባጭ እንቅስቃሴ፤ ትግሉን ለማሳካት በተነደፈው ተለዋዋጭ ስትራቴጂ፣ ፈር በሳተው የብሔር ትግልና በስተመጨረሻ ትግሉ ባስገኘው ፋይዳ ላይ በመመርኮዝ ሲሆን ነገሮችን በምሁራዊ መንገድ በተጨባጭ ለማየት፣ የተሻለ ዕድል ይሰጣል። ትችቱ ከዚህ በተለየ አግባብ ከሆነ፣ ከወፍ ጫጫታ አይዘልም” በሚል ሐሳባቸውን አስፍረዋል።
ይሁንና ብዙዎች የዋለልኝ አጭር ጽሑፍ ከአጨቃጫቂነቱ በተጨማሪ በኢትዮጵያ የመገንጠልና የብሔር ነፃ አውጪነት ራሳቸውን ላደራጁት ሐሳባዊ ድጋፍ ማስገኘቱን ብዙዎች ይስማሙበታል።
የብሔር ጭቆና፣ የመብት ጭቆና ወይስ ሁለቱም?
ከድኅረ ታኅሣሥ ግርግር በኋላና ወደ አብዮቱ ፍንዳታ መቃረቢያ የፖለቲካ ኃይሉ የተበታተነና ያልተቀናጀ ዝንባሌውን ለውጦ ድርጅታዊ መልክና አመራር የያዘበት ወቅት ነበር። ሀብታሙ ብርሃኑ በ2009 ባሳተሙት “ታላቁ ተቃርኖ” በሚሰኝ መጽሐፋቸው የፖለቲካ ኃይሎች መሰብሰብና መቀናጀት እንደማሳያ ሲጠቅሱ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ከ1964 ጀምሮ ኅልውና አግኝቶ የትጥቅ ትግልን የመርሓ ግብሩ ምሰሶ አድርጓል፣ የሶማሌ ነፃነት ግንባር እንዲሁ በተመሳሳይ ጊዜ ተቋቁሞ ትግሉን አጠናክሯል፣ በተጨማሪም ትግራይ ውስጥ በ1966 መባቻ ትግራይን ከኢትዮጵያ ገንጥሎ ከኤርትራ ጋር የማዋሐድ ዓላማ የነበረው ድርጅት ውጊያ መቀስቀሱን ጠቅሰዋል።
የተቃውሞው ኃይል ራሱን አደራጅቶ በኃይል ከመንቀሳቀሰ ጎን ለጎን በራሳቸው መንገድ ለሚያራመምዱት አመለካከት ርዕዮት ዓለማዊና ኅልዮታዊ ማብራሪያ ሊሰጡ ጥረት ማድረግ የጀመሩበትም ወቅት እንደነበር ተዘግቧል።
ከዋና ዋና አመለካከቶች መካከል የመደብ – ብሔር ቀዳሚነት/ተከታይነት ፍትጊያ የሚጠቀስ ነው። ሀብታሙ መጽሐፋቸው የመደብ-ብሔር ፍትጊያው የኢትዮጵያን መዋቅራዊ ችግር ለመለየት በተደረጉ ያመረሩ ክርክሮችና ትንቅንቆች ውስጥ በተለይ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ወቅት የታየ ፍጭት ነበር ይላሉ። ማብራሪያቸውንም በመቀጠል የቀኝ ዘመምና የግራ ዘመም ፖለቲከኞችንና ምሁራንን ያስተነትናሉ።
ቀኝ ዘመም ዝንባሌ ያላቸው ኃይሎች ዋናው የኢትዮጵያ ማነቆ የመደብ ጭቆና ነው ከማለታቸውም ባሻገር “የብሔር ጥያቄ” ብሎ ነገር እንደማይዋጥላቸው ይገልጻሉ። ለእነዚህ ወገኖች ዋናው ጉዳይ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ነው። ይህ አስተሳሰብ ያላቸው ልኂቃን “የብሔር ጥያቄ” የሚለውን ሥያሜ ራሱ እስካለመጠቀም ይደርሳሉ። ለአብነትም መስፍን ወልደማሪያም (ፕሮፌሰር) በ2005 ባሳተሙት መጽሐፍ “መክሽፈ እንደኢትዮጵያ ታሪክ” ውስጥ በማጣጣል ድምፀት “ጎሰኝነት፣ ቀበሌነት፣ ጎጠኝነት፣ መንደርተኝነት…” ብለው ይጠሩታል።
በሌላ በኩል ግራ ዘመም ዝንባሌ ያላቸው ኃይሎች ደግሞ “የብሔር ጥያቄ”ን ዋናው የኢትዮጵያ ችግር እንደሆነ ያደርጉታል። በመሆኑም ንጉሣዊ አገዛዝ በ“አብዮታዊ” ትግል መለወጥ እንዳለበት የሚያምኑ እንደሆኑ ሀብታሙ ይገልጻሉ። በአንጻሩም የመደብ ጭቆናን የብሔር ጥያቄው ጥገኛ ያደርጉታል። ሀብታሙ “ግራ ዘመሞቹ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እስከመገንጠል የችግሩ መፍትሔ እንደሆነም ይከራከራሉ” ብለው ጽፈዋል።
ይሁንና ሁለቱን ዝንባሌዎች የሚያመሳስላቸው ጥያቄያቸው መልስ ሲያገኝ የሌላውን ጥያቄ አብሮ የሚፈታ ችግር እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል።
የአርበኞች ግንቦት 7 ቃል አቀባይ ኤፍሬም ማዴቦ በበኩላቸው ማርክሲስታዊ ልኂቃኖቻችን ለብዙ ጊዜ የተከራከሩበትና በኢትዮጵያም በ1960ዎቹ ደም የተቃቡበት የመደብ – ብሔር ጭቆና ጥያቄዎች አሁን መነሳቱ ትርጉም የለውም ይላሉ። “እኛ እዚህ ውስጥ የለንበትም፤ ከባለፈው ስህተት ተምረናል። አሁን የሚሻለው መፍትሔው ላይ ማተኮሩ ነው” በማለት ምላሽ የሰጡት ኤፍሬም “መታወቅ ያለበት ቁም ነገር አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የምናየውን ችግር ያመጣው ለብሔር ጭቆና እታገላለው የሚለው ኃይል ነው። ስለዚህ የሚበጀን መፍትሔው ላይ ትኩረት ማድረግ ነው” በማለት መክረዋል።
የፌደራሊዝም ፅንሰ ሐሳብ
በፌደራሊዝም ላይ የተጻፉ ብዙ ድርሳናት ስለፌዴራሊዝም ስርዓት ሲተነትኑ በአንድ በድንበር የተከለለ አገር ውስጥ ያሉ ሁለትና ከዚያ በላይ መንግሥታት በተጻፈ ሰነድ አማካኝነት በግልጽ ተከፋፍሎ የተሰጠ ሥልጣን እና ኃላፊነት ኖሯቸው የተናጠልና የወል አስተዳደር /self rule and shared rule/ አጣምሮ የሚገነባ የአገረ መንግሥት አወቃቀር ነው። በአጭሩ ፌዴራሊዝም የማዕከላዊ መንግሥት እና የክልል መንግሥታት ኅብረት ነው ማለት ይቻላል።
አሰፋ ፍስሐ (ዶ/ር) ለፌደራሊዝም ማስተማሪያነት ባዘጋጁት ያልታተመ መጽሐፍ ላይ እንደጠቀሱት የፌዴራሊዝም ስርዓት ሥልጣንና ኃላፊነትን በማዕከላዊ መንግሥት የተከማቸ ሳይሆን በተለያዩ ደረጃዎች ለሚዋቀሩ ሌሎች የአስተዳደር ማዕከሎች የተከፋፈለ ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ ክፍፍሉ ምን ገጽታ አለው? ማን ምን ያገኛል? የትኛውን? የሚሉ ጥያቄዎች የፌዴራል ስርዓቱን ባሕሪ የሚወስኑ እንደሆኑ ያብራራሉ።
በርካታ ምሁራን ፌዴራሊዝምን የሁለትዮሽ ፌዴራሊዝም እና የትብብር ፌዴራሊዝም በሚል በሁለት ይከፍሉታል። የሁለትዮሽ ፌዴራሊዝም የሚባለው በኅብረቱ ውስጥ ባለው የሥልጣንና የኃላፊነት ድልድል ማዕከላዊ መንግሥቱና ክልሎች በግልጽ ተለይቶ የሚታወቅ፣ ለጣልቃ ገብነት ዕድል የማይሰጥ፣ እኩል ሥልጣንና ኃላፊነት አላቸው የሚል ነው። ስለሆነም በመንግሥታቱ መካከል ያለው ግንኙነት የአግድሞሽ ብቻ ነው ብሎ ያምናል። በመሆኑም በመንግሥታቱ መካከል በሚኖር ግንኙነት ውጥረት እንዲፈጠር ምክንያት የሚሆን ነው። በጣም ግትርና ጥቅምን ለማቻቻል ዕድል የማይሰጥ በመሆኑ ቀላል የጋራ ችግሮችን እንኳን ለመፍታት ረጅም ጊዜ ይወስዳል። የአሜሪካ ፌዴራሊዝም ስርዓት በተለያዩ ስርዓቶች ካለፈ በኋላ አሁን ላይ የደረሰበት ደረጃ ለዚህ በምሳሌነት የሚመጥን እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ።
የትብብር ፌደራሊዝም ግን ሁለቱም (ማዕከላዊ መንግሥትና የክልል መንግሥታት) እኩል ሥልጣን እንዳላቸው ይወስድና የሥልጣንና ኃላፊነት መደራረብ ሊያጋጥም እንደሚችል ታሳቢ ያደርጋል። የመንግሥታት ግንኙነታቸው ማዕከል የሚያደርገውም ትብብርን ሲሆን ግንኙነታቸው የሁለትዮሽና ተዋረዳዊ ነው። ለዘብተኛ የሆነና ችግርን በድርድርና በተግባር በሚያስገኙት ውጤት ላይ ተመሥርቶ የመፍታት አቅጣጫን ይከተላል። የጋራ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ሲያሳልፉም መንግሥታቱ ዕኩል ተሰሚነት ይኖራቸዋል። ይህ ዓይነቱ ፌደራሊዝም ዐቢይ ጉዳይ ላይ በመተባበርና በጋራ እየመከሩ ውሳኔ ለመስጠት ትኩረት ይሰጣል። አገራዊና ክልላዊ ተቋሞች ተራርቀው የቆሙ ሳይሆኑ በብዙ ጉዳዮች ላይ በጋራ የሚሠሩ ናቸው። ማዕከላዊ መንግሥቱና ክልላዊ መንግሥታትም ቀላል የማይባሉ ሥልጣንና ኃላፊነቶች በጋራ ይይዛሉ።
ፌደራሊዝም በኢትዮጵያ የብሔር ጥያቄና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እስከመገንጠል
የኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ስርዓት በ1987 በፀደቀው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት እውን ሆኗል። ይኸው ሕገ መንግሥት በአንቀፅ 1 ላይ አገሪቱ የምትከተለው የመንግሥት አወቃቀር ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት እንደሆነ አስቀምጧል። የዚህ ስርዓት ዋነኛ መለያ ደግሞ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰንና የእኩልነት መብታቸውን መሠረት ያደረገ ፌዴራላዊ የመንግሥት አወቃቀር፣ አደረጃጀትና አሠራር ነው።
በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ውስጥ ከተካተቱት 106 አንቀፆች ውስጥ የተወሰኑ አንቀፆች የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎችን የማያስማሙ ቢሆኑም፣ የአንቀፅ 39ን ያክል ግን አጨቃጫቂ አንቀፅ አለ ለማለት አያስደፍርም። ይህንን ጉዳይ በተመለከተ እ.አ.አ. በ1992 ከታተመው “Ethnic Federalism in a Dominant Party State: The Ethiopian Experience 1991-2000” ከሚለው የሎቪስ አለን ጥናት በኢትዮጵያ ፌዴራል አወቃቀር ግልጽ የሆነ አያዎ እንዳለ ብዙ ጸሐፊዎች ማስፈራቸውን ያስቀምጣል። በአንድ በኩል ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የተወሰኑ ሁኔታዎችን አሟልተው የመገንጠል መብት ተሰጥቷቸዋል። ይህ ከሌሎች የፌዴራል ስርዓታት በተለየ የፌዴራሉ አካላትን ነጻነት የተለጠጠ ያደርገዋል። በሌላ በኩል፣ የአባል አገረ-መንግሥታቱ ሥልጣን በአንፃሩ በጣም ውሱን ነው። የክልል መንግሥታቱ ሥራቸውን ለመሥራት በፌዴራል መንግሥቱ ላይ ጥገኛ ናቸው ብሎ ጽፏል።
ይኸው ጽሑፍ የመገንጠል መብት አንድን አገረ መንግሥት ፌዴራላዊ ለመባል እንዳይበቃ እና ዜጎች ለማዕከላዊ መንግሥቱ ያላቸው ታማኝነት ቀስ በቀስ እንዲቀንስ ያደርገዋል የሚሉ መከራከሪያ ነጥቦች እንዳሉ ይጠቅሳል። በተጨማሪም፣ ክልሎች ኅብረቱን የመልቀቅ ነጻነቱ ሲኖራቸው፣ በማዕከሉ እና አገረ መንግሥታቱ መካከል ያለው የፖለቲካ መዋቅር ከፌዴሬሽን ይልቅ የላላ ንዑስ ብሔራዊ ቁጥጥር ያለው ኮንፌዴሬሽን ዓይነት ይሆናል። ሉዓላዊነት ለብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መሰጠቱም ቢሆን ብሔረሰቦች ከፌዴሬሽኑ ብቻ ሳይሆን ከክልሉ አገረ መንግሥታት ሳይቀር እንዲገነጠሉ ሊያደርግ ይችላል። ይህ ያልተለመደ ሕገ መንግሥታዊ ስርዓት ከመሆኑም ባሻገር የሚመስለው አንድም የፌዴራል ስርዓት ዛሬ ላይ የለም በማለት ያትታል። ሌሎች የፌዴራል ስርዓቶችን ብንመለከት፣ አንዳንድ የዘውግ ቡድኖችን ወይም ክልሎችን የመገንጠል መብት የሰጡ ስርዓቶች አሉ። ነገር ግን እነዚህኞቹ ከሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች ውጪ የተሰጡ ናቸው በሚል ተጽፏል።
በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ፍልስፍና መምህር ግደይ ደረፉ የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም በአብዛኛው ቋንቋ መሠረት ያደረገ ዘውጋዊ ይሁን እንጂ ሁሉም ክልሎች በአንድ ዓይነት መስፈርት ስላልተዋቀሩ ቅይጥ ልንለው እንችላለን ብለዋል። ኢትዮጵያ ከ1983 የመንግሥት ለውጥ በኋላ ፌደራሊዝምን ባትቀበል ኖሮ የመበታተን ዕጣ ይደርሳት ነበር ያሉት ግደይ “ምንም እንኳን የውስጥ ፖለቲካው ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ጉድለት ቢኖረውም ቢያንስ ፌደራሊዝሙ የኢትዮጵያን አንድነት አስቀጥሏል” በሚል ከኢትዮጵያ በአገርነት ደረጃ ከመቀጠል ዕድል ጋር በማያያዝ መከራከሪያ ሐሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ አጋርተዋል።
የኢሕአዴግ የንድፈ ሐሳብ መጽሔት ‹አዲስ ራዕይ› የመስከረም – ጥቅምት 2010 ዕትም የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በሕገ መንግሥቱ ሦስት የተቆራኙ መብቶችን ያቀፈ ፅንሰ ሐሳብ እንደሆነ ያስነብባል። አንደኛ ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ በቋንቋው የመናገር፣ የመጻፍና ቋንቋውን የማሳደግ፤ ባሕሉን የመግለጽ፣ የማዳበርና የማስፋፋት እንዲሁም ታሪኩን የመንከባከብ መብት አለው። ሁለተኛ ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ በሰፈረበት መልክዓ ምድር ራሱን የሚያስተዳድርበት መንግሥታዊ ተቋም የመመሥረት መብት ያለው ከመሆኑ በተጨማሪ በክልልና በፌዴራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብት አለው። ይህም የራስ አስተዳደርን ከጋራ አስተዳደር ጋር ያጣመረ ሕገ መንግሥታዊ ስርዓት መሠረት ጥሏል። ሦስተኛው የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ያልተገደበና እስከ መገንጠል የሚደርስ መሆኑ ነው።
የመገንጠል መብትን በተመለከተ መጽሔቱ የሚከተለውን በተጨማሪነት አስፍሯል። “የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት የወሰኑት በራሳቸው ፍላጎትና በነጻ ፈቃዳቸው ላይ ተመሥርተው ነው። በመሆኑም የመገንጠል መብት ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ማግኘቱ የፌደራላዊ አንድነታችን ምሰሦና መሠረት ይሔው ፍላጎታቸውና ነጻ ፈቃዳቸው መሆኑን የሚያበስር ነው።… የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት የመጨረሻ መዳረሻ አንዳንዶች እንደሚሉት አገር መበታተን ሳይሆን ጠንካራና ዴሞክራሲያዊ አንድነቷ የተጠበቀ አገርን መመሥረት ነው።”
የኦነግ ቃል አቀባይ ቶሌራ ዳባ ከአዲስ ማለዳ የብሔር ጥያቄን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ በኢትዮጵያ ውስጥ ከተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ ሲነሳ የነበረ ጥያቄ ቢሆንም እስከአሁን ግን ለጥያቄው አጥጋቢ የሆነ ፍትሕን፣ እኩልነትን፣ ዴሞክራሲን ያረጋገጠ የፌደራል ስርዓት ተዘርግቷል ብሎ ድርጅታቸው እንደማያምን ገልጸዋል። እንደ ቶሌራ ማብራሪያ በብዛት በስርዓቶቹ ውስጥ ይታይ የነበረው ቀጥታ መልስ ከመስጠት ይልቅ አድበስብሶ የማለፍ ሁኔታ ነው በማለት በየስርዓቱ የተሰጡ ምላሾችን ዘርዝረዋል። “በኃይለሥለሴ ጊዜ የተነሳው ጥያቄ መልሰ ለመስጠት ባለመፈለጉ ለስርዓቱ መደርመስ ዋነኛ ምክንያት ይኸው የብሔር ጥያቄ ነው። ደርግ ጥያቄውን መኖሩን የብሔር እኩልነትን አምኖ በአዋጅ ብቻ ለመመለስ ሞክሯል። ኢሕአዴግ በበኩሉ ጥያቄውን ለመመለስ የፌደራል ስርዓት አወቃቀር ተክሏል። ይሁንና ስርዓቱን ራሱ በሚፈልገው መንገድ ብቻ በማዋቀሩ የሕዝብ ፍላጎትን አላሟላም።”
በሌላ በኩል የአርበኞች ግንቦት 7ቱ ኤፍሬም ለቀረበላቸው ተመሳሳይ ጥያቄ መልስ ሲሰጡ “የብሔር ጥያቄ በኢትዮጵያ ውስጥ ይገባኛል፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው አስተዳዳር፣ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ሕግ ወዘተ ውስጥ እኩል ተቀምጬ፣ እኩል መካፈል አለብኝ የሚለውን እንደግፋለን። ለዘመናት ሲነሳ የነበረው በአካባቢ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ነው። ሉዓላዊነትን ቆርሶ ነው ለክልል የሰጠው እና በዚህ በኩል እናምናለን” ብለዋል።
ይሁንና ቃል አቀባዩ ንቅናቂያቸው ገና የፖለቲካ ፓርቲ ስላልሆነ በእያንዳንዱ የአገሪቱ ጉዳይ ላይ በመወያየት የያዘው አቋም እንደሌለ ገልጸው በግላቸው ግን አንቀጽ 39ን በተመለከተ ያላቸውን አመለካከት ጨምረው አንጸባርቀዋል። ኤፍሬም “በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትሕ፣ ነጻነት፣ እኩልነት እና በየአካባቢው ራስን በራስ ማስተዳደር ሙሉ በሙሉ እስከሰፈኑ ድረስ የመገንጠል ጥያቄ የሚነሳበት ምክንያት የለም። አገርን ለመገንባት ገና መሠረቱን ስትጥል እንገነጥላለን ብለን ለመገንባት አንችልም። ኢትዮጵያን ትገነጠላለች ብለን የምንገነባት አይደለችም፤ ኢትዮጵያ ለብዙ ዘመናት የኖረች አገር ስትሆን አሁንም አንድነቷን ጠብቃ መኖር አለባት” በማለት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የፌደራሊዝሙ እንከኖች
ኦነግ ኢትዮጵያ የተዋቀረችበት በአብዛኛው ቋንቋን መሠረት ያደረገው ፌደራሊዝም ጋር ፀብ እንደሌለው ይግለጽ እንጂ አተገባበሩን በተመለከተ ቃል አቀባዩ ቶሌራ “ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር የብሔሮች መብት በፍፁም አልተከበረም። ለይስሙላ ብቻ በየአካባቢው ያሉ ሰዎችን የመመደብ ሁኔታ ነው ያለው” ብለዋል። በአጠቃላይ ኦነግ ለኦሮሞ ሕዝብ መብትና አገር ባለቤትነት እንዲከበር ሲታገል የሌሎችም መብቶች እኩል መከበር አለባቸው ከሚል አቋም ተነስቶ እንደሆነ የተናገሩት ቶሌራ “ኦነግ የኦሮሞ ሕዝብ መብት መከበር የሌላውም ሕዝብ መብት መከበር ነው ብሎ ያምናል። ስለዚህ እውነተኛ እኩልነት፣ ፍትሕ፣ ወንድማማችነትና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ከተፈለገ ብሔሮች መብታቸውን ተጎናፅፈው የሚፈልጉትን መወሰን አለባቸው” ሲሉ አጠቃለዋል።
ግደይ በበኩላቸው ከቶሌራ ጋር ይስማማሉ። “በመርህ ደረጃ ፌደራሊዝሙ ችግር የለበትም፤ ዋናው ችግር አተገባበሩ ነው” ያሉት ግደይ ኢሕአዴግ ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከማምጣቱ በፊት የግለሰብና አልፎ አልፎ የቡድን መብቶችን ይጥስ የነበረ በመሆኑ እንዲሁም ግንባሩ ግራ ዘመም ሆኖ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ስለሚከተል ክልሎችን ያለምንም ተፅዕኖና ጣልቃ ገብነት ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ አላደረጋቸውም።
የፌደራሊዝሙ ችግር የአፈፃፀም ነው የሚለውን “ፍፁም ውሸት ነው” የሚሉት ኤፍሬም “አሁን በሰፊው ሲተገበር የምናየው ከክልሌ ውጣልኝ የሚባለው የግጭት መንስዔ መጤና መሥራች የሚባለው አመለካከት የፌደራሊዝሙ ውጤት ነው” በማለት የአፈፃፀም ችግር የሚለውን መከራከሪያ ነጥብ አጣጥለውታል።
መፍትሔው ምንድን ነው?
“Ethnic Federalism in a Dominant Party State: The Ethiopian Experience 1991-2000” በሚለው የጥናት ጽሑፍ መሠረት በርካታ የፌዴራሊዝም አጥኚዎች እንደሚሉት አንድ ፌዴሬሽን መንግሥት ከሕግ በታች ካልሆነ ሐቀኛ ሊሆን አይችልም። የፖለቲካ ኃይሎቹ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች ካላከበሩ የተሰጡት ዋስትናዎች ዋጋ የላቸውም። መንግሥት ለሕግ ታዛዥ መሆኑን ለማረጋገጥ የፌዴራል ስርዓቱን አተገባበር እና የፖለቲካ አመራሮችን ሥራዎች መመልከት ያስፈልጋል። ነገር ግን የሕግ ማዕቀፉ በራሱ የፌዴራል ስርዓቱ የፌዴራል እና ክልሎች ግንኙነትን በመወሰን ረገድ መዋቅራዊ የቁጥጥር ድንጋጌዎችን መጣል አለበት። እዚህ ጋር መነሳት ያለበት ጥያቄ ‹የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የፖለቲካ አመራሩ የፌዴራል መርሖችን እንዳይጥስ በቂ የቁጥጥር መንገዶችን አስቀምጧል ወይ?› የሚለው መከራከሪያ ነጥብ ይነሳል።
ኤፍሬም ‹ምን ዓይነት ፌደራሊዝም ለኢትዮጵያ ያስፈልጋታል› ለሚለው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ “እንደዚሁ በአንድ ቡድን ፍላጎት ላይ ብቻ የተመሠረተ ሳይሆን ኅብረተሰቡን በሥፋት ባሳተፈ ጥናት መሠረት የመስኩ ባለሙያዎች ምክረ ሐሳብ ላይ ተመሥርቶ ቢወሰን ይሻላል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ኤፍሬም በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ኮሚሽን ጉዳዮችን በተመለከተ ሊያጠና ስለተቋቋመው ኮሚሽን ተገቢነት አዎንታዊ ምለሻቸውን ሰጥተዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 4 ኅዳር 29 ቀን 2011