የኢትዮጵየ ፌዴራሊዝም እና ዴሞክራሲ

0
495

ዴሞክራሲ የሥልጣን ምንጩ ሁሉም ዜጎች የሆኑበት ፖለቲካዊ ስርዓት ነው፤ ፌዴራሊዝም ደግሞ የተለያዩ ትንንሽ አገራት በጥምረት የሚመሠርቱት የአስተዳደር ዓይነት ነው። ይሁን እንጂ ዴሞክራሲ እና ፌዴራሊዝም ባልተማከለ አስተዳደራዊ ምርጫቸው መሥመር ላይ ይገናኛሉ። የዚህ ዘመን ዴሞክራሲ ተዘዋዋሪ (‹ኢንዳይሬክት›) ዴሞክራሲ በመሆኑ፥ እንደ አቴናውያን ዘመን ነዋሪዎቹ በሙሉ ተሰብስበው በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የሚወስኑበት ቀጥተኛ (‹ዳይሬክት›) ዴሞክራሲ አይደለም። ይልቁንም ወኪሎቻቸውን በየአካባቢያቸው በመምረጥ ይህንን ማድረግ ለሚችለው ምክር ቤት ይልካሉ። በፌዴራሊዝም ማዕከላዊው መንግሥት ብቸኛው የሥልጣን ባለቤት አይሆንም፤ ይልቁንም ከክልል መንግሥታት ጋር ይከፋፈላል። ለዚህም ነው ፌዴራሊዝም የተናጠል እና የወል አመራር (‹ሰልፍ ኤንድ ሼርድ ሩል›) ነው የሚባለው።
ፌዴራሊዝሞች የሚመሠረቱት ሉዓላዊ በሆኑ አገሮች ምክክር ጥምረት መመሥረት ሲችሉ ነው። የኢትዮጵያ ፈዴራሊዝም ግን ማዕከላዊውን መንግሥት በመበተን የክልል መንግሥታት ከተፈጠሩ በኋላ የፌዴራል መንግሥቱን (ወይም ማዕከላዊውን መንግሥት) በነፃ ፈቃዳቸው እንደመሠረቱት ተደርጎ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠው።
የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ከሚነሱበት ዋነኛ ትችቶች መካከል በሕዝቦች ፈቃድ ሳይሆን በገሚሱ ልኂቃን ፈቃድ ሌሎች ላይ የተጫነ ነው የሚለው አንዱ እና ዋነኛው ነው። ምንም እንኳን የ1987ቱ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ሲፀድቅ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከተመረጡ ሰዎች ጋር ውይይት የተደረገበት ቢሆንም፥ በወቅቱ የአርቃቂ ኮሚሽኑ አባል የነበሩት እና ኋላም መፅደቁን አስመልክተው ፊርማቸውን ያኖሩበት የመጀመሪያው የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ነጋሶ ጊዳዳ (ዶ/ር) ሳይቀሩ ደጋግመው እንደተናገሩት አሁንም ድረስ ውይይት እና ሕዝበ ውሳኔ ሊደረግባቸው የሚገቡ የሕገ መንግሥቱ አንቀፆች አሉ።
የሕዝባዊ ተሳትፎ ጉዳይ ትልቅ የዴሞክራሲያዊ መርሕ ጉዳይ ነው። ዴሞክራሲ የሥልጣን ምንጩ ዜጎች ናቸው ሲባል፥ ልኂቃኑ የሚያምኑበት ርዕዮት ምንም ሆነ ምን የመረጣቸውን ሕዝብ ፈቃድ ብቻ ማስፈፀም አለባቸው ማለት ነው። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የትጥቅ ትግል አሸንፎ ሥልጣን የተቆጣጠረው ሕወሓት/ኢሕአዴግ የፌዴራሊዝሙ አወቃቀርም ላይም ይሁን የክልል አወሳሰን ላይ ቀድሞ የነደፈውን ከማስቀመጥ በስተቀር በሕዝቦች ውይይት እና ፈቃድ ላይ ተመሥርቶ ያስተካከለው አንዳችም ነገር የለም። ይህም የሕዝባዊ ተሳትፎ ወይም ይሁንታ መርሕን የሚነቀንቅ ነው። በመሆኑም ሕገ መንግሥቱ ከመፅደቁ አስቀድሞ በሒደቱ ላይ የነበሩት ቅሬታዎች እስካሁን ድረስ የዘለቁበት ምክንያት ይህ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 4 ኅዳር 29 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here