ከታገቱት ሕንዳውያን መካከል ሁለቱ ሲለቀቁ አምስቱ አሁንም ታግተዋል

0
760

‹የአይኤልናኤፍኤስ› እና ‹ኤልሳሜክስ› ለተባለ የሕንድና ስፔን ድርጅቶች በሽርክና የሚሠሩበት ተቋም ሠራተኛ የሆኑት ኢትዮጵያዊያን ለሥራቸው የደሞዝ ክፍያ ባለማግኘታቸው ምክንያት አግተዋቸው ከነበሩት ሰባት ሕንዳዊያን መካከል ሁለቱን በጤና ምክንያት የለቀቁ ሲሆን አምስቱ ሕንዳዊያን ግን አሁንም አልተለቀቁም። ሁለቱ ሕንዳውያን ከመለቀቃቸው በፊት ካሉበት ሥፍራ በኢትዮጵያ ለሕንድ ኤምባሲ ስለጤና ሁኔታቸው የሚገልጽ ኢሜል የላኩ ሲሆን ኤምባሲው ከፖሊሶች ጋር በመሆን እንዲለቀቁ አግዟቸዋል ተብሏል። ከተለቀቁት ሁለቱ ሕንዳውያን መካከል አንዱ በጨጓራ ሕመም ሲሰቃይ የነበረ ሲሆን ሌላው ደግሞ በኃይለኛ ትኩሳት ተይዞ ነበር ተብሏል።
የታገቱት ሰባት ሕንዳዊያን በመንገድ ሥራ ላይ ተሠማርተው የነበረ ሲሆን ለማምለጥ ያደረጉት ሙከራ አለመሳካቱ ተገልጿል። ከመጋቢት ወር ጀምሮ ለሥራቸው የደሞዝ ክፍያ ያላገኙት አጋቾቹ፣ ሕንዳዊያኑን ብንለቃቸው ደሞዛችንን አናገኝም የሚል ሥጋት አላቸው። የአካባቢው ሠራተኞች በድምሩ አምስት ሚሊየን ብር ያህል ደሞዝ እንዳልተከፈላቸው እየተናገሩ ነውም ተብሏል። ከታገቱት የሕንድ ዜጎች ውስጥ አራቱ በቡሬ፣ ሁለቱ በወሊሶና አንዱ በነቀምት የተያዙ ሲሆን በታገቱበት ካምፕ ውስጥ የመንቀሳቀስ ነጻነት ቢኖራቸውም ከካምፑ ግን መውጣት አይችሉም።
የኩባንያው ሠራተኛ የሆኑት ሱሚትራ ኅዳር 23 በትዊተር ገጻቸው የሚሠሩበት ኩባንያ የሕንድ ዜግነት ላላቸው አርባ አራት ሕንዳውያንም ደሞዝ እንዳልከፈላቸው ገልጸዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሕንድ የውጪ ጉዳዮች ሚንስቴር ቃል አቀባይ ራቪቭ ኩማር ‹ኢኮኖሚክ ታይም› ለተባለ የሕንድ ጋዜጣ ስለታገቱት ሕንዳውያን በሰጠው ምላሽ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ችግሩን ለመፍታት በቅርበት እየሠሩ እንደሆነና ጉዳዩ በቅርቡ እንደሚፈታ ገልጿል። ሱሚትራ ሮይ ግን ኅዳር 25 በትዊተር ገጹ ላይ የኢትዮጵያ ፖሊስ ሦስት የሥራ አጋሮቼን አዲስ አበባ ላይ አስሯል ጉዳዩ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ ነው በማለት ጽፈዋል።
ከነቀምት ቡሬ የሚዘረጋውን የመንገድ ግንባታ ንድፍ ለመሥራት፣ ለመገንባትና ለመጠገን ተወዳድረው ያሸነፉትና በሽርክና የሚሠሩት የሕንድና የስፔን ድርጅቶች ከኢትዮጵያ መንገድ ባለሥልጣን ጋር ኅዳር 2008 የስምንት ዓመት ውል ተፈራርመው ነበር። ፕሮጀክቱ የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኘው ከዓለም ባንክ ሲሆን የኮንትራቱ ዋጋ 223 ሚሊዮን ዶላር ነው።
በግንባታው የሚያካተተው 86 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ከነቀምት እስከ አንዶዴ የሚዘረጋው መንገድ አንዱ ሲሆን ሌላው ደግሞ ከአገምሳ እስከ ቡሬ 84 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው መንገድ ነው። ነገር ግን የመንገዶቹ ግንባታ በሚካሔድበት ወቅት አይ ኤልና ኤፍ ኤስ በገጠመው 12.6 ቢሊየን ዶላር (347.6 ቢሊየን ብር) ኪሳራ በዓለም ዙሪያ ያሉትን ፕሮጀክቶችን ለማቋረጥ ተገዷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 4 ኅዳር 29 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here